Tuesday, May 21, 2013


የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ በቅዱስ ሲኖዶሱ ታገዱ


cover

- እግዱ ከሙስና ጋር የተገናኘ ነው
- ‹‹ሙስናው በአንድ ሀገረ ስብከት ብቻ አይደለም›› አገልጋዮች
የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ጽዮን አባ ሕሩይ ወንድይፍራው ከስራ ታገዱ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በበላይነት እያስተዳደረ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በዋና ጸሀፊው አቡነ ህዝቅኤል ፊርማና ማህተም ለምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጻፈው ደብዳቤ ዋና ስራ አስኪያጁ መልአከ ጽዮን አባ ሕሩይ ወንድይፍራውን ከስራ ማገዱን አስታውቋል፡፡
በ7/9/2005 ከአቡኑ ቢሮ የወጣው ደብዳቤ የምዕራብ ሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ በመተላለፍ በራሳቸው ፈቃድ የሰራተኞች ቅጥርን በይፋ ሳያወጡ ቅጥር መፈጸማቸውን፣የደመወዝ ጭማሪ ማድረጋቸውንና ዕድገትና ዝውውር መፈጸማቸውን ያትታል፡፡ ስራ አስኪያጁ ይህንን ተግባራቸውን እንዲያቆሙ በቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም በማን አለብኝነት በተግባራቸው በመቀጠላቸው እግዱ ተፈጻሚ እንዲሆን ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል፡፡
‹‹ልማት እየተዳከመ፣እሰተዳደር እየተበደለ፣ባለ ጉዳይ እየተጉላላ ዝም ብሎ መመልከቱ ተገቢ ባለመሆኑ ከስራ ታግደዋል›› የተባሉትን ስራ አስኪያጁን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም በቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሙስና መንሰራፋቱንና በዘመድ አዝማድ በየጊዜው ቅጥር እንደሚፈጸም ያነጋገርናቸው ሰዎች ይጠቅሳሉ፡፡
በስራ አስኪያጁ ላይ የተወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ ተገቢ ስለ መሆኑ ፍኖተ ነጻነት ያነጋገረቻቸው የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ‹‹ችግሩ ግን ያለው በምዕራብ ብቻ ሳይሆን በደቡብ፣በሰሜንና በምስራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከቶች በመሆኑ ሲኖዶሱ ምዕራብን በነካበት እጁ ሌሎቹንም እንዲመለከት ጠይቀዋል፡፡
ለስራ አስኪያጁ ደብዳቤውን በፊርማ በማጽደቅ የላኩት አቡነ ህዝቅኤል ደብዳቤውን መላካቸውን ቢያምኑም ሙስናውን ፈጸሙ የተባሉትን ስራ አስኪያጅ በህግ ለመጠየቅ ሲኖዶሱ ስለማቀዱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ‹‹ያንን የማድረግ  ኃላፊነት የሌሎች ነው፡፡››ብለዋል፡፡
     Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment