July 30, 2013 02:25 am
“ፋሺስቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት እንዳይመስላችሁ፡፡ ሸፍታ ማለት ያለ አገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ መጥቶ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን፡፡” አቡነ ጴጥሮስ፡፡
ዛሬ ሐምሌ 22 ቀን ጀግናው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ በግፍ የተገደሉበት ቀን ነው፡፡ እኒህ ታላቅ አባት ለሰማዕትነት ያበቃቸው ዋናው ምክንያት በወቅቱ ለተጠየቁት ቀላል ለሚመስል ጥያቄ “ቃሌን አልክድም” ብለው በመቆማቸው ነበር፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ አገራችንን ወርሮ ሕዝቡን ባስጨነቀ ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ ከአርበኛው ጋር በመቆም የጣሊያንን ሠራዊት በድፍረት ሲቃወሙና አርበኛውንም ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ከጊዜያት በኋላ በፋሺስቶች ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ጣሊያኖች ራሳቸው በሰየሟቸው ዳኞች ፊት አቡኑን ለፍርድ በማቅረብ ከላይ ሲታይ በጣም ቀላል የሚመስል ጥያቄ ያቀርቡላቸዋል፡፡ የጥያቄው ዓላማ አቡኑን የጣሊያን ተገዢ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበረውን ሕዝባዊ ዓመጽ ለማብረድ ቢቻልም ደግሞ የብዙሃኑን ድጋፍ ለማግኘት የታሰበበት ነበር፡፡
ስለዚህም የግራዚያኒ ዳኞች አቡነ ጴጥሮስን ለፍርድ ባቀረቧቸው ጊዜ የጠየቋቸው “ሊቀጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ እንዲሁም ሌሎች የጣሊያንን የበላይነት ተቀብለዋል፤ እርስዎም እንዲሁ ተቀብለው ሌሎችም እንዲቀበሉ ቢያደርጉ ይሻላል፤ ብቻዎን ማመጽ ምንም አይሰራልዎትም፤ ይህንን ቢያደርጉ ምን ይመስልዎታል …” የሚል እንድምታ ነበረው፡፡ … አቡኑም “ከመሞት መሰንበት” በማለት የቀረበላቸውን ምክር አዘል አስተያየት መቀበል አላቃታቸውም፡፡ ሆኖም ለእምነታቸውና ለሕዝባቸው የገቡትን ቃል ከሚክዱ ሞትን እንደሚመርጡ በድፍረት ለዳኞቹ መለሱላቸው፤ እንዲህም አሉ፤
“አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ … ስለ አገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ … እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ” የሚል ነበር፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” አ.አ. 1980፤ ገጽ 157)
ረቡዕ ሐምሌ 22 ቀን 1928ዓም (July 29, 1936) አቡነ ጴጥሮስ ከፊት ለፊታቸው የተደገነውን የጣሊያንን መትረየስ ሳይፈሩ ከመገደላቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የሚከተለውን በመናገር የመጨረሻ ቃላቸውን ሰጡ፡፡
“ፋሺስቶች ያገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሏቸው እውነት እንዳይመስላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ አገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ መጥቶ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን፡፡” (ዝ.ከ.፤ ገጽ 157)
አቡነ ጴጥሮስ ይህንን ከተናገሩ በኋላ የፋሺስት የጦር መኮንኖችና ጄኔራሎች በተሰበሰቡበት አደባባይ የተሰማው የማያቋርጥ የጥይት እሩምታ ነበር፡፡ በእጃቸው ከያዙት መስቀል በቀር “መሣሪያ” በእጃቸው ያልነበራቸው የሃይማኖት አባት የተናገሩት ቃልና ያደረጉት ቆራጥ ውሳኔ የግራዚያኒን ጦር ወኔ ሰለበው፡፡ ለአቡኑ አንድ ጥይት አልበቃ ብሏቸው የመትረየስ እሩምታ ተኩስ በመልቀቅ በግፍ ረሸኗቸው፡፡
ፍርሃት ለአንድ ሰው መትረየስ ያስተኩሳል፤ ለአይጥ ታንክ ያሰልፋል፤ “ለቄጠማ ሰይፍ ያስመዝዛል”፤ የመናገርና የመጻፍ መብቴ ይከበር ለሚል የጸረ አሸባሪ ሕግ ያስወጣል፤ ሰላማዊውን ሰው “አሸባሪ” ያስብላል፡፡ ፍርሃት ያስደነግጣል፤ ያስፈራል፤ ያንቀጠቅጣል፤ ያሸብራል፡፡ ፈሪ የደፋሩ ድፍረት ያስደንቀዋል፤ ድፍረቱን ይመኛል፤ ከዚያ ለመውጣት ግን ራሱ ፍርሃት አንቆ ይይዘዋል፤ ፍርሃት ራሱ ፈሪውን ያስፈራዋል፤ “አልገዛም፤ ቃሌን አልለውጥም” የሚለው የደፋሩ ውሳኔና ቆራጥነት እጅግ ስለሚያሸብረው ራሱ ተሸብሮ ሽብር ይነዛል፤ ያስራል፤ ያሰቃያል፤ ይገድላል፡፡ አልበቃ ሲለው ሃውልት ያስፈርሳል፡፡ ግን አይረካም፤ ምክንያቱም ፍርሃት ሳይሆን ነጻነት ነው ርካታን የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ እንደፈራ ኖሮ እንደፈራ ይሞታል፤ ቃሉን የሚጠብቀው ግን በነጻነት ኖሮ በነጻነት ይሞታል፤ ሞቶም ግን በቃሉ ምክንያት ይታወሳል፡፡ የጴጥሮስ ቃል መቼም አይሞትም!!
(ይህ ጽሁፍ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ርዕስ አቶ መክብብ ማሞ ከጻፉት ጦማር ላይ በሰጡን ፈቃድ ለወቅቱ በሚመች መልኩ የቀረበ ነው፤ ለጸሐፊው ምስጋናችን ይድረሳቸው፤ ፎቶ wikimapia)
No comments:
Post a Comment