Thursday, January 29, 2015

“በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ሰው ነኝ” – የአርቲስት አስቴር በዳኔ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ

ሰሞኑን በማህበራዊ ድረገፆች እና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ላይ ስሟ በተደጋጋሚ የሚነሳው አርቲስት አስቴር በዳኔ የሀገራችንታዋቂአርቲስቶችን ባሳተፈውና ህወሃት የተመሰረተበትን 40 ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም በጠየቀቻቸው ጥያቄዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆና ሰንብታለች፡፡ አስቴር ለመከላከያ ሚኒስትር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለሆኑት ለጄኔራል ሳሞራ የኑስ ባቀረበቻቸው ጥያቄዎች የደነገጡ አንዳንድ የሙያ ጓደኞቿ ሳይቀሩማግለልና መድልዎለመፍጠርም ሲሞክሩ ስለመታየታቸው ይነገራል፡፡ የራሷን አቋም በግልፅና በድፍረት በዚያ መድረክ ላይ ካቀረበችው አስቴር በዳኔ ጋር አዲስ አበባ ላይ አጠር ያለ ቆይታ ከቁምነገር መጽሄት ጋር አድርጋለችለግንዛቤ እንዲረዳዎ -ሐበሻ እንደወረደ አስተናግዳዋለች::


ቁም ነገር፡- ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ስምሽ በስፋት እየተነሳ ነው፤ ምንድነው?
አስቴር፡- እንግዲህ ከሰሞኑ የደደቢት ጉዞ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በጉዞው ላይ ለየት ያሉ ጥያቄዎች
ጠይቃለች በሚል መሰለኝ የተለያየ ነገር እየተባለ ያለው፡፡

ቁም ነገር፡- አንቺስ የተለየ ጥያቄ ጠይቄያለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?
አስቴር፡- ያሉና ሁሉም የሚያውቀውን ህዝቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችን ነው የጠየቅሁት፤ አዲስ ነገር አለው ብዬ አላስብስም፡፡

ቁም ነገር፡- በመጀመሪያ እስኪ በጉዞው ላይ እንዴት እንድትሳተፊ እንደተጠራሽ ንገሪኝ?

አስቴር፡- እንደማንኛውም አርቲስት ነው የተጠራሁት፤ ጉዞው እንዳለ የነገረኝ አርቲስት መለሰ ወልዱ ነው፡፡ የህወሃትን 40 ዓመት ምክንያት በማድረግ አርቲስቶችን ወስደው ሊያስጎበኙ አስበዋል አንቺም ተጋብዘሻል ሲለኝ ደስ አለኝ፡፡ እንደ ፊልም ሰሪ ታሪካዊ ፊልም የመስራት ፍላጎት ልቤ ውስጥ ስላለኝ ለወደፊቱ የሚሰራ ነገር አይጠፋም ብዬ ሄድኩ፡፡ወደ እዛ ስንሄድ በቲቪ ብቻ የምታያቸው ባለስልጣኖች ከእኛ ጋር ጃኬት አድርገው መንገድ በመንገድ ሲሄዱ ሳይ ገረመኝ፡፡

ቁም ነገር፡-እነማን እነማን ነበሩ?

አስቴር፡- ዋና ዋናዎቹ ባለስልጣናት ነበሩ፤ እንግዲህ ሁሉንም ላላውቃቸው እችላለሁ፤ ግን የማውቀውን ያህል ጥሪ ካልከኝ፤ አቦይ ስብሃት፤አቶ በረከት ስምኦን፤አቶ አዲሱ ለገሰ፤ አቶ ስዩም መስፍን፤ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፤ አቶ አባዱላ፤ / ካሱ ኢላላ ነበሩ፡፡

ቁም ነገር፡- ለጄኔራል ሳሞራ ያነሳሽው ጥያቄ ምን ነበር?

አስቴር፡- ከስብሰባው በፊት በአውቶብስ ስንሄድ አብረን ካለን አርቲስቶች ጋር ያው የተለመደ ወሬ እናወራለን፡፡ ሁሉም የመሰለውን ነው የሚናገረው፡፡ እኔ ደግሞ የምናገረው የማምንበትን ነው፡፡ የማስበውን እግዚአብሔር ያውቃል፤ ኑሮዬ ካሜራ ፊት ለፊቱ እንደተደቀነበት ሰው መሆን አለበት ብዬ ነው የማስበው ፡፡ ማስመሰል አልወድም፡፡እና እዛ አውቶብስ ውስጥ ስናወራ የምናወራውን የሰማ አንድ የኢህዴግ አባል የሆነ አርቱስትለምን ይህንን እዚህ የምታወሩትን መድረክ ተዘጋጅቶ አትናገሩም?› አለ፡፡ እኔ ደስ ይለኛል አልኩና በማግስቱ ነው መሰለኝ የደርግ 604 ክፍለ ጦር የተደመሰሰበትን ቦታ አስጎብኝተውን ስንመለስ ስብሰባ ተጀመረ፡፡አዳራሹ በሙሉ ሰው ሞልቷል፤ፖሊሶች ጠባቂዎች አሉ፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም አሉ፡፡ እና ስብሰባው ተጀምሮ ጄኔራል ሳሞራ ገለፃ ሲያደርጉ አንዳንድ ማስታወሻዎችን እየፃፍኩ ነበር፡፡ ለምሳሌ እሳቸው ሲናገሩ ምን አሉለአስር ዓመታት ያህል ስንታገል ቆይተን ውጤት አልመጣ ሲል በአዲስ አስተሳሰብ ነው ለውጥ ያመጣነውብለው ነበር፡፡እንደውም ምንድነው ያሉትአሮጌ አስተሳሰብ አዲስ አስተሳሰብን ለመቀበል ይጎትታልብለው ነበር፡፡እንግዲህ እስከ እዛ ቀን ድረስ የተለያዩ የትግሉን ቦታዎች ተመልክተናል፡፡ እና ከእሳቸው ገለፃ በኋላ መድረኩ ለጥያቁ ክፍት ሲሆን አርቲስት አበበ ባልቻ መጀመሪያ ጠየቀ፤ ከዚያ ሳምሶን ማሞ ጥያቄ ጠየቀ/እናንተ እንደውም ባለፈው እትማችሁ ላይ አውጥታችሁታል/ ከዚያ ጥያቄ የሚጠይቅ ጠፋ፤ ቤቱ ፀጥ አለ፡፡ጠይቁ እየተባለ በየሻይ ቤቱና በየምግብ ቤቱ ባለስልጣናቱን በጀርባ ከማማት አሁን ነው መጠየቅ ያለብኝ ብዬ አሰብኩ፡፡ግን ፈራሁ፤ከዚያ ለአቶ በረከት በትንሽ ወረቀት ላይጥያቄ መጠየቅ ፈልጌ ነበር፤ ግን ፈራሁብዬ ላኩላቸው፡፡

ቁም ነገር፡- እንዴት ለእሳቸው ለይተሽ ይህንን ጥያቄ ጠየቅሽ?

አስቴር፡- ምን ሆነ መሰለህ? ከዚያን ቀን ቀደም ብሎ፤ እዚህ አዲስ አበባ ኤፍኤም ላይ ተንሻፎ ስለእኔ የተወራ ወሬ ነበር፤ በጉዞው ላይ በነበርኩበት ጊዜ ትንሽ አሞኝ ነበር፤ መንገዱም ሙቀቱም በሰዓቱ ምግብም ስለማንበላ አንዳንዴ ከጉብኝት በኋላ 10 ሰዓት ነበር ምሳ የምንበላው በዚህ በዚህ የተነሳ ታምሜ በየቦታው እቀመጥ ነበር፡፡ የሆነ ቦታ ተቀምጬ ሳለ ከጀርባዬ አንድ ሰው ትከሻዬን መታ መታ አድርጎውሃ ጠጪ የእኔ እህትሲለኝ፤እሺ የኔ ወንድምብዬ ቀና ስል አቶ በረከት ናቸው፡፡ እንዴት እንደደነገጥኩ ልነግርህ አልችልም፡፡በስመ አብ ሁሉ ብዬ አማትቤ ነበር፡፡ ከዛ በየመንገዱ ላይ ሌሎቹም ባለስልጣናት ሲያገኙን ‹.አስቴር እንዴት ነው? በርቺይሉኝ ነበር፡፡ ስብሰባ የተካሄደው ከዛ በኋላ ስለነበር ለአቶ በረከት ወረቀቷን ስልክ አንብበውየፈለግሽውን ጠይቂብለው ምልክት ሰጡኝ፡፡ በወቅቱ ለሴቶች ዕድል ይሰጥ ሲባል ሌላ ሰው ስላልነበረ ለእኔ ተሰጠኝ፡፡ የተቀመጥኩት ከበስተኋላግራ ወንበር ላይ ነበር፡፡ የመጠየቅ ዕድሉ ሲሰጠን ግን ማይክ ስለማይደርስ ወደፊት ነይ ተብዬ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጬ ነበር የጠየቅሁት፡፡ እንዴት እንደፈራሁ
ልነግርህ አልችልም፡፡ አንዳልኩህ ቤቱ በሙሉ በባለስልጣናት ተሞልቷል፡፡ግን እንደምንም ብዬ የፃፍኩትን ወረቀት እያየሁ ጠየቅሁ፡፡

ቁም ነገር፡-ምንድነው የጠየቅሽው?

አስቴር፡-ለምሳሌ ደርግን ለምን ጠላት ብለን እንጠራለን? ከደርግ ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፤ በአይዲዮሎጂ ልዩነት ነው እንጂ በአብዛኛው ንፁህ የኢትዮጵያ ልጆች አሉበት፤ አሁንም ጠላት ማለት ተገቢ ነው ወይ? የሚለው የመጀመሪያ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ለሀገር ለመስራት ብለው የሚወዳደሩ በመሆናቸው ተፎካካሪ ፓርቲ ለምን አይባሉም? ተቃዋሚ የሚባለው ግን ከስሙ ጀምሮ የግድ መቃወም ያለበት ይመስለዋል፤ ግንቦት ሲመጣ 24 ዓመት ይሆናችኋል፤ እና ከዚህስ በኋላ በአዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና ሌላ የፖለቲካ ፖርቲ በምርጫ አሸንፎ ሀገሪቱን ሲመራ ልናይ እንችላለን ወይ? የሚልም አለ፡፡መንግስት ለመቀየር ከዚህ በኋላ የግድ ጦርነት አያስፈልግም፤ ስለዴሞክራሲ ስታስቡ ልባችሁ ምን ይላችኋል? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ነው የጠየቅሁት፡፡

ቁም ነገር፡- ምላሹስ?

አስቴር፡- ጄኔራል ሳሞራ የተቻላቸውን ያህል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ደርግን በተመለከተ ጠላት ያልኩትን ይቅርታ አድርጊልኝ ነው ያሉት፡፡ ትክክል ነው የደርግ ወታደር ተገዶ የሚዋጋ ነው፤ ነገር ግን ምን አለ መሰለሽ በወታደራዊ ውጊያ ውስጥ መጀመሪያ ላይ ተዋጊን ሞት ሞት እንዲሸተው ማድረግ ያስፈልጋልሲሉ አርቲስቱ ሁሉ አጨበጨበ፤ ተቃዋሚ ፓርቲን በተመለከተ ተፎካካሪ በሚለው ቢተካ እኔ ተቃውሞ የለኝም ግን አንዳንድ ተቃዋሚ የሀገሩን ጥቅም ለውጪ ሁሉ አሳልፎ የሚሰጥ አለ ብለዋል፡፡

አስቴር፡- ከጥያቄሽ በኋላ በአርቲስቶች በኩል የነበረው ስሜት ምን ይመስላል?

ቁም ነገር፡- ብዙዎቹ ሸሹኝ፤ከእኔ ጎን መሆን ራሱ የፈሩ ነበሩ፤ ትተውኝም የሄዱ አሉ፡፡ የሚገርምህ ግን ባለስልጣናቱም ሆነ የእነሱ ደጋፊዎች እኛ እኮ የታገልነው ማንም ሰው የመሰለውን እንዲናገር ነው፤ ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅሽው፤
ነበር ያሉኝ፡፡

አስቴር፡- ከዋናዎቹ ጥያቄውን ከተጠየቁት ሰዎች ሳይመጣ ከሙያ ጓደኞችሽ መምጣቱ ምን ስሜት ፈጠረብሽ?

ቁም ነገር፡-አላውቅም፤ እንግዲህ ምናልባት እንደዚህ ብላ ትጠይቃለች ብለው አስበው ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ውስጤ አንድ ነገር ነግሮኛል፤ አንዳንዶቹ ደስተኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ፡፡ ምናልባትም ትንሽ ደፋር ሳልሆንባቸው አልቀረሁም/ ሳቅ/ አንድ አርቲስት እንደውም ማታ ራት ከበላን በኋላ አጠገቤ መጥቶ ምን አለኝ መሰለህ? አንቺ ምን ይሁን ነው የምትይው?› አለኝ፤ ምን ይሁን አልኩኝ? አልኩትኢህአዴግ ህዝብ እስከመረጠው ጊዜ ድረስ ዓመትስ ቢነግስ ምን አለበት?› አለኝ፡፡ እኔ ታዲያ ምን ቸገረኝ፤ እኔ እኮ ስለዲሞክራሲ ስለተነሳ ነው ጥያቄ የጠየቅሁት እንጂአንድ ሰው ተነስቶ እኔ ንጉስ ነኝቢለኝ ዓመት ንገስ ነው የምለውአልኩት፡፡ይሄ ግን የብዙዎቹን አስተሳሰብ የሚወክል አስተያየት እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ የተለየ ነገር ፈጥሬ የተናገርኩ ሰው አይደለሁም፡፡ የተሰማኝን ነው የተናገርኩት፡፡እውነት ነው ብዬ የያዝኩት ነገር ካለ በድፍረት እናገራለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- በየማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ስላንቺ እየተባሉ ያሉትን ነገሮች ተመልክተሻቸዋል?

አስቴር፡- እኔ ብዙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ አይደለሁም፡፡ በሳምንት አንድና ሁለት ጊዜ ባይ ነው፡፡ ለምሳሌ የእኔን ፎቶና የባለስልጣናትን ፎቶ አድርገው ስድብ በመፃፍ የሚያሰራጩ አሉ፤ ይሄ ትክክል አይደልም፤ የእኔ አላማ መሳደብ አይደለም፤ በመሳደብም ሆነ የሰውን ክብር በመንካት የሚመጣ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ከፋም ለማም ሀገሪቱን እያስተዳደሩ ያሉ ሰዎች ናቸው፤ ያለፉበትንም የትግል ሂደት ሄደን ተመልክተናል፡ የሚካድ አይደለም፡፡ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች አጠንክሮ ችግሮቹንም መንገር ነው የሚያስፈልገው፡ ፡እኔ በአሁኑ ወቅት ጊዜ የለኝም፤ ብዙ ስራ አለኝ፤ አራት መፅሐፍ ላሳትም ያዘጋጀኋቸው አሉ፤ አንድ ግጥም ሲዲ ጨርሻለሁ፤ የቤተሰብ ሀላፊ ነኝ፡፡ የልጆች እናት ነኝ፡፡ ፌስቡክ በሚሰጠው አፍራሽ አስተያየት ላይ ምንም ልል አልችልም፤ አልሞቀኝም አልበረደኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ ፊልም ሰርቼ ብታወቅ ነው የምመርጠው፡፡ የሚገርምህ ቤተመንግስት ሁሉ ተጠራች ብለው የሚያወሩ አሉ፡፡

ቁም ነገር፡- ጉዳዩ ከፖለቲካ ጋር መያያዙ አስጨንቆሻል?

አስቴር፡- ለምን ያስጨንቀኛል? የፖለቲካ ጥያቄ ስትጠይቅ ጉዳዩ ወደ ፖለቲካ እንደሚሄድ እገምታለሁ፡፡ግን እኔ የጠየቅሁት ጥያቄ ካየሁት ከሰማሁት፤ሰው ከሚያወራው ተነስቼ በመሆኑ ያን ያህል አነጋጋሪ መሆኑ አስገርሞኛል፡፡

ቁምነገር፡- አስቴር ፖለቲከኛ ናት?

አስቴር፡-አይደለሁም፤

ቁምነገር፡-ፖለቲካ ትወጃለሽ?

አስቴር፡- ማለት.. የሚያናድዱኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ በዚያ በኩል ያለውን ሁኔታ ለማወቅ የምቆፍር አይነት ሰው ነኝ፡፡ ግን የፖለቲካ ጋዜጣና መፅሔት የምከታተል ሰው አይደለሁም፡፡ እርግጥ ነው በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ሰው ነኝ ፡፡

ቁምነገር፡- አርቲስት ከፖለቲካ ነፃ መሆን ይችላል ብለሽ ታስቢያለሽ?


አስቴር፡- አርቲስት ፖለቲከኛ ሳይሆን መስታወት ነው፡፡ መስታወት ደግሞ ያለውን ነገር በግልፅ ነው የሚያሳየው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ቁም ነገር፡- በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለችው አስቴር ምን አይነት ሴት ናት?
አስቴር፡- አስቴር በጣም ቆንጆ፤ በንጉሱ ፊት ሞገስ ያገኘች፤ ለህዝቧ ምህረትን ያመጣች ብልህ ሴት ናት፡፡እናትም አባትም ሆኖ መርዶኪዮስ ነው ያሳደጋት፡፡መርዶኪዮስ ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ነበር የሚያስተዳድርው፡፡ ንጉሱ ሲያገባት አይሁዳዊ መሆኗን አያውቅም፡፡ መርዶኪዮስ ሐማ ለሚባለው የንጉሱ ባለሟል አልሰግድም በማለቱ እንዲገደል ይወሰናል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን መላ ዘሩ ሁሉ እንዲጠፋ ይፈረድበታል፡፡ ይህን ጊዜ መርዶኪዮስ አስቴርን በዚህ ጊዜ ህዝብሽን ማዳን አለብሽ ይላታል፡፡ንጉሱ ብዙ ሚስቶች ስላሉት የሚፈልጋትን ካላስጠራ በቀር እሱ ጋር መቅረብ አይቻልም፡፡ አስቴር ግን ህዝቡ ለሶስት ቀን ፆም ፀሎት ይያዝ አለች፤ ከሶስት ቀን በኋላ ንጉሱ ሳያስጠራት ቢገድለኝም ይግደለኝ ብላ ንጉሱ ፊት ሄዳ ቆመች፡፡ ንጉሱ ዘንጉን ከዘረጋላት አለፈች ማለት ነው፤ ዝም ካለ ግን ያው ትገደል ነበር፡፡ ግን አስቴር በንጉሱ ፊት ሞገስ አገኘች፡፡ ምንድነው የምትፈልጊው? ሲላት ስለህዝቧ ተናገረች ስለህዝቧ የተጻፈው የሞት ደብዳቤ ለጠላቶቿ ሆነ፤ህዝቧንም አዳነች ማለት ነው፡፡ በጣም ነው አስቴርን የምወዳት፤
ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ?


ቁም ነገር፡-ለሁሉም አስተያየት ለሰጡኝ ሰዎች ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ አድናቆታቸውን ለሰጡን ብቻ ሳይሆን ለተቹኝም ለሰደቡኝም አመሰግናለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰው ሁልጊዜ የሚናገረው በአዕምሮውና በአስተሳሰቡ በእውቀቱ ደረጃ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደእኔ ያስብ ለማለት አይቻልም፡፡የተነገረውን ነገር የምትቀበልበት ልብ ነው አንተን የሚገልፅህ፡፡ ቀና አስተሳሰብ እንዲኖረን ነው የምፈልገው፡፡አንድ የሚያደርገን ነገር ላይ ብናተኩር ነው ደስ የሚለኝ፡ በፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ እንደ ጠላት ባንተያይ እላለሁ፡፡ፖለቲከኛነትና እንጀራም ቢለያይ ጥሩ ነው፡ እኔ ለማንም ጥላቻ የለኝም፤ ማንንም አልቃወምም፡ ፡ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ እንፍጠራት ነው የምለው፡፡ እየተፈራራን የትም አንደርስም፡፡የመሪዎቻችንን ልብ በፍቅር መማረክ ይቻላል፤ፈሪ ህዝብ ለምንም አይጠቅምም ፡፡ መንግስትም ፈሪ ህዝብ ይዞ ልማቱን መቀጠል አይችልም፡፡ ከዚህ ፍርሃት እንደ ህዝብ ተላቀን በፍቅርና በሰላም ለሀገር ይጠቅማል የምንለውን አሳብ እየሰጠን እንድንኖር ነው የምምኘው፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/38553

No comments:

Post a Comment