እነሱ ከአባቶቻቸው አይበልጡም እኛም ከአባቶቻችን አናንስም!
June 14, 2013
ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ወረራና ደባ መፈፀም የጀመረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በአባይ ላይ ግድብ ለመስራት ከመነሳቷ እጅግ በርካታ አመታት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ ሀገራችን ከግብፅም ሆነ ከሌሎች የተቃጣባትን ተደጋጋሚ ወረራዎች በመመከትና ጠላቶቿንም ድባቅ በመምታት ነፃነቷን ጠብቃ መኖሯ ለጠላቶቿ መራር የሆነ እውነት ነው፡፡ በተለይም ከጥንት ጀምሮ የአባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ጥልቅ ምኞት የነበራት ግብፅ በሃገራችን ላይ የፈፀመችውን ግልፅና ድብቅ ወረራ በመመከት ተደጋጋሚ ሽንፈትን አከናንበን መልሰናታል፡፡
ሀገራችንን በጦር አውድማዎች ማሸነፍ እንደማትችል በቂ ትምህርት የወሰደችው ግብፅ ከቅርብና ሩቅ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማበር ዛሬ በኤርትራና በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ የተቀመጡ አማፅያንን በማስታጠቅና ሁለንተናዊ ድጋፍ በመስጠት ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠልና ኢትዮጵያም እንድትዳከም ከፍተኛ ደባ ፈፅማለች ፡፡ ግብፅ ይህን ሁሉ ግልፅ እና ስውር ደባ የምትፈፅመው ኢትዮጵያ በወንዞቿ መጠቀም የማትችል ደካማ ሐገር እንድትሆን ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ጥረቷ ግን ደካማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከመሞከሯ ውጭ የምኞቷን ያህል አልተሳካላትም፡፡ ቢሆንም እኛን ኢትዮጵውያንን እርስ በእርሳችን በማናከስ በጦርነትና በክፍፍል ተጠምደን ወንዞቻችንን የመጠቀም አቅም በማሳጣት ለዘለዓለም ብቸኛ ተጠቃሚ ሆና መኖር ትፈልጋለች፡፡ ይህ ካልተሳካላት ቀጥተኛ ወረራ በመፈፀም የወንዞቻችን ምንጮች ለመቆጣጠር እንደምትመኝ የየዘመናት ሙከራዎቿ ያረጋግጣሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን ግድብ አስመልክቶ ሰሞኑን ከግብፅ በኩል የሚሰማው ዛቻና ማስፈራሪያም ከላይ የተገለፁት እውነታዎች ነፀብራቅ ነው፡፡ በመሠረቱ በአባይ ወንዝ ላይ የተጀመረው ግድብ ከሐገራዊ ጠቀሜታው ይልቅ የገዥውን ፓርቲ የስልጣን እድሜ ለማራዘም የታለመና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚደለቅ ከበሮ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል፡፡ የግድቡ ሥራ የገዥውን ፓርቲ የተለየ አሣቢነትና ተቆርቋሪነት የሚያሳይ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው ልፈፋ ከተራ ጩኸት በዘለለ የዜጎችን ልብ የሚያማልል አይደለም፡፡ በአንፃሩ ከገዥው ፓርቲ አመለካከት ውጭ ያሉ ዜጎችን የግድቡ ሥራ የማይመለከታቸው አድርጎ ለማቅረብ የሚደረገው የወሬ ክምር ልብን የሚሰብር ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያ ክብርና ኩራት መሠዋት ለዜጎችም ጥቅም መጠበቅ እነማን ምን እንደከፈሉና እንደሚያስቡ ለታሪክ በመተው ሃገርን መክዳትና መጥላትን በሌሎች ላይ ለመለጠፍ የሚደረገው ሩጫ ግን እንዲታሰብበት እንመክራለን፡፡
የግድቡ ሥራ ከስም አወጣጥ ጀምሮ የፕሮጀክቱ አነዳደፍ፤ የፋይናንስ አሰባሰብ፣ ግንባታውን የሚያካሂዱ ድርጅቶች አመራረጥና ሌሎችም ጉዳዮች እጅግ ግልፅነት የጎደላቸውና ባለቤትነታቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ ተነጥቆ ለተወሰኑ ቡድኖች በተለይም ለገዥው ፓርቲ ፍላጎት ማሳኪያ እየዋለ መሆኑ ቀርቶ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በሚያስማማ ሁኔታ እንዲካሄድ ፓርቲያችን አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ሐገራችን ለሚያስፈልጋት ዓላማ ሁሉ በወንዞቿ መጠቀሟን በመቃወም በግብፅም ሆነ በሌላ በማንኛውም አካል የሚፈፀሙ ዛቻም ሆነ ሌሎች አሉታዊ ድርጊቶችን ፓርቲያችን አጥብቆ ያወግዛል፡፡ የሃገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅም ማንኛውንም መሰዋዕትነት መክፈልን ከጀግኖች አባቶቻችን የወረስነው አኩሪ ታሪካችን በመሆኑ ይህን ቃል ኪዳን ማክበርና መጠበቅ የፓርቲያችን የፀና አቋም ነው፡፡
በመጨረሻም አሁን የተፈጠረው ውጥረት በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያደርግ እያሳሰብን ነገር ግን ግብፅ ይህን አልቀበልም በማለት ፍላጎቷን በሃይል ለማስፈፀም የምትፈልግ ከሆነ የአባቶቻችንን ታሪካዊ አሸናፊነት የምንደግመው መሆኑን ከታሪክ እንድትማር ለማስታወስ እንገደዳለን፡፡
ሰኔ 7 ቀን 2005 ዓ.ም
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment