Thursday, July 24, 2014

የምርጫ ነገር

july 24th,2014

በመቀሌ አንዳንድ ጓደኞቼን «የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትፈልጋላቹህ ? ለምን ገብታቹህ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ አታደርጉም ? » ስላቸው «ዝም ብለን ለምን እንለፋልን። እንደተለመደው ይዘርፉታል። የህዝብ ድምጽ አይከበርም» አሉኝ። በጣም ገረመኝ ። ምክንያቱም ድሮስ አንባገነን ስርዓቶች ፍትሓዊ ምርጫ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ እንዴ? አንባገነን መንግስታት በሚመሩት ሃገር ነጻ፣ ፍትሓዊ እና ተአማኒ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠር አለበት። አለበለዚያ አንባገነኖች ፍትሓዊ ምርጫ እንዲያካህዱ ባህሪያቸው አይፈቅድላቸውም።

ባለፉት 23 አመታት ፍትሓዊ ምርጫ ቢደረግ ኖሮ፣ ኢህአዴግ እስካሁን ስልጣን ላይ አይቆይም ነበር። ስለዚህ ዜጎች በሃቀኛ ተቀዋሚ ፓርቲዎች ስር ተደራጅተው፣ ስርዓቱ ካላስገደዱት መጪው ምርጫም እንደለመደው አጭበርብሮ ስልጣን ላይ ለመቆየት እንደሚፈልግ አሁን በሃቀኛ ተቀዋሚዎች ላይ እየደረሰ ካለው አፈና መገንዘብ ይቻላል።
ሃቀኛ ተቀዋሚ እያልኩ ያለሁት በስመ ተቀዋሚ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚፈልጉ የይስሙላ ተቀዋሚዎች ስላሉ ነው። እነዚህ በህዝብ እና በሃገር እየቀለዱ ያሉ ግለሰቦች እና ተቃዋሚ ነን የሚሉ፣ ማንም ሰው የማይከተላቸው እና የእለት ጉርሳቸው ኢህአዴግ የሚቆርጥላቸው ናቸው።
ስለዚህ ዜጎች ላለፉት 23 ዓመታት ከጫንቃቸው አልወርድም ብሎ በምርጫ ስም በየ 5 ዓመቱ በህዝብ እና በሀገር ላይ እየቀለደ ያለ ስርዓት የከፋፍለህ ግዛ ስልቱ በማክሸፍ፣ ሁሉም ዜጋ ፤አገሪትዋን ከጥፋት ለመታደግ የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጽሃን ዜጎች በእስር ቤት እየማቀቁ ነው። «ነገስ ማን ይታሰር ይሆን ?» እያልን ሁሌ የሰቀቀን ሕይወት ከመምራት ሁላችን፣ እንደ አብርሃ ደስታ፣ ከፍርሃት ቆፈን በመውጣት፣ ለመብታችን መቆም መቻል አለብን። ከአንባገነኖች ፍትሓዊ ምርጫ ከመጠበቅ ከዝንብ ማር መጠበቅ ይቀላል። ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
ሃፍተይ ገብረሩፋኤል ( መቀሌ )
http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/15298


No comments:

Post a Comment