“ማፈናቀሉ የሚካሄደው በመንግሥት ትዕዛዝ ነው፤ ወደ ክስ እናመራለን”
“በቤኒሻንጉል የህወሃት ታጋዮች ሰፋፊ እርሻ አላቸው”
April 23, 2013 04:10 am
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ2000 ሺህ በላይ ትግሬዎች ባለይዞታ መሆናቸውንና ማንም ሳይነካቸው በሰላም እንደሚኖሩ፣ በቶጎ ወረዳ ከስልሳ በላይ ነባር የህወሃት ታጋዮች ሰፋፊ የእርሻ መሬት ወስደው በባለሃብት ደረጃ እንደሚገኙ የመኢአድ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አስታወቁ። ከሌሎች ብሔረሰቦች ተለይቶ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመበት ያለውን የአማራ ብሔረሰብ በድጋሚ ለማስወጣት መታቀዱንም በመረጃ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
በቦታው በመገኘት አስፈላጊውን መረጃ እንደሰበሰቡ ለአሜሪካ ሬዲዮ የገለጹት የመኢአድ ስራ አስፈጻሚ በክልሉ ከሚኖሩት የተለያዩ ብሔረሰቦች ተለይቶ የአማራ ብሔረሰብ እንዲፈናቀልና እንዲሰቃይ የሚደረገው በማዕከላዊ መንግስት ትዕዛዝ እንደሆነም አመልክተዋል።
መኢአድ ያሰራጨውን መግለጫ ተከትሎ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሃይሉ ሻወል፣ ድርጊቱ በበታች የቀበሌና ወረዳ አመራር አካላት ተፈጽሟል መባሉን ተቃውመዋል።”ሰዎቹ እንዲወጡ ሲታዘዝ ያ ሁሉ ወታደር ከየት መጣ?” በማለት የጠየቁት አቶ ሃይሉ ሻወል፣ በርካታ የወያኔ ሰዎች በቦታው እያሉ አማራው ተለይቶ እንዲፈናቀል የበታች ባለስልጣናት በራሳቸው ውሳኔ ይህን ሊያደርጉ እንደማይችሉ ተናግረዋል። በማያያዝም በርካታ ተጨባጭ ማስረጃ ስለተሰባሰበ ጉዳዩን ወደ ዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ባላቸው የተለያየ መስመር ፍርድ ቤቱ የሚቀበላቸውን ማስረጃዎች በማጣራት አስፈላጊ መረጃዎችን እንዳሰባሰቡ የገለጹት ኢንጂነር ሃይሉ ሻወል፣ “የሰውና የቪዲዮ መረጃ አለን። የመንግስት ወታደሮች ህዝብ ሲደበድቡ፣ መኪና ተገልብጦ ሰዎች ሜዳ ላይ ሲሰቃዩ፣ በግድ ሲፈናቀሉ … የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አሰባስበናል። ወደ ክስ እናመራለን” በማለት መናገራቸውን የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ (ቪኦኤ) አመልክቷል።
የመኢአድ የስራ አስፈጻሚ አባል በበኩላቸው የመንግስት ባለስልጣኖችና ካድሬዎች በኩምሩክ ሕዝብ በመሰብሰብ ማነጋገራቸውን ይጠቅሳሉ። እሳቸው እንዳሉት ህዝቡ “ለምን በዘራችን ሳቢያ ይህ ሁሉ ስቃይ ይደርስንባል?” በማለት ጠይቆ ነበር። የሰበሰቧቸው ባለስልጣናት “ክልሉ የናንተ አይደለም ውጡ” ሲሉ እንደመለሱላቸው የጠቀሱት የስራ አስፈጻሚ አባል፣ በሌላ በኩል የተፈጸመው ህገ ወጥ የዘር ማጥፋት ተግባር የመንግስት እጅ ያለበት እንዳይመስል ለክልሉ ነዋሪዎች “አማራን አታስጠጉ፣ ከአማራ ጋር አትብሉ፣ ከአማራ ጋር አትጠጡ፣ ቤት አታከራዩ፣ ይህን ማድረግ ወንጀል ነው” በማለት መንገራቸውንና በዚሁ መነሻ ህዝቡ በክልሉ ያሉ አማሮች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጥያቄ እንዲያቀርቡ መመሪያ መሰጠቱን አመልክተዋል። ይህ የሚሆነውም ጥያቄው ከህዝብ የመጣ እንደሆነ ለማሳየት እንደሆነም አስታውቀዋል።
በዘር፣ በሐይማኖትና በአመለካከት አንድን ማህበረሰብ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት መሞከር፣ ማሸማቀቅ፣ ሴቶችን መድፈር በዘር ማጥፋት እንደሚያስጠይቅ ያመለከቱት የመኢአድ የስራ አስፈጻሚ አባል፣ “ይህ ሁሉ ተፈጽሟል” በማለት ድርጅታቸው በዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት ከድምዳሜ መድረሱን ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ክልል ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ስህተት መሰራቱን ማመናቸውና ድርጊቱን የፈጸሙት ኪራይ ሰብሳቢ የወረዳና የበታች አመራሮች እንደሆኑ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። በተመሳሳይ ለስራ ፈረንሳይ አገር በነበሩበት ወቅት ለጀርመን ሬዲዮ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ፕሬዚዳንቱ ተፈጸመ ስላሉት ስህተት “የማውቀው ነገር የለም። አልሰማሁም። እኔ የማውቀው ደን ጨፍጭፈው በሃይል መሬት የያዙ መፈናቀላቸውን ነው” ብለዋል። ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማርያም ቀደም ባሉት ሳምንታት ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉትን ዜጎች አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ወንጀሉ የዘር ማጥፋት ስለሆነ ክስ መመስረት እንደሚቻል አመልክተው ነበር።
መኢአድ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ አረካ ቀደም ሲል የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች አያይዞ ለክስ እንደሚጠቀምበት አመልክቷል። በጥያቄና መልሱ ወቅት ከነበሩት ጋዜጠኞች መካከል “የተፈናቀሉት ተመልሰዋል። ለምን አትተውትም” በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ጋዜጠኞች እንደነበሩ የቪኦኤው የአዲስ አበባ ዘጋቢ ጠቆም አድርጎ አልፏል።
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment