Saturday, September 13, 2014

ማን ነው በአሸባሪነት መጠየቅ ያለበት ?

በወያኔ መንደር ሽብርተኝነት ለየት ያለ መልክ ነው ያለው የወያኔ የሽብርተኝነት መስፈርትም ሆነ ትርጓሜ ብዙ ሃገሮች፤ አንባገነን የተባሉት ሳይቀሩ ስለሽብርተኝነት ካላቸው ግንዛቤም ሆነ ከአለም አቀፉ መመዘኛዎች የተለየ ነው። የሽብርተኝነት ተግባር እየተተረጎመ ያለው በወያኔ ባልሥልጣናት የመሸበር መንፈስና ሰለራሳቸው ሥልጣን ብቻ በማሰብ ከጭንቀት በመነጨ የፍርሃት ስሜት ላይ የተመሰረተ ነው:: ባለሥልጣናቱን ጭንቅት ወስጥ የሚጥል፣ የሚያስደነብር፣ የሚያስቀይም፣ የሚያስቆጣ ወይም የሚያሰፈራራና እንቅልፍ አጥተው እንዲያድሩ የሚያደርግ ተግባራትን የፈጸመ ሁሉ በሽብርተኛነት ይፈረጃል:: ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀይ መስመር አስምረውና አዋቅረውት የሄዱትን የወያኔን አጥር የሚነቀንቅ ብቻ ሳይሆን ጠጋ የሚልም ሁሉ በአሸባሪነተ ሊፈረጅ፣ ሊታሰርና ሊከሰስ እንዲሁም ሊፈረድበት እንደሚችል እየታየ ነው:: ለአገዛዝ ሥርዓቱ የሥልጣን ዘመን መራዘም ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉዋቸውን አካላትና ግልሰቦች ሁሉ አሸባሪ አያሉ መክሰስ የተለመደ ሆኗል። ብዕራቸውን አንስተው በመንግሥት ላይ የሰሉ ትችቶችን በመጻፍ ተቃውሟቸውን የገለጹ፣ የሃይማኖትና የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን በመወከል የመብት ጥያቄዎችን አንስተው የተሟገቱ የሕዝብ ወኪሎች፣ በወያኔ በባለሥልጣናት የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ሙስናዎችን፣ አገርና ሕዝብን ያዋረዱ ተግባራትን ያጋለጡና ባደባባይ ሥርዓቱን የሞገቱ ጋዜጠኞች፣ የማህብራዊ ድረ-ገጽ ገተሳታፊዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጭምር የሽብርተኝነት ካባ እያከናነቡ ማጎርና መወንጀል የሥርዓቱ ዋና ስልት ሆኗል። ይህም ወያኔ አለም በሚሸበርበት ጉዳይ ሳይሆን ራሱ በፍርሃት በፈጠረው የሽብር ዓለም ወሰጥ መሆኑን ያሳያል::

   ዳዊት ደምመላሽ

No comments:

Post a Comment