Thursday, December 24, 2015

ግፍ ሲፈጸም ዝምታን ከመረጥን እንደ አገር እንጠፋለን -ሃብታሙ አያሌው | ከቂሊንጦ እሥር ቤት

ለነጻነታቸው በሚያደርጉት ትግል፣ ኢትዮጵያ እንደ እናት ሆና የረዳቻቸዉ ፣ እንደ ጋና፣ ታንዛኒያና ሴኔጋል ያሉ የአፍሪካ አገሮች እንኩዋን ሳይቀሩ የትናየት በደረሱበት ዘመን፣ እንደ ደርግ ዘመን አሁንም በኢትዮጵያ፣ ረሃብና ችጋር የሚገድለን አልበቃ ብሎ፣ ኢትዮጵያዉያን በኢትዮጵያዉያን እጅ እየተገደሉ ነው። 

በቅርቡ በጎንደር እና በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎቸ እንዳየነው፣ በዜጎች ላይ የደረሰው ግድያ፣ ድብደባና ግፍ እጅግ በጣም ልቤን እንዳደማው መግለጽ እወዳለሁ። ለሞቶት ነፍስ ይማር፣ ለቤተሰቦቻቸዉም መጽናናቱን ያብዛላቸው እላለሁ።

በወገኖቻችን ላይ የደረሰን ጭካኔ አጥብቄ እያወገዝኩ ፣ የአገዛዙ ታጣቂዎች ተቃዉሞ ከሚሰማባቸው ቦታዎች በአስቸኩዋይ እንዲወጡ እጠይቃለህ። መንግስት ገዳዮችን፣ ትእዛዝ የሰጡትን ለፍርድ እንዲያቀርብና ጉዳት ለደረሰባቸው አስፈላጊውን ካሳ እንዲሰጥ እጠይቃለሁ። ገዢዎች የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄ በማናናቅ፣ በሚቆጣጠሩት ሜዲያ በሕዝብ ላይ የሚያሰሙት ዛቻ፣ ማስፈራራት ፣ ስድብ አቁመው፣ ለሕዝብ መሰረታዊ የመብት፣ የነጻነት የፍትህና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እጠይቃለሁ።

እኔን ጨመሮ በርካታ ዜጎች በሰላም ሐሳባችንን በመግለጻችን ሽብርተኞች ተብለን፣ ፍትህ ተነፍገን በግፍ ታስረናል። ነጻ ጋዜጦች ተዘግተዋል። በሌሎች አገሮች የእንስሳት መብቶች ሲከበሩ፣ በኛ አገር ግን ለሰብእና ክብር አይሰጥም። ዜጎች በአገራቸው ፈርተዉና ተሸማቀው ነው የሚኖሩት። ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ስደትን መርጠዋል። በልማት ስም ጥቂቶችን ለመጥቀም፣ ገበሬዎች ከእርሻቸው ይፈናቀላሉ። “ከዚህ ብሄረሰብ ናችሁ፣ የናንተ መሬት አይደለም” ተብለው ብዙዎች የዘር ማጽዳት ወንጀል ይፈጸምባቸዋል። በጎንደር ለምለም የአገራችን መሬት፣ ሕዝብ ፓርላማው ሳያውቀው ሊሰጥ እንደሆነ እየሰማን ነው። አገር በ 11% አድጋለች እየተባለ፣ አሥር ሚሊዮኖች ለረሃብ ተጋልጠዋል። ይሄ ሁሉ መቆምና መስተካከል አለበት። “ኢሕአዴግ ልብ ይበል ፤ 
የጥፋት እጆቹን ይሰብሰብ ፣ ሕዝብን ያክብር፣መሰረታዊ የፖለቲካ ሪፎርም ያድርግ፣ ለብሄራዊ መግባባት ራሱን ያዘጋጅ” እላለሁ።


ነጻነትን ለተጠሙ፣ ፍትህን ለተራቡ ኢትዮጵያዊያን መልእክት አለኝ። ነጻነት፣ ፍትህ ከሌሎች በስጦታ የሚሰጠን አይደለም። ነጻነትና ፍትህ እኛው ራሳችን ታግለን የምናገኘው ነው። በመሆኑም የአገሪቱዋ ሕገ መንግስት እና አለም አቀፍ ሕጎች በሚፈቅዱት መሰረት፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምጻችንን እንድናሰማና ትግሉን እንድንቀላቀል ጥሪ አቀርባለሁ። ግፍ ሲፈጸም ዝምታን ከመረጥን እንደ አገር እንጠፋለን። የአንዱ ሕመም እኛንም ሊያመን ይገባል። እንተባበር፣ እንደራጅ፣ በጋራ፣ በማያዳግም ሁኔታ፣ “በኢትዮጵያችን ከዚህ በሁዋላ በግፍ ደም መፈሰስ የለበትም” እንበል። አሁንስ በቃን !!!!

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/49378

No comments:

Post a Comment