Wednesday, July 9, 2014

አንበሳውን በጅቦች ተከቦ አየሁት (ነቢዩ ሲራክ)

july.9.2014
ኢቲቪ የአንዳርጋቸው ንግግር ነው ብሎ ያቀረበው ፊልም አስቂኝ ነው። እንደነ ቢቢሲ በኮርፖሬሽን ደረጃ ለመዋቀር በቃሁ የሚለው ድርጅት በሴኩርቲ ( በድብቅ )ካሜራ የተቀረጸ የደበዘዘና የተቆራረጠ ፊልም ሲያቀርብ ማፈር ነበረበት።
አንዳርጋቸው ከተያዘ 2 ሳምንታት አለፉ። ዛሬ በድብቅ ካሜራ ተቀርጾ የተላለፈው ፊልም በእለቱ ኢትዮጰያ ሲገባ የተቀረጸ ነው – አለማቀፍ ግፊት ቢበዛብን እናሳየዋለን ብለው ቀርጸው ያስቀመጡት ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን አንዳርጋቸው እያንዳንዷን ቀን በድብደባ እያሳለፈ ነው። ኢቲቪ ልብ ካለው አንዳርጋቸውን ላይቭ(Live) ያሳየን።
አንበሳው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውል አንድም ነገር አልሰጣቸውም። “እኔ ስራየን ጨርሼ ደክሞኛል፣ እረፍት እፈለግ ነበር” ነው ያለው፤ ይህንን ደግሞ ዶ/ር ብርሃኑ ና ንቅናቄው አስቀድመው ተናግረውታል- አንዳርጋቸው ስራውን በጊዜ አጠናቆና ሃላፊነቱን ለወጣት አመራሮች ሰጥቶ እሱ መጠነኛ የዲፕሎማሲ ስራ እየሰራ ነበር።
ህወሃቶች በደንፎ “የትግራይን ህዝብ ትጠላለህ?” ብለው ጠየቁት። “ለማንም ህዝብ ጥላቻ የለኝም” ብሎ መለሰላቸው። አንዳርጋቸው የትግራይን ህዝብ ከጉጅሌው እንለየው የሚል ጽኑ አቋም ነበረው፣ያንን ነው የደገመው።
የታዩትን ፎቶግራፎች ድሮም አውቃቸዋለሁ፤ ከላፕቶፑ የተወሰዱ ናቸው። በእዚህ እድሜው የአውሮፓ ህይወቱን ትቶ በዛ አይነት ህይወት ለመኖር መፍቀዱ የሚደነቅ ነው። የእኔንም ኮምፒዩተር በቫየረስ በከሉት እንጅ እነዚህና ሌሎች ፎቶዎችም ነበሩኝ።
ፈገግታና ደግነት ደግሞ ባህሪው ነው። ጠላቶቹን ሳይቀር በፈገግታው ይገላቸዋል።
ከሁለት ሳምንት ድብደባ በሁዋላ ለፕሮፓጋንዳ የሚሆን ነገር አለማግኘታቸው ሃረር ውስጥ በጅቦች ተከቦ አልበላም ብሎ ሲታገል የነበረውን አንበሳ አስታወሰኝ።
ኮራሁብህ ወንድሜ አንዲ።
ትናንትን ያስታወሱኝ ትናንትና ዛሬ
ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ …

ግንቦት 8/1981 በደርግ የመጨረሻ አመታት መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ ከሸፈ። የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ የተባሉት ሃገሪቱ በከፍተኛ ወጭ ያስተማረቻቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች የተወሰኑት ሲሰው የቀሩት በቁጥጥር ስር ዋሉ። ዛሬ ላይ ሆኘ በጎልማሳ እድሜየ ከጋዜጠኛ ወንድሜ ጋር ስኖር እኔም እጋራቸው የነበሩ መረጃዊችን እና ያችን ቀን ሳስታውሳት ልዩ ስሜት ይሰማኛል ። ያ ስሜት ዛሬ አቶ አንዳርጋቸውን በኢቲቪ ጎስቁለው ሳያቸው በአይነ ህሊናየ የተከበሩት ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይን አስታወስኩ: (
ሜጀር ጄኔራል ፋንታ አፈር መስለውና ገርጥተውና ፊታቸው ክችም ብሎ በቁጥጥር ስር ውለው ለመርማሪዎች በሰጡት ቃል ጦርነቱን ለማስቆም ብቸኛው አማራጭ አስተዳደሩን መቀየር ውጭ ሌላ መንገድ የለውም ብለው ኩዴታውን እንዳቀነባበሩ በድፍረት ተናገሩ ! ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ በሃገሪቱ ከፍተኛ የሚባሉትን ስልጣኖች የጨበጡ ፣ ኑሯቸው የተደላደለላቸው ቢሆንም ለኢትዮጵያ መጻኢ ሰላም ሲባል መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ መነሳሳታቸውን ሳይደብቁ ታሪካው ምላሽ ነበር !
ሐምሌ 13 ቀን 1981 ዓም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ በደርግ ሳንባ የሚተነፍሱት ራዲዮና ቴሌቪዥኑ “… የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያቀናበሩት ከሀዲው ጄኔራል ፋንታ በላይ ጠባቂያቸውን በካራቴ መትተው ለማምለጥ ሲሞክሩ በሌሎች ዘቦች ተገደሉ” ብሎ የታላቁን ጀኔራል ሞት አረዳን: (
የደከሙ የተጎሳቆሉ አቶ አንዳርጋቸውን ጸጋን ንግግር ማምሻውን ከኢቲቪ ብሰማ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይን አስታወሰኝ ! ትናንት ጀኔራል ፋንታ የሞቱላት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬው ልጆቿን እየበላ ነው: ( ይህ ሂደት የት ላይና መቸ እንደሚቆም ያሳስበኛል ኢትዮጵያን አምላክ ይታረቃት … ብየ ጎኔን አሳረፍኩ
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/32266

No comments:

Post a Comment