አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በመላ ኢትዮጵያ የሚካሄድ የሦስት ወር ሕዝባዊ ንቅናቄ በማቀድ ወደ ተግባተር መግባቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ እቅድ መሰረትም የደቡብ ወሎ ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላት ሀገራዊ ጥሪውን በደስታ ከመቀበልም ባለፈ በቅድሚያ በደሴ ከተማ እንዲካሄድ ባቀረብነው ሀሳብ መሰረት ፓርቲያችን ተቀብሎ እድሉን ስለሰጠን ያለንን ደስታ እንገልፃለን፡፡
የደሴና አካባቢው ሕዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በሙስናና፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ገፈፋ ሰለባ የሆነ ህዝብ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በደሴ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ እንድናዘጋጅና ሕዝቡ አሉ የሚላቸውን ማሕበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ በነቂስ አደባባይ በመውጣት ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲያሰማ፤ ስርዓቱ ላይ ጫና እንዲያሳርፍ እንድናደርግ ኃላፊነት ከተሰጠን በኋላ ስኬታማ እንዲሆን ብርቱ ጥረት አድርገናል፡፡ በሂደቱም በደሴ ከተማና በወረዳዎች ያሉ አባሎቻችን ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ይህም ሆኖ የማዕከላዊና የዞኑ የፓርቲው አመራሮች ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ያደረጉት አስተዋፅኦና ትግል እጅግ እንዳኮራን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
የደሴው ሰላማዊ ሰልፍ በርካታ መሰናክሎችን አልፎ፣ ብዙ ሽዎችን አሳትፎ፣ የታለመለትን ዓላማ ከግቡ በማድረስ በስኬት በመጠናቀቁ በሕዝባችን ትልቅ ኩራት እንዲኖረን አድርጎናል፡፡ በጨዋነት ሰላማዊ ሰልፉ ላይ በመታደም ፍፁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ያሉበትን በርካታ ችግሮች ያሰማው የደሴና አካባቢው ሕዝብ የመንግስትን ሽብር መፍጠርም አውግዟል፤ የፍትህ እጦት ሰለባ መሆኑን አሰምቷል፡፡ ስለዚህ የደቡብ ወሎ ዞን ደሴ አንድነት ቅርንጫፍ ለሰላማዊ ሰልፉ መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሁሉ ከልብ እያመሰገነ ከምንም በላይ ለለታላቁ የደሴ ሕዝብ ያለውን ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል፡፡ እናመሰግናለን፡፡ ይሄ ሰላማዊ ሰልፍ የመጀመሪያው እንጅ የመጨረሻ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በቀጣይነትም ሁሉንም አይነት የሰላማዊ ትግል ስልቶችን በመጠቀም ሕዝቡን ለለውጥና ለነፃነቱ በአንድነት ዙሪያ ተሰባስቦ እንዲታገል ቀን ከሌት እንሰራለን፡፡
ነፃነታችን እስከሚረጋገጥ የሚሊዮኖች ድምፅ መሰማቱን ይቀጥላል!!!
No comments:
Post a Comment