Friday, December 6, 2013

ኔልሰን ማንዴላ እና ኢትዮጵያ!!

December 6, 2013
የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በ95 አመታቸው ከዚህ አለም ሲለዩ፤ የተለያዩ አገሮች እንደየራሳቸው ግንኙነት የራሳቸውን ታሪክ ሲያወሩ ነበር። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ሃዘናቸውን ሲገልጹ ከማንዴላ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመግለጽ ነበር። እኔ በምኖርበት አትላንታ ከተማ ዜናው ሲቀርብ፤ ኔልሰን ማንዴላ አትላንታ በመጡበት ወቅት፣ ከነአንድርው ያንግ ጋር ሆነው የማርቲን ሉተር ኪንግ ማዕከልን ስለመጎብኘታቸው ነበር – ዋናው ዜና። ሁሉም አገር ስለማንዴላ የየራሱ ትዝታ አለው። ኢትዮጵያውያንም ስለኔልሰን ማንዴላ የራሳችን ታሪክ እና ትዝታ አለን። እናም ማንዴላ የዛሬ 51 አመት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ስለነበረው ጉዳይ በማውጋት ታሪካችንን እንጀምራለን።
Nelson Mandela, the revered statesman who emerged from prison after 27 years
በዳዊት ከበደ ወየሳ
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ በ1962 ዓ.ም አራተኛው የፓን አፍሪካ ስብሰባ በኢትዮጵያ እንዲደረግ ጃንሆይን ፍቃድ ጠየቁ። ጃንሆይ በጉዳዩ ተስማሙና በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም የአፍሪካ ታዋቂ የነፃነት ታጋዮች ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ከእነዚህም መሃከል ሚስተር ኦሊቨር ታምቦ፣ ሚስተር ሮበርት ሙጋቤ፣ ሚስተር ኬኔት ካውንዳ እና ሚስተር ኔልሰን ማንዴላ ይገኙበታል። (በኋላ ላይ እነዚህ ወጣት ታጋዮች የየአገራቸው ፕሬዘዳንት ሆነዋል) ይህ ጉዞ በተለይ ለኔልሰን ማንዴላ በህይወታቸው ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጡት ነው።
Nelson Mandela and Col. Tadesse in Addis Ababa, Ethiopia
የኔልሰን ማንዴላ አሰልጣኝ ከነበሩት መካከል፣ ኮሎኔል ታደሰ አንዱ ነበሩ። ይህ ፎቶ ማንዴላ እና ኮ/ል ታደሰ (በሗላ ጄነራል) ለመታሰቢያ የተነሱት ነው
የኔልሰን ማንዴላን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ያሰናዱት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ። በወቅቱ በአፓርታይድ የዘረኝነት ቀንበር ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ ጥቁር ዜጎችዋ ያለፈቃድ አገሪቱን ለቀው እንዳይወጡ የሚያዝ ህግ አውጥታ ነበር። ይህ ህግ ለኔልሰን ማንዴላ ጉዞ አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጠረ። በመሆኑም አቶ ከተማ ይፍሩ ለኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልፅ ፓስ ፖርት ካዘጋጁላቸው በኋላ ነበር፤ በፌብሩዋሪ 1962 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፤ ወቅት ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።
በወቅቱ ለኔልሰን ማንዴላ የተዘጋጀው ፓስፖርት ላይ ማንዴላ እንደጋዜጠኛ ሆነው፤ ስማቸው ዴቪድ ሞሳማይ ተብሎ ነበር የተጻፈው። ስሙን የተጠቀሙት ደቡብ አፍሪካ እያሉ አብሯቸው ከነበረው ጓደኛቸው ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ስለነበረው ጉዞ እናውጋ። ኔልሰን ማንዴላ “Long Walk To Freedom” በሚለው መፅሃፋቸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አየር መንገድ ድረስ መጥተው እንዴት እንደተቀበሏቸው ገልፀዋል። እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ ኔልሰን ማንዴላ…
ለንደን የነበሩትን ጓደኞቼን በወዳጅነት ስሜት ተሰናብቼ ወደ አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ ተጓዝኩ። እስካሁን ባለው ህይወቴ ለማላውቀው ወታደራዊ ስልጠና ነው የምሄደው። የስድስት ወር ወታደራዊ ስልጠና ለማድረግ በያዝኩት ፕሮግራም መሰረት ነው ወደ ኢትዮጵያ የምጓዘው። አዲስ አበባ ስደርስ መጀመሪያ ተቀብለው ያነጋገሩኝ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከተማ ይፍሩ ነበሩ። ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። ከዚያም “ኮልፌ” ወደሚባለው አንድ የከተማው ክፍል ወሰዱኝ።
የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ የሚሰለጥነው እዚህ ኮልፌ የሚባለው ሰፈር ነው። የባታሊዮኑ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው ከዚህ ነው። አኔ ወታደራዊ የሳይንስ ጥበብ እንድማር የተመደብኩበትም ስፍራ እዚህ ነው። እስካሁን ባለኝ ልምድ ጀማሪ ቦክሰኛ ከመሆን ውጭ ስለጦር ሜዳ ፍልሚያ የረባ እውቀትም የለኝም። አሰልጣኜ መቶ አለቃ ወንድሙ በፍቃዱ ይባላል። በጣልያን ወረራ ግዜ የደፈጣ ተዋጊ የነበሩ ልምድ ያላቸው ወታደር ናቸው።
በአዲስ አበባ መውሰድ የጀመርነው የስልጠና ፕሮግራም ጥብቅ ነው። ከጠዋቱ 2፡00 ሰአት እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ ስልጠና ላይ እንቆያለን። ከዚያ የምሳ ሰዓት ነው። ከዚያ ከሰዓት ከ8፡00 እስከ 10፡00 ስልጠናው ይቀጥላል። ከ10፡00 ሰዓት በሁዋላ እስከምሽቱ ድረስ ስለ ወታደራዊ ሳይንስ የንድፈ ሃሳብ ገለጻ ይደረግልናል። ይህንን ስልጠና የሚያደርጉልን ኮሎኔል፤ የፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ናቸው። በንጉሱ ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲከሽፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
በስልጠናው የአውቶማቲክ መሳሪዎች እና የሽጉጥ አጠቃቀምን ተማርኩ።
መጀመሪያ ኮልፌ ከዚያም ከኮልፌ 50 ማይልስ የምትርቅ ቦታ ከወታደሮቹና ከንጉሱ የክብር ዘበኛ አባላት ጋር ሄጄ የኢላማ ተኩስ ተለማመድኩ። የሞርታር ተኩስና እንዲሁም የቦንንብ አሰራሮችን፤ ፈንጂዎችን የማክሸፍ ዘዴንም ተማርኩ። አሁን እያደር ወታደር እየሆንኩ ስሄድ ይታወቀኛል። እንደ ወታደር ማሰብ ለመድኩኝ። ወታደር መሆን እንደ ፖለቲከኛ ከማሰብ የሚለይበት የራሱ መንገድ አለው።
እዚህ ቦታ ላይ በጣም የወደድኩት ጠዋት ተነስተን የምናደርገው የማለዳ ጉዞ ነው። ጠመንጃ፣ ጥይትና ጥቂት ውሃ እንይዛለን። እናም በተሰጠህ ጊዜ ውስጥ ያንን ርቀት ተጉዘህ የታዘዝከውን ፈፅመህ መድረስ አለብህ። በዚህ ወታደራዊ ጉዞ የአገሪቱን ገጠራዊ ክፍሎች ለማየት እድሉን አገኘሁ። የመሬቱ አቀማመጥ በጣም ቆንጆ ነው። ጥቅጥቅ ያለ ደንና ከፍተኛ ቦታዎችን አየሁ። ገጠሩ በጣም ሁዋላ ቀር ነው። ሰዎች በእንጨት መቆፈሪያ ነው የሚያርሱት። ምግባቸውም ትንሽና በቀላሉ የሚዘጋጅ ነው። እቤት የሚጠመቅ ቢራ ወይም ጠላ አላቸው፤ ኑሯቸው እዚህ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ መከረኞች ጋር ተመሳሳይ ነው። መቼም ደሃ ሰዎች የትም ቢኖሩ ኑሯቸው አንድ አይነት ነው፤ ብዙም አይለያዩም።
በስልጠናዬ ወቅት ኮሎኔል ታደሰ ብዙ ጉዳዮችን እያነሱ ያስተዋውቁኛል። ስለ ደፈጣ ውጊያ፤ ሃይል እንዴት ማዋቀር እንደሚቻል አንድን ጦር እንዴት ማዘዝና መምራት እንደሚቻል፤ በጦር ውስጥ ወታደራዊ ስነ ስርአትን ለማስፈን ምን ማድረግ እንደሚገባ ያስተምሩኛል።
አንድ ምሽት እራት ላይ ለደቡብ አፍሪካ ትግል ምን አይነት ጦር እንደሚያስፈልገንና የሰራዊቱ ባህሪ ምን መሆን እንዳለበት አጫወቱኝ። “ይኸውልህ ማንዴላ… አንተ የምትመሰርተው ነፃ አውጪ ሃይል እንጂ መደበኛ ጦር አይደለም። የናንተን ጦር ሰዎች የምትቀርፅበት ስልት ከመደበኛው ጦር አሰራር የተለየ ነው። አንተ መመስረት ያለብህ ነፃ አውጪ ጦር ነው። በትግል ላይ ስትገባም የምትመራቸው ተከታዮችህ ፍፁም እርግጠኝነት እንዲሰማቸውና ሁሉም ሃሳብህን እንዲከታተሉ ማድረግ መቻል አለብህ። ይህ በመደበኛው ጦርም ውስጥ ያለ ነው። ከስራ በሁዋላ በእረፍት ሰዓትህ ማድረግ የሚገባህ ግን ከመደበኛው ደንብ ውጪ ይለያል። አንተና የመጨረሻው ተራ ተዋጊ እኩል መሆናችሁን የሚያሳይ አቀራረብ ሊኖርህ ይገባል። የሚበሉትን ትበላለህ፤ የሚጠጡትን ትጠጣለህ። ምግብህን ወደ ግል ክፍልህ መውሰድ የለብህም። እራስህን ገለል አታድርግ፤ እዚያው አብረሃቸው ሁን።” አሉኝ። የኮሎኔልን ሃሳብ ተረድቻለሁ። ሃሳቦቹ የሚደነቁና መልዕክት ያዘሉ ናቸው። እንደነዚህ ያሉ ቁም ነገሮችን በየፕሮግራሙ መሃል ይነግሩኝ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለስድስት ወር ስልጠና ነው። ስምንት ሳምንት እንደሆነኝ ግን ከድርጅቴ ‘የአፍሪካ ኮንግረስ’ አንድ የቴሌ ግራም መልዕክት ደረሰኝ። ባስቸኳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንድመጣ የሚጠይቅ ነው። የዚያን ጊዜ የነፃነት ትግሉ መፋፋም ጀምሯል። እናም የግንባሩ አዘዥ እዚያው ቦታው ላይ መገኘት ስላለበት ነው የጠሩኝ። ኮሎኔል ታደሰ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካርቱም የምሄድበትን መንገድ ቶሎ አዘጋጁልኝ። ስንሰነባበት አንድ ሽጉጥና ሁለት መቶ ጥይት ስጦታ አበረከቱልኝ። ስለ ስልጠናውም ሆነ ሰጡኝ ትምህርት ትልቅ አክብሮት እንዳለኝ ገለጽኩና ጉዞዬን ጀመርኩ። መሳሪያ ተሸክሞ ረዥም መንገድ መጓዝን ብለማመድም የተሰጠኝ መሳሪያ ከባድ ነው። ሁለት መቶ ጥይት ጀርባ ላይ መታጠቅ ህጻን ልጅ በጀርባ እንደማዘል ነው የሆነብኝ።
ኦገስት 5 ቀን፣ 1962 ላይ… ኔልሰን ማንዴላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ኤርፖርት ሲደርሱ ጥብቅ ፍተሻ ተደረገባቸው። ከጦር መሳሪያው በተጨማሪ በኪሳቸውም ውስጥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሆናቸውን የሚገልጽና የአቶ ከተማ ይፍሩ ፊርማ ያለበት ፓስፖርት ተገኘባቸው። በኢትዮጵያ መቆየታቸውን የሚገልጽ የጃንሆይ ማስታወሻና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ከተማ ይፍሩ አነስተኛ ፎቶ ነበር። እነዚህን ጨምሮ 173 መረጃዎች በሪቮንያ የአፓርታይድ ችሎት ላይ ቀረበባቸው – 1963።
እነዚህና ሌሎች መረጃዎች በሪቮንያ ፍርድ ቤት ቀርቦ በኔልሰን ማንዴላ ላይ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው፤ በዚሁ አመት በ1963 ሮቢን ደሴት ላይ ወደሚገኘው ወህኒ ተወረወሩ።
Nelson Mandela with Mengistu Haile Mariam
ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በሗላ መጀመሪያ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በወቅቱ ፕ/ት መንግስቱ ሀይለማርያም አቀባበል ሲያድርጉላቸው
ከብዙ ውጣ ውረድና የ27 አመታት ትግል በኋላ ማንዴላ ከእስር ተፈቱ። እናም መጀመሪያ ከጎበኟቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። በፓስፖርታቸው ላይ ያሉት የመጀመሪያ ቪዛዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። መጀመሪያ ከጎበኟቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆነች። በኋላ ላይ በመጽሃፋቸው ላይ ሲጽፉ፤ “ኢትዮጵያ በኔ ውስጥ ልዩ ስፍራ አላት። በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ ያደረኳቸው ጉብኝቶች ቢደመሩ እንኳን፤ በኢትዮጵያ ከነበረኝ ቆይታ አይበልጡም።” በማለት ለኢትዮጵያ ያላቸውን ልዩ ስሜት ገልጸዋል። (በነገርዎ ላይ የኔልሰን ማንዴላን የህይወት ታሪክ የሚገልጽ፤ በኢትዮጵያ ያሳለፉትንም ወታደራዊ ስልጠና ህይወት የሚያሳይ ትልቅ ፊልም ተሰርቷል)
ኔልሰን ማንዴላ ከ እስር ቤት ከወጡ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በወቅቱ እነ ጄነራል ታደሰ ብሩ በህይወት አልነበሩም። ጊዜውም ተለውጧል። ቆየት ብሎ ኔልሰን ማንዴላ በህይወት ካገኟቸው ሰዎች መካከል አቶ ከተማ ይፍሩ አንዱ ነበሩ።
ከሰላሳ አመት በፊት አብረው የተነሱት ፎቶ ማንዴላን ለእስር እንዳላበቃቸው፤ አሁን ግን በነፃነት እንደገና ተገናኝተው የመታሰቢያ ፎቶ ለመነሳት በቁ። (አቶ ከተማ ይፍሩም ከጥቂት አመታት በፊት አልፈዋል)
ከመሰናበታችን በፊት… በአንድ ነገር እንሰነባበት። የኔልሰን ማንዴላ የልደት ቀን ሲመጣ፤ ተማሪዎችን ጨምሮ ህዝቡ በሙሉ ልደታቸውን ያከብራል። ለኔልሰን ማንዴላ ትልቁም ትንሹም “ማዲባ ሃላላ፣ እንወድሃለን አባባ” እያሉ ይዘምሩላቸዋል።
Madiba, Halala
Happy birthday to you!
Happy birthday to you!
Happy birthday dear Tata!
We love you Tata
We love you Tata
Nelson Mandela. Ha hona
Ya tshwanang le wena (there is no like you)
Yeep yeep!
Hooray!
እኛም በዚሁ ስንሰናበት፤ አንድ ነገር ለማለት ወደድን። አሁን የውሸት ወይም ድራማዊ ለቅሶ ሳይሆን፤ የእውነት ሃዘን የምናይበት ጊዜ ይሆናል።
ነፍስ ይማርልን!
 Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment