Thursday, February 26, 2015

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ ዘገባ Feb 25.2015

2014 ዓም ለሰብዓዊ መብት ይዞታ እጅግ አስከፊ ዓመት እንደነበር ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ባወጣው ዘገባው አስታወቀ። በዘገባው መሠረት፣ በብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት፣ በኢትዮጵያም ጭምር የሰብዓዊ መብቱ ይዞታ ባለፉት ዓመታት ይበልጡን እየተበላሸ መሄዱ ነው የጎላው።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ካለፉት በርካታ ዓመታት ወዲህ ተስፋፍቶ ቢታይም፣ በተለይ የፊታችን ግንቦት የሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር የመናገር፣ እና የመሰብሰብ የመሳሰሉ መሠረታዊ ነፃነቶችን መገደብን በተመለከተ ጥሰቱ መባባሱን በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኙት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ተባባሪ ባልደረባ ሬይቸል ኒክልሰን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።


« ያለፈው አውሮጳዊ ዓመት 2014 በጋዜጠኞች በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ የእስራቱ ድርጊት በጣም የተስፋፋበት ዓመት ነበር። ስድስት ጦማርያን እና ሶስት ጋዜጠኞች ባለፈው ሚያዝያ መታሰራቸው፣ በኋላም በፀረ ሽብር ወንጀል መከሰሳቸው እና ለፍርድ መቅረባቸው ወይም፣ መንግሥት አካሄድኩት ካለው አንድ ጥናት በኋላ በበርካታ አሳታሚ ድርጅቶች እና ሕትመቶች ላይ የሽብር ተግባር አሲራችኃል በሚል ክስ መመሥረቱ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል፣ ይህን ተከትሎ የአሳታሚዎቹ ድርጅቶች እንዲዘጉ በመደረጉም ለብዙ ጋዜጠኞች ሸሽተው ሀገር ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል።

ተቃውሞ እንዳይወጡ የማከላከሉ ርምጃም ዓመቱን ሙሉ ቀጥሎዋል። እና ሀሳብን በነፃ የመግለጹ እና በፖለቲካውም ውስጥ በሙሉ በሙሉ የመሳተፉ ነፃነት ከምርጫው ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም እየጠበብ መምጣቱን ታዝበናል። »

በሀገሪቱ የዘፈቀደ እስራት፣ መጠን ያለፈ የኃይል ተግባር እና ሰዎች ካለ ፍርድ የተገደሉባቸው ጥሰቶች መታየታቸው የተዘረዘረ ሲሆን፣ ለነዚሁ ጥሰቶች የፌዴራል እና ያካባቢ ፀጥታ ኃይላት ተጠያቂ መሆናቸውን ነው ከብዙ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ የሚከታተሉት የአፍሪቃ ቀንድ ተባባሪ ባልደረባ ሬይቸል ኒክልሰን የኦሮሚያን አካባቢ በምሳሌነት በመጥቀስ ያመለከቱት።

« በኦሮሚያ አካባቢ ያለውን ሰፊ ጭቆናን እና አንዳንድ የመብት ጥሰትን በተመለከተ አምና ለብቻው አንድ ዘገባ አውጥተናል።ባለፈው ሚያዝያ እና ግንቦት ከአዲስ አበባና አካባቢዋ ጋር የተጣመረውን የልማት መሪ አቅድ በመቃወም በኦሮሚያ ፌደራል መስተዳድር ሰልፍ በብዛት በተካሄደበት ወቅት፣ ከፍተኛ ጥሰት ተፈጽሞዋል፣ ብሎም፣ ተቃውሞውን ለመበተን ሰዎች በብዛት ሲታሰሩ እና መጠነ ያለፈ የኃይል ተግባር ሲካሄድ ተመልክተናል። በነዚህ ጥሰቶች ላይ የፀጥታ ኃይላት ተሳታፊዎች ነበሩ። የጦር ኃይሉ እና ልዩ ኃያላትም መጠን ባለፈ የኃይል ርምጃ ተጠቅመዋል። ተቃውሞው ከቀዘቀዘም በኋላ እስካለፈው ሀምሌ ድረስ 350 እስከ 500 አባሎቹ እንደታሰሩበት ከኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ገልጾልናል። ስለዚህ እስራቱ ዓመቱን ሙሉ ቀጥሎዋል። »

እስረኞች የቁም ስቅል እንደሚደርስባቸው የገለጸው የአምነስቲ ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ወኪሎች በሌሎች ሀገራት በስደት የሚገኙ መንግሥት የሚፈልጋቸውን ስደተኞችን ካንዳንዶቹ ሀገራት በመተባበር በግዳጅ ወደ ትውልድ ሀገራቸው መመለሰቻውን በጥብቅ ነቅፎዋል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል 2011 ዓም ወዲህ በሀገሪቱ እንደልብ ተንቀሳቅሶ መረጃዎችን መሰብሰብ መከልከሉን በመግለጽ ድርጅቱ በውጭ ሀገር ካሉ ኢትዮጵያውያን ወይም በሀገር ውስጥ ካሉት ተባባሪዎቹ ላይ ጥገኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓለም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመንግሥታት እና ከታጣቂ ቡድኖች ከሚገጥማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመከላከል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን አላደረገም ሲል 160 ሀገራት የሰብዓዊ መብት ይዞታን የዳሰሰው ድርጅት በዘገባው ወቀሳ ሰንዝሮዋል።

አርያም ተክሌ
http://www.dw.de/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%9D%E1%8A%90%E1%88%B5%E1%89%B2-%E1%8A%A2%E1%8A%95%E1%89%B0%E1%88%AD%E1%8A%93%E1%88%BD%E1%8A%93%E1%88%8D-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%8A-%E1%8B%98%E1%8C%88%E1%89%A3/a-18278968

No comments:

Post a Comment