Sunday, January 4, 2015

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ህብረት የአቋም መግለጫ


የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ና ህጋዊ የመብት ማስረከብ ትግል ከጀመረ እነሆ ሶስት አመት አስቆጠረ ለዚህ ሰላማዊ
የመብት ትግል መነሻ የሆነው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ሶስት ህጋዊ የመብት ጥያቄዎችን ለመንግስት በማቅረብ ምላሽ
እንዲሰጣቸው በወከላቸው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አማካኝነት ከመንግስት ጋር ውይይት ከጀመሩ ቦኋላ መንግስት
ከሙስሊሙ ህብረተ ሰብ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ከመስጠት ይልቅ የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ይዘው የቀረቡትን ህዝቡ መርጦ
የወከላቸው መሪዎቹን አስሮ ጥያቄዎቻቸውን በማዳፈን መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነበር።

ድርጅታችን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ህብረት በሙስሊሙ ህዝባችን ለኢትዮጵያ መንግስት
ያቀረባቸው ህጋዊ ና የመብት ጥያቄዎች መሆናቸውን ያምናል መንግስትም ተገቢ መልስ መስጠት እንዳለበት ና ያለ ምንም
ጥፋት እስከ ዛሬ ድረስ አስሮ የሚያጕላላቸውን ህዝበ ሙስሊሙ የወከላቸው መሪዎቹን መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በነጻ
መልቀቅ አለበት ብሎ ያምናል፡፡

ድርጅታችን ሙስሊሙ ህብረተ ሰብ ጥያቌዎቹን ለማስመለስ የተከተለው ሰላማዊ የትግል ስልቱን ይደግፋል በሰሜን አሜሪካ
የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችንም በማደራጀት የንዋይ ና የሞራል ድጋፍ ያደርጋል።

አለአግባብ የታሰሩት የህዝበ ሙስሊሙ መፍቲሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎች ነጻ የህሊና እስረኞች ናቸውና በነጻ ና በአስቸኳይ
እንዲለቀቁ ድርጅታችን አጥብቆ ይጠይቃል።

ድርጅታችን በግል ተነሳሽነት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ እስረኞች ጉዳያቸውን በአፍሪካ ሰብአዊ መብት ፍርድ ቤት
እንዲታይላቸው ያቀረቡትን ይደግፋል፡ ይሄንን የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ጥሰት ለማጋለጥ ና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው
ለማቅረብ በሙሉ ሀይሉ ይንቀሳቀሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሙስሊሙ ህዝባችን በነዚህ ባለፉት ሶስት አመታት ባደረጋቸው ሰላማዊ የመብት ትግል ላይ ሰላማዊያን
ዜጎች ገድለዋል፤ አስረዋል፤ደብድበዋል፤አንገላተዋል፤የእህቶቻችን ሂጃብ አስወልቆ አቃጥለዋል፤በቤት ለቤት ፍተሻ ሰበብ ክብረ
ንጽህናም አስደፍረዋል፤ንብረት አስዘርፈዋል፤ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ በየአስባቡ ከትምህርት ቤቶች ና ከስራ ገበታቸው
አስባርረዋል፤ገሚሱንም ለስደት ዳርገዋል በመሆኑም ለዚህ ሁሉ በደል ድርጅታችን መንግስት ተጠያቂ ነው ብሎ ያምናል።

መንግስት በሀይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም የሚለውን ህገ መንግስት አንቅጽ ጥሶ እጁን ጣልቃ በማስገባቱ ድርጅታችን
መንግስት ጣልቃ ያስገባውን እጁን ሙሉ በሙሉ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ይጠይቃል።

ድርጅታችን የኢትዮጵያ መንግስት ከሙስሊሙ ህዝባችን እርቅ ማድረግ ከፈለገ ሌላ ሶስተኛ አካል ሳያስፈልገው ሙስሊሙ
መርጦ ከወከላቸው ና በእስር ከሚገኙት መሪዎቹ ጋር በመነጋገር ሙስሊሙ ያነሳቸው የመብት ጥያቌዎቹን ሙሉ በሙሉ
አዎንታዊ መልስ በመስጠት ና በዚህ ምክንያት ያሰራቸውን መሪዎቹን ና ሌሎቹን ጨምሮ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት
አለበት ብሎ ያምናል።

የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ህገ መንግስት ጥሰቱ ሙስሊሙን ያሸማቀቀ ወይም አንገት ያስደፋ መስሎት ከሆነ ትልቅ የግንዛቤ
ችግር አለበት እንላለን እንዲያዉም በውጭ ና በሀገር ውስጥ የምንገኝ የ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከምን ግዜ በበለጠ ከራሳችን
አልፎ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ጋርሁሉ አንድ አድርጎናል በጋራ መታገልንም አስተምሮናል፡ ከሁሉም በላይ
ውስጣችንን አጥርተን ወደ ጌታችን አቅርቦናል ለዚህም ጌታችንን አላህን ክብር ና ምስጋና ይገባው እንላለን።

ትግላችን በአላህ ፈቃድ ና ሀይል እስከ ድል ደጃፍ ይቀጥላል!!! አላሁ አክበር!!!

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37752

No comments:

Post a Comment