Tuesday, July 16, 2013

ሸንጎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጣይነት እያካሄደ ካለው ትግል ጎን ይቆማል


የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ  ዕሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ. ም በጎንደርና በደሴ ከተሞች የተካሄዱትን ትዕይንተ-ሕዝቦች ይደግፋል። ”የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!” በሚል መሪ ሃሳብ ሥር በአንድነት ፓርቲ አቀነባባሪነት የተጀመረው የሕዝብ እንቅስቃሴ፤ የተጋረጠበትን እንቅፋት ሁሉ አልፎ እነሆ በደሴና በጎንደር ከተሞች በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ የፍራቻ ድባብን ሰብሮ በይፋ ለመግልጥ መቻሉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ተግባር ነው።
ሃሳብን በሰላማዊ መንገድ መግለጥ የሰው ልጅ የተፈጥሮ መብት ነው። ይህ መብት ደግሞ ሰው በሰውነቱ ሊከበሩለት ከሚገቡት በርካታ መብቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በዓለም አቀፍ ሕግጋትም የተደነገገ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶቶች እጅግ ብዙ ናቸው። በኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት መሰቃየት፣ ከዚህም የተነሳ ስብዕናውን የሚያዋርዱ ተግባራት ውስጥ እንዲሰማራ መገደዱ፤ የሕግ የበላይነት ተደፍጥጦ የሕዝቡ በሆነ ባልሆነው ምክንያት መደብደብ፤ መታሰር፣ መሰቃየት፤ መገደልና ለስደት መዳረግ ዕለታዊ ተግባራት መሆናቸው፤ ሙስና በስፋት መንሰራፋቱ፤ የመፃፍ፤ የመናገር፤ በነፃነት የመደራጀት መብቱ ሊከበርለት አለመቻሉ፤ በሃይማኖቱ ውስጥ የአገዛዙ ጣልቃ ገብነትና አያደረሰበት ያለው ሰቆቃ፣ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት ቀየው ያላግባብ መፈናቀሉ፤ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ድምፁን ሊያሰማ አለመቻሉ፣ በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት በገዛ ሀገሩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ተዘዋውሮ ለመሥራትና ለመኖር አለመቻሉ፣ ሕዝብ የሚፈልገውን መንግሥት ሊመርጥ አለመቻሉ…ወዘተ በዚህ ሥር የሚጠቃለሉ ሰቆቃዎች ናቸው፡
ከላይ የተጠቀሱትን ሰቆቃዎች አስወግዶ መብቶችን ለማቀዳጀትና እንደሰው ለመኖር የፍራቻ ድባብን ወርውሮ በመጣል አጠንክሮ መታገል የግድ ነው። ተደጋግሞ እንደሚነገረው፤ ያለትግል ድል የለምና።
አዎ ያለው አገዛዝ በጭካኔ የተሞላ ነው። ያለው አገዛዝ ሕዝብ በፍርሃት ተሸብቦ ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ የማያደርገው ነገር የለም። አገዛዙ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ይረዱኛል የሚላቸውን እርምጃዎች ሁሉ ቢወስድም፤ ለመብቶቹ መከበር የሚታገልን ቆራጥ ሕዝብ ግን ለረጅም ጊዜ አንበርክኮ መግዛት አይችልም። ይህን ሃቅ ከራሳችን የትላንትና የትላንት በስቲያ ታሪካችን፤ እንዲሁም ዛሬ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚታየው እውነታ ትምህርት መውሰድ ይቻላል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ፤ አሁን ደግሞ (ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ. ም) በጎንደርና በደሴ ከተሞች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍራቻ ድባብን ሰብሮ በመውጣት መብቶቹን ለማስከበር ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ይህ በቁርጠኝነት እየተካሄደ ያለው አበረታች ትግል ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደጎን በመተው በአንድነትና፣ በቀጣይነት የሕዝቡን ትግል ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም ይህንን ታሪካዊ ግዳጅ ለመወጣት ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ  ድርጅቶች ተባብረው እንዲታገሉ አሁንም ጥሪውን ያቀርባል። ሸንጎው ከምሥረታው ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ሁሉ ዛሬም ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
የተባበረና የቆረጠን ሕዝብ ፍላጎት የሚገታ ምንም ኃይል ከቶውንም አይኖርም!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment