Saturday, July 18, 2015

ማሰር፣ ማሽበር፣ ማወክ የማይሰለቸው ግፈኛ አገዛዝ


ገዢው ፓርቲ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ማሻሻያዎች አድርጎ ለብሄራዊ መግባባት ራሱን እንዲያዘጋጅ ከተለያዩ ማእዘናት ጥሪ ቀርቦለታል። የሕሊና እስረኞችን እንዲፈታ በተደጋጋሚ ተጠይቋል። ሆኖም አገዛዙ እንኳን ሊሰማ እንደዉም በጣም እየባሰበት መጥቷል። ዜጎችን በማሰርና በማሸበር የሚረካው አገዛዝ ዛሬም በወገኖቻችን ላይ የሰቆቃ በትሩን እየያሳረፈ ነው።

ወደ ብሄራዊ መግባባት እንዲመጣ በስፋት ጥሪ እየቀረበለት ቢሆንም አገዛዙ እንደ አበደ ዉሻ፣ እንደዉም ጭካኔዉንና ግፈኝነቱ በጣም ጨምሯል። ዜጎችን ማሰር፣ መግደል፣ ማሸበሩን አጧጡፎታል። ብዙዎች ያለ ምንም ማስርጃ ታስረው በወህኒ እየማቀቁ ነው። ከነዝኢኡህ መካከል አንዱ የሁለት ልጆች አባትና የአንዲት መልካም ኢትዮጵያዊት ባለቤት ስንታየሁ ቸኮል ነው።

ስንታየው ድብቅ ነገር አይወድም። ንግግሩ ቀጥተኛ ነው። ሐሳቡን የመሰለዉን ከመናገር ወደ ኋላ የማይል ነው። ሞትና መታሰርን በጭራሽ የማይፈራ ፣ አገሩን የሚወድ ጀግና ኢትዮጵያዊ ። እርሱ በመታፈኑ፣ በዜጎች ስቃይ የሚደሰቱ እንደመሆናቸው፣ አሳሪዎቹ ሊደሰቱ ይችሉ ይሆናል። በሺዎች የምንቆጠር የትግል አጋሮቹ ደግሞ ልናዝን እንችላለን። ከስንታየው ጋር ወዳጅ ነኝ። ስለ ስንታየሁ ብዙ አወቃለሁ። አንድ ነገር አስረግጬ የምናገረው ነገር ቢኖር፣ ስንታየው ለአገርና ለህዝብ ሲል መታሰርን እንደ ትልቅ ጸጋና ክብር የሚቆጠር፣ ወኔና ጀግንነት የተሞላ ኢትዮዮጵያ ካፈራቻቸው ብርቅዬ ታጋዮች መካከል አንዱ መሆኑን ነው።

ስንታየሁ ወያኔ ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ አምጽ ቀስቅሰሃል በሚል ነው ያሰሩት። ምንም አይነት የሕግ ጁደት ሳይደረግ፣ ምስክሮች ሳይሰሙ ነው የስድስት ወራት እስራት በጥቂት ቀናት ዉስጥ የተፈረደበት። ቤተሰብ እንዳይጠይቀው፣ የአዲስ አበባ ንዋሪ ሆኖ ሸዋ ሮቢት ወስደው አሰሩት። (የጎንደርና የጎጃምምም እስረኞችን አዲስ አበባ አምጥተው እንደሚያስሩት) ።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስንታየው ቸኮሎች፣ አሏት። «ታጋይ ቢሞት ትግል አይሞትም» ነበር የሚባለው። ታጋይ ቢታሰርም ትግል አይታሰርም። ብርቱካን ሚደቅሳን አሰሩ፤ እነ አንዱዋለም፣ እነ እስክንደር ተነሱ ። እነ አንዱዋለም ሲታሰሩ እነ ሃብታሙ ፣ ዞን ዘጠኞች ተነሱ። እነ ሃብታሙ ሲታሰሩ ደግሞ እነ መሳይ ምትኩ እነ ስንታየሁ ተነሱ። የሕዝብ መሰረታዊ የለዉጥ ጥያቄ በኃይል ማፈን በጭራሽ አይቻልም።

ለተቀረነው እንዲህ እላለሁ። ብናዝን ማዘናችን ተገቢ ነው። ሆኖም የነስንታየው መታሰር፣ እኛ አዝነን እንድንቀመጥ ሳይሆን ለነጻነት የሚደረገዉን ትግል የበለጠ አጧጡፈን እንድንቀጥል ሊገፋፋን ይገባል። የበለጠ አንድነታችን እያጠናከርን፣ ገዢው ፓርቲ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከሁላችንም መስማት መጀመር አለበት። በየቀበሌያችን ፣ ትምህርት ቤታችን፣ ሰፈራችን፣ እድሮቻችን … እየተደራጀን እንቅስቃሴዎችን እናድርግ። እንመካከር። እንነጋገር። ሀዘናችንን ወደ ተግባር እንለዉጥ።
የሕሊና እሥረኞች በሙሉ እስኪፈቱ ትግሉ ይቀጥላል !!!!!
http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/18213#more-18213

No comments:

Post a Comment