የአባይ ውሀ የኢትዬጵያና የግብፅ ውዝግብ
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት የአባይን ውሀ ፍሰት እንዳይቀንስ ለማድረግ ሁሉንም አማራጮች ከመውሰድ እንደማትቆጠብ ግብፅ አስጠነቀቀች ።
የግብፅ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ ስለ አወዛጋቢው የአባይ ግድብ ለደጋፊዎቻቸው ትናንት ማምሻውን ባሰሙት ንግግር ከአባይ ወንዝ አንድ ጠብታ ውሀ እንኳን ቢጎድል ፣ የምንወስደው አማራጭ ደማችንን ማፍሰስ ይሆናል ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP ዘግቧል ። ጦርነት ናፋቂዎች አይደለንም ሆኖም ደህንነታችንን ማንም አደጋ ላይ እንዲጥል አንፈልግም ሲሉም ሙርሲ አስጠንቅቀዋል ። አንድ የሙርሲ አማካሪ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ የግድቡን ሥራ እንድታቆም ግብፅ ትጠይቃለች ብለው ነበር ። የግብፅን አቋም ለማስረዳትም የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ከማል አመር በመጪዎቹ ቀናት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሂሻም ካንዲል ተናግረዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትር ካንዲል ለግብፃውያን ወሀ የሕይወትና የሞት ጥያቄ እንዲሁም የሃገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ዋስትና እንደሆነም አስታውቀዋል ። ስለ ግብፅና ኢትዮጵያ የአባይ ወሐ አጠቃቀም ውዝግብ የተጠየቁት የታንዛንያ የውሀ ህብት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ሱዲ ምኔቴ ውዝግቡ በሰለማዊ መንገድ እንዲፈታ አሳስበዋል ። እንደ ባለስልጣኑ የውሐው አጠቃቀም በትብብር መከናወን ይኖርበታል ።
«ግጭትን ለማስቀረት ሠላማዊ የሚመስለኝ ብቸኛው መፍትሄ የተፋሰሱ አገራት በመተባበር በጠረጵዛ ዙሪያ መወያየታቸው ነው ። ይህ ነው ብቸናው መንገድ ምክንያቱም የውሐ ሃብት አስተዳደር የተፋሰሱን ሃገራት ትብብር ይሻል ። ለብቻ መሥራት አይቻልም ። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የውሀ ሃብት አስተዳደሩን ብቻየን መሥራት እችላለሁ የሚያስብ ከሆነ በጣም ስህተት ነው ። የውሃ ሃብቱን እንዴት በጋራ መጠቀም እንደሚችሉ መነጋገር አለባቸው ። »በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ና የግብፅ ውዝግብ ግብፅ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ችግር መፍጠሩን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በእንግሊዘኛው ምህፃር UNHCR አስታውቋል ። ኮሚሽኑ እንዳለው ግብፅ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸውና ከመንግሥት አስተዳደር በኩል ጥቃት ና ወከባ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል ። ግብፅ ለሚገኙ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ደህንነትና መብቶቻቸውም እንደከበሩ አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸም ዓለም አቀፉ ድርጅት አሳስቧል ።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምታሥገነባዉ የኤሌክትሪክ ሐይል ማመንጫ ግዙፍ ግድብ ሠበብ ከግብፅ ጋር የገጠመችዉ የቃላት አተካራ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ። ግድቡ ወደ ግብፅ የሚፈሠዉን የዉሀ መጠን ይቀንሳል ብለዉ የሰጉት የግብፅ ባለሥልጣናት የግድቡ ሥራ እንዲቆም እስከ መጠየቅ ደርሰዋል። የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሥለ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ባለሥልታናት ጋር ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ እንደሚሔዱ ባለፈዉ ዕሁድ ቢያስታዉቁም ከካይሮ የሚሠማዉ ማሳሰቢያ ግን እንደቀተለ ነዉ። የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ትናንት በሠጡት መግለጫ ግብፅ ወደ ሐገሯ ከሚፈሰዉ የአባይ ዉሀ መጠንም አንዲት ጠብታ እንኳ እንዲቀንስ አትፈቅድም።
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment