Saturday, April 27, 2013

የኤርትራ አየር መንገድ ወደ አውሮፓ እንዳይበር ታገደ

28 April 2013 ተጻፈ በ       



የኤርትራ አየር መንገድ ከበረራ ደኅንነት ሥጋት ጋር በተያያዘ ወደ ማንኛውም የአውሮፓ አገር እንዳይበር የአውሮፓ ኅብረት አገደ፡፡

የአውሮፓ ኅብረት በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የበረራ ደኅንነት ሥርዓትን በአግባቡ አላሟሉም የሚላቸውን አየር መንገዶች ወደ አውሮፓ የአየር ክልል እንዳይበሩ የሚከላከል ሲሆን፣ የአየር መንገዶቹን ስም ዝርዝር ያሳውቃል፡፡ የስም ዝርዝሩም የአውሮፓ ኅብረት የበረራ ደኅንነት ጥቁር መዝገብ በመባል ይታወቃል፡፡

ኅብረቱ በቅርቡ ያወጣው የበረራ ደኅንነት ጥቁር መዝገብ የኤርትራ ብሔራዊ አየር መንገድ የሆነው የኤርትራ አየር መንገድ “ኤር ኦፕሬተር ሠርቲፊኬት” ቁጥር “AOC” No 004 የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መለያ ቁጥር “ERT” የተመዘገበውና ናስኤር ኤርትራ የተባለው አየር መንገድ “AOC” No 005 የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መለያ ቁጥር “ኤንኤኤስ” ወደ ማንኛውም የአውሮፓ አገር እንይይበሩ መታገዳቸውን ይጠቁማል፡፡ መዝገቡ በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ፈቃድ የተሰጠው ሌላ ማንኛውም አየር መንገድ ወደ አውሮፓ መብረር እንደማይችል ያሳያል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1991 የተመሠረተው የኤርትራ አየር መንገድ በ2003 ዓ.ም. በተከራየው አንድ ቦይንግ 767 አውሮፕላን ሥራ የጀመረ ሲሆን ወደ ሮም፣ ካይሮ፣ ጅዳ፣ ዱባይ፣ ፍራንክፈርት፣ ካራቺ፣ ኬፕታውንና ካርቱም ሲበር ቆይቷል፡፡ አየር መንገዱ ከአስመራ ወደ አሰብና ምፅዋ ይበራል፡፡

የኤርትራ አየር መንገድ አንድ ኤርባስ 319-200፣ ሁለት ኤርባስ 320-200 እና አንድ ቦይንግ 767-200E አውሮፕላኖች ተከራይቶ ይሠራል፡፡

በበረራ ደኅንነት ሥጋት ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት በጥቁር መዝገቡ ውስጥ ካሰፈራቸው አየር መንገዶች 100 ያህሉ የአፍሪካ አየር መንገዶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል 42 ያህሉ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከአንጎላ 13፣ ከጎረቤት አገር ሱዳን 12 አየር መንገዶች በአውሮፓ ኅብረት ጥቁር መዝገብ ውስጥ ሰፍረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በጥቁር መዝገቡ ውስጥ የገባ አንድም አየር መንገድ የለም፡፡

 Posted By,Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment