ሕዝብ የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት በሆነበት ሃገር ፍትህ ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ትቀመጣለች፡፡ እውነትም ምሰሶና ወጋግራ ሆና ፍትህን ዘወትር የመደገፍ እድሏን ትጎናጸፋለች፡፡ በኢትዮጵያ የፍትህና የእውነትን የክብር ቦታና ሚና አፈ-ሙዝ ወስዶታል፡፡ ፍትህና እውነት ደግሞ ትቢያ ላይ ተጥለዋል – ምንም እንኳ እንደወደቁ ባይኖሩም፡፡
በኢትዮጵያ ፍትህና እውነት ትቢያ ላይ ባይጣሉ ኖሮ ለዓመታት ይቅርና ለሰዓታት እንኳን በእስር ቤት ግርጌ መጣል ባላስፈለገንም ነበር፡፡ ፍትህና እውነት በኢትዮጵያ አድራሻ ቢኖራቸው ኖሮ ለዚህ ዓለም እንግዳ የሆኑት ልጆቼ ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን የአባታቸውን ፍቅር በግፍ ባልተነጠቁ ነበር፡፡ ፍትህና እውነት የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን ብትሆን ኖሮ ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን ባለቤቴ ከእኔ ጋር የመኖር ሰብዓዊ መብቷን ተገፋ በወጣትነት እድሜዋ የመበለትነት ህይወት የመግፋት እዳ ባልወደቀባት ነበር፡፡ ፍትህና እውነት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንኳን መንሳፈፍ ቢችሉ ኖሮ በሃሰት ዶሴ ከታሰርኩ በኋላም ለዓመታት በእስር ቤት ውስጥ ተጨማሪ የግፍ ፅዋ እንድንጎነጭ ግድ ባልሆነብኝም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እውነትና ፍትህ ከትቢያ የተሻለ ቦታ ቢኖራቸው ኖሮ ረጅም ርቀት አቆራርጠው ሊተይቁኝ የሚመጡ ጠያቂዎቼ የመጠየቅ መብታቸውን ለዓመታት ሳይሆን ለሰዓታት እንኳን ባልተነፈጉም ነበር፡፡
በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊቷ ኢትዮጵያ እኔና ቤተሰቤ ፍፁም ኢሰብዓዊ ከሆኑ ነገሮች ጋር ተላምደን፤ በሞትና በህይወት መካከል ያለው ልዩነት እስኪጠፋን ድረስ በአባቶቻችን፣ በራሳችንና በልጆቻችን ሃገር፤ በህዝባችን ፊት በማናለብኝነት ጥቂት አፄዎች ጢባጢቢ እንዲጫወቱብን ተበይኖብናል፡፡ በውል የማውቀውን የራሴን ጉዳይ በዋናነት ባነሳም የእኔና የቤተሰቦቼ ህይወት የእነ እስክንድር ነጋንና ሌሎች አንባቢ ፈፅሞ የማይዘነጋቸው ኢትዮጵያውያንና ቤተሰቦቻቸውም ፅዋ መሆኑን ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም፡፡ በየትም ቢሆን አንድ ዜጋ የግፍ ፅዋ እንዲጎነጭ ሲገደድ የሚጠጣው የኢ-ፍትሃዊነት ስቃይ ጥልቅ ነው፡፡ በተለይ ግን በሚወደው ህዝቡ ፊትና የእኔ ብሎ በሚኮራበት ሃገሩ እንደርሱ ደምና ስጋ የለበሱ ጥቂቶች ያሻቸውን ሲፈፅሙበት የግፉ ስቃይ ከመቼውም በላይ ይከፋል፡፡ ይህንን ከመሰለው የኢፍትሃዊነት ስቃይ ለአፍታም ቢሆን የሚያሳርፋቸው ግን አንድ ነገር አለ፡፡ አንባቢ የማይዘነጋቸው ወይዘሮ ሮዛ ፓርክስ መቀመጫቸውን ለቀው የኋላ ወንበር ላይ እንዲቀመጡ አሊያም ከአውቶብስ እንዲወርዱ ሲጠየቁ በእግራቸው መሄድን መምረጣቸው ብቻ ሳይሆን ለምርጫቸው የሰጡት አመክንዮ ጥልቅ ትርጉም አለው፡፡ ‹‹በእግርሽ ይሄንን ያህል ማይል መጓዝ ይሻላልን?›› ለሚለው ጥያቄ ‹‹እግሮቼ ይደክማሉ ነፍሴ ግን ታርፋለች›!›› ብለው ነበር፡፡
እኔም በምወዳት ሃገሬ በህዝቤ ፊት ከእነቤተሰቤ የግፍ ሰለባ ብሆንም ህሊናዬን የሚጎረብጠኝ ነገር ባለመኖሩ የእኔም ነፍስ እረፍት አላጣችም፡፡ የሌሎች በግፍ የታሰሩ ጓደኞቼም ህሊናቸውው ፍፁም እረፍት የተጎናፀፈ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ትልቁ የህሊና እዳ በሃሰት ካሰሩኝ በኋላም በግፍ ተግባራቸው የሚመፃደቁት አሳሪዎቼ እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል የተገደደ እኔን የሚመስል ዜጋ ሞትንም እንኳን ቢሆን በክብርና በደስታ ለመጋፈት ይዘጋጃል እንጂ ህሊናውን ሰላም በሚያሳጣ ድር ተጠልፎ አይወድቅም፡፡
ውድ አንባቢ በእኔ ጫማ ውስጥ ቢቆሙ ከዚህ የተለየ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በሃገርዎ፣ በህዝብዎ ከምንም በላይ በህልውናዎና በእጣዎ ላይ የግል አቋምዎን እንዳያራምዱ በሃሰት ዶሴ ተጠርቀው መቀመቅ ቢወርዱ ከዚህ የተለየ አቋም ሊኖርዎት ይችል ይሆን? በሚያምኑበት ጉዳይ ተሸብበው የሚነገርዎትን ብቻ እንዲፈፅሙ ቢነገርዎት ይስማማሉን? የመብቶቹ ባለቤት ላልሆነ ዜጋ ሰው መሆን ማለት ምን ትርጉም ይሰጣል? ይኸ ሁሉ አንሶ በእሾህ በታጠረ የፖለቲካ ሰርጥ ውስጥ በተቦዳደሰ እግርዎ እያነከሱ እንዳይንከላወሱ እንኳን ‹‹እግር በመቁረጥ›› ፈሊጥ የተካኑ ገዥዎች እግርዎን ቢቆርጡት ምን አይነት ስሜት ይፈጥርብዎታል? ጥቂት ዙፋን ላይ የተቀመጡ ባለጊዜዎች ምን ማሰብ እንዳለብዎ እንኳን ሳይቀር ሲወስኑልዎ እና ባጠቃላይ የርስዎ ህልውናና ተፈጥሮአዊ መብትዎችዎ በነሱ መዳፍ ስር ያሉ፤ ከፈለጉ ብቻ ቆንጥረው የሚሰትዎ ካላሻቸው የሚነፍጉት ሲሆን ምን አይነት ትርጉም ይሰጥዎት ይሆን?
አዎ ሀገር በጭቆና ቀንበር ስር ስትወድቅ ድጋፍ ብቻ እንጅ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት ስርየት የሌለው ሃጢያት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ለገዥዎች በታጠረው አጥር ውስጥ በድፍረት ለማቋረጥ ሲሞክሩ ‹‹ቀዩን መስመር አልፈዋል›› በሚል አይቀጡ ቅጣት ይቀጣሉ፡፡ በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ግፎች እንደነውር ወይም ግፍ ሳይሆን አገዛዙን ለማስቀጠል የሚያስፈልጉ፤ ከትልቅ አዕምሮ የተቀዱ ልዩ የፖለቲካ ቀመሮች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
በአገዛዙና የግፍ ሰለባ በሆነ እኔን በመሰለ ዜጋ መካከል የሚደረገው ትግል ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ አገዛዙ እስረኛውን ለማምከን ሲተጋ እኔን የሚመስል እስረኛ በግርግም ውስጥም ሆኖ ደግሞ ህይወት በከንቱ እንዳይባክን ይታገላል፡፡ ለዚህም ነው አገዛዙ እስር ቤት ውስጥ እንኳን ከሌሎች አያሌ እስረኞች በተለየ ግፍ የሚፈፀምብኝ፡፡ እኔም እኔን የመስበር ተልኳቸው ገብቶኛልና ግብግቡን ለማሸነፍ ፍፁም በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኘ ለሀገሬ ይበጃል ያልኩትን ሀሳብ በሁለት መፅሐፎች ለማድረስ ሞክሬያለሁ፡፡ ከነጉድለቱም ቢሆን ‹‹ያልተሄደበት መንገድ›› ከብዙ ፈተና በኋላ ለአንባቢ ሲደርስ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡ አሁን ደግሞ የፈጣሪ ፀጋ በዝቶልኝ ታምር በሚመስል መልኩ ‹‹የሀገር ፍቅር ዕዳ›› የተሰኘውን ሁለተኛ መፅሐፌ ለአንባቢ በመድረሱ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በሀገር ፍቅር ዕዳ የግል ህይወቴን ጭምር ጨልፌ ለማካፈል ሞክሬያለሁ፡፡ የእኔ የዝቅታ ህይወት የሚሊዮኖችን ኢትዮጵያውያንን ህይወት እንደሚወክል በማመን፡፡ ምንም እንኳ የሚያስኮፍስ ያለፈ ታሪክ ባይኖረኝም ታሪክ የሚያኩራራው ብቻ አይደለምና ከተመላለስኩባቸው ውሃ አልባ ሸለቆዎች አንባቢዎች የሚቃርሟቸው ጥቂት ቁምነገሮች አይጠፉም፡፡ የህይወት ከፍታ ከሩቅ ስለሚታይ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ዝቅታን ለማሳየት ግን ጉልበት ይጠይቃልና ለማሳየት በመሞከሬም እንዲሁ ደስታ ይሰማኛል፡፡
በሀገር ፍቅር ዕዳ የእኔን ከፍና ዝቅ ህይወት ብቻ ሳይሆን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለኝን እይታ ያለምንም ማድበስበስ ለአንባቢ ለማካፈል ሞክሬያለሁ፡፡ ያልተሄደበት መንገድ ላይ በሩቁ የሰማኋቸውን አስተያየቶች በዚህኛው ለማረም ተፍገምግሜያለሁ፡፡ አንባቢ እንደሚረዳው መፅሐፌም እንደኔ ነፃነት የተነፈገ በመሆኑ እንደሌሎች መፅሐፍቶች ከመታተሙ በፊት በተለያዩ ሰዎች ተገምግሞ እንደገና አርሜው የመውጣት እድሉን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ግድፈቶች ካሉ አንዱ መንስኤ ይሄው ነው፡፡
ህይወቴ አንባቢን የሚስያተምሩ፣ ነገሮችን ከተለየ ማዕዘን ለማየት የሚረዱ፤ ከተቻለም ፈገግ የሚያሰኙ ነገሮች እንዲገኙበት ትልቅ ምኞት አለኝ፡፡ በህላዌ ዘመናችን ስንመላለስ የህይወትን ትርጉም ከሚሰጡ ምግባሮች መካከል አንዱን ለመከወን ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ምን ያህል ተሳክቶልኝ ይሆን? ይህንን ለናንተ ልተወው፡፡
ለዘመናት ልባችን በናፍቆት ለዛለላት የዴሞክራሲና የነፃነት ጀምበር የምትወጣበት ታላቅ የንጋ ቀን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀረበ መሆኑን በፍፁም በማመን፡፡
አንዷለም አራጌ (ቃሊቲ፤ የህሊና እስረኛ)
http://satenaw.com/amharic/archives/9171