Thursday, July 11, 2013

ደሴ በፖለቲካ ቅስቀሳ ተናዉጣለች !

july.11.2013
ሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም
ደሴ በፖለቲካ ቅስቀሳ ተናውጣላች። በአንድ በኩል፣ አንድነት ሕዝቡ ሕገ መንግስታዊ መብቱን የመጠቀም ፣ ሃሳቡን በነጻነት የመግልጽ፣ መሪዎቹን በፈለገ ጊዜ የመሾምና የመሻር መብት እንዳለው እያስተማረ፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለዉን የግፍ ቀንበር በመቃወም፣ እግዚአብሄር የሰጠዉን፣ የአለም አቀፍ ሕግ ሆነ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የፈቀደለትን መብት በመጠቀም ደሴዎች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በላወድ ስፒከር እየቀሰቀሰ ነዉ።
በራሪ ወረቀቶች በስፋት እየተሰራጩ ሲሆን ፓርቲዉ ያዘጋጃዉን ፔቲሽን ሕዝቡ እየፈረመ ነዉ። የደሴ ህዝብ መነሳሳት ከመቼዉም ጊዜ በላይ፣ ደሴ ዙሪያ እንዳሉ ተራሮች ከፍ ከፍ እያለ የመጣበት ሁኔታ ይታያል። ወረቀቶች የሚበትኑና ፔትሽን የሚያስፈረሙ በርካቶች እስርና እንግልት እየደረሰባቸው፣ እንዳይበትኑ እየተከለከሉ ሲሆን፣ በአብያተ ከርስቲያናት፣ ጸሎት ቤቶችና መስኪዶችም ህዝቡን ለመድረስ እየተሞከረ ነዉ።
በሌላ በኩል ገዢው ፓርቲም፣ የራሱን ቅስቀሳ ጀመሯል። «እኛ ከአንድነት የተሻልን ነን። እኛ የለጠ ጥቅምህን እናስጠብቅልሃለን። እኛ ላንተ የቆምን ነን» የሚል ቅስቀሳ ሳይሆን የኢሕአዴግ ካድሬዎች እያደረጉ ያሉት፣ ሕዝብን የማስፈራራትና የማስጨነቅ ቅስቀሳን ነዉ። ወደ ሰልፉ የሚወጡ እንደሚታሰሩ፣ አንድነትን በመደገፋቸውም ትልቅ ዋጋ እንደሚከፍሉ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው ነዉ።
የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች፣ በየቤቱ በመሄድ አንድነትን ከሚከሱበት አባባሎች መካከል «እነርሱ መልሰዉ ቅንጅትን ሊያመጡባችሁ ነዉ» የሚል እንደሚገኝበት ከስፋራዉ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት የአንድነት አመራር አባል «የደሴ፣ የጎንደር ሆነ የመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ፣ በዘጠና ሰባት ቅንጅት ያስቀመጣቸውን የሰላም የዲሞክራሲና የኢትዮጵያዊነት መርህዎች ደግፎ ነዉ ድምጹን ለቅንጅት ሰጥቶ የነበረዉ» በማለት፣ የአንድነት ፓርቲን እንደ ቅንጅት መክሰሳቸው ፣ ወያኔዎች፣ አላወቁትም እንጂ አንድነትን ነዉ እየጠቀሙ ያሉት» ብለዋል።
ሲያክሉ ፣ ቅንጅት የሚለዉ ስም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ለግለሰቦች ቢሰጠም፣ ያኔ የነበሩ አመራር አባላት በብዛት ባይኖሩም፣ የቅንጅት መንፈስ ግን መቼም ሊጠፋ እንደማይችል፣ አንድነትና ሌሎች በሚመሩትም ትግሎ እንደገና እየተንጸባረቀ እንዳለም ለማስረዳት ሞክረዋል። «ግለሰቦች ይሄዳሉ፣ ድርጅት ይመጣል ፣ ድርጅት ይሄዳል። የሕዝብ የሰላም የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄ ግን በምንም ተዓምር ለዘላለም ሊታፈን አይችልም። ገዢዉ ፓርቲ ከሕዝብ ተጻራሪ ሆኖ ከሚቆም የሕዝብን ጥያቄ የማዳመጥ ባህል፣ በአስቸኳይ ቢያዳብር ይሻለዋል» በማለት አስረድተዋል።
       Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment