Sunday, December 27, 2015

እነ ሀብታሙ አያሌው በጠቅላይ ፍ/ቤት የቃል ክርክር አደረጉ | አብርሃ ደስታ “ጭቆናን ካላጋለጥኩ ምኑን ተቃዋሚ ሆንኩት?” አብርሃ ደስታ

‹‹እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደመሆኔ መጠን የኢህአዴግን ጭቆና ማጋለጥ ግዴታዬም መብቴም ጭምር ነው! ይህን ካላደረጉ ምኑን ተቃዋሚ ሆንኩ?›› አብርሃ ደስታ ‹‹እኔ አሸባሪ አይደለሁም! የታሰርኩት በኢህአዴግ የፖለቲካ ሴራ ነው! እኔ የፖለቲካ እስረኛ ነኝ!›› ዳንኤል ሺበሺ


በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በሥር ፍ/ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋና በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ውስጥ ከአመራሮቹ ጋር የተከሰሰው አቶ አብርሃም ሰለሞን በፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓ.ም በመቅረብ የቃል ክርክር አድርገዋል፡፡

በችሎቱ የተሰየሙት ግራ ዳኛ መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ታህሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም ተከሳሾቹ የፍ/ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ዳኜ መላኩ ከሰብሳቢነታቸው እንዲነሱ ባቀረቡት የፅሁፍ አቤቱታ ላይ መልስ ለመስጠት፤ የተከሳሾቹንና የአቃቤ ሕግን የቃል ክርክር ለማድመጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተከሳሾቹ ‹‹ሰብሳቢው ዳኛ ይነሱልን!›› ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ፍ/ቤቱ ስላላመነበት ውድቅ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

አቃቤ ሕግ በችሎቱ ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታው ተከሳሾቹ ከግንቦት ሰባት አመራር አባላት ጋር በተለያየ ጊዜ መገናኘታቸውን፤ ይህንንም የሚያስረዳ ማስረጃ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ማቅረባቸውን ነገር ግን የስር ፍ/ቤቱ እነዚህን ማስረጃዎች ሳይመዝን ‹‹በደፈናው ውሳኔ ስለሰጠ›› ይግባኝ መጠየቃቸውንና የስር ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሲሰጥ ከጭብጥ መውጣቱን ገልጿል፡፡ ‹‹ፍ/ቤቱ ከፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀፅ 23 መሰረት የቀረበውን የሰነድ ማስረጃዎች በመመልከት የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍ/ቤቱ ይወስንልን ዘንድ እንጠይቃለን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌውና 5ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን በጠበቃቸው አምሃ መኮንን በኩል የመከራከሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ አቶ አምሃ መኮንን የስር ፍ/ቤቱ ደምበኞቻቸውን በነፃ ሲያሰናብታቸው የቀረቡትን ማስረጃዎች መዝኖ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ አቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ያቀረባቸው ነገሮች እንደመረጃ እንጂ እንደማስረጃ ሊያዙ እንደማይገባ የተከሳሾቹ የቀድሞ ጠበቃ በስር ፍ/ቤት ክርክር አድርገው የስር ፍ/ቤቱ ሐምሌ 2 ቀን 2007 ዓ.ም ‹‹በማስረጃ ሊያዙ ይገባል!›› ብሎ ብይን ማስተላለፉን አቶ አምሃ አውስተዋል፡፡ ጠበቃው ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በኩል የሚቀርቡ ማስረጃዎችም ፍ/ቤት ሊመረምራቸው እንደሚገባ ሲያስረዱ፡- ‹‹የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በኩል የሚቀርቡ መረጃዎችን ፍ/ቤቱ ሙሉ ለሙሉ የሚቀበል ከሆነ የፍ/ቤቱ ሚና ምን ሊሆን ነው? ፍ/ቤቱ ከተቋሙ በኩል የሚቀርቡለትን መረጃዎች ሙሉ ለሙሉ የሚቀበል ከሆነም ፈራጁ ፍ/ቤት ሳይሆን ብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ነው›› በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ደምበኛቸው አቶ ሀብታሙ አያሌውም በክሱ ላይ ‹‹ዘመነ ካሴ›› ከተባለው የግንቦት ሰባት አባል ጋር በመነጋገር አብረው ለመስራት ተስማሙ ተብሎ ቢገለፅም ይህን የሚያስረዳ ማስረጃ አለመቅረቡን ገልፀዋል፡፡ ደምበኛቸው ከግለሰቡ ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ አንድም ቦታ ላይ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን እንዳልገለፁ ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡ በክሱ ላይ የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የሆነው አቶ ሀብታሙ አያሌው ከዘመነ ካሴ ጋር ግንኙነት አደረጉ ተብሎ የተገለፀው ከእውነታ የራቀ መሆኑን ጠበቃው ገልፀዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ አቶ ሀብታሙ አይደለም የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሊሆኑ ቀርተው፤ የፓርቲው አባል እንዳልነበሩም አቶ አምሃ አስረድተዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ በበኩላቸው በክሱ ላይ ተከሳሽ በዚህ የሞባይል ቁጥር ግንኙነት አድርጓል ተብሎ አለመገለፁን የስልክ ልውውጡም ምን እንደሆነ የሚያስረዳ አንዳች ነገር አለመቅረቡን ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡

አቶ አምሃ ደምበኛቸው በሆነው 5ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን ላይ ምንም አይነት የሰነድ ማስረጃ አለመቅረቡን የግንቦት ሰባት አባል ነው ሲባልም፤ በግንቦት ሰባት መዋቅር ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ አለመቅረቡን ደምበኛው በምንም አይነት የሽብርተኝነት ተግባር ላይ እንደተሰማራ የሚገልፅ ምንም አይነት ማስረጃ አለመቅረቡን ገልፀዋል፡፡ አቶ አብርሃም ሰለሞን በበኩሉ ያለአንዳች ማስረጃ መታሰሩን ሲያስረዳ፡- ‹‹ከታሰርኩ በኋላ ነው ማስረጃ ሲፈለገብኝ የነበረው፤ ከታሰርኩ በኋላም ቤቴ እንኳ አልተፈተሸም፡፡ መንግስት አሰረኝ ብዬ አላምንም ያሰረኝ አንድ ግለሰብ ነው›› ሲል ተደምጧል፡፡

2ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ 3ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ ያለጠበቃ በመቆም በግል ክርክራቸውን ያካሄዱ ሲሆን፤ ሶስቱም ተከሳሾች የአቃቤ ሕግ የይግባኝ ማመልከቻ ላይ እነሱን የሚመለከት ቅሬታ አለመቅረቡን ለፍ/ቤቱ ገልፀዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹እኔ አሸባሪ አይደለሁም! የታሰርኩት በኢህአዴግ የፖለቲካ ሴራ ነው! እኔ የፖለቲካ እስረኛ ነኝ!›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የቃል ክርክር ለማድረግ ያዘጋጁት ወረቀትም በማረሚያ ቤቱ እንደተቀደደባቸው ለፍ/ቤቱ አሳይተዋል፡፡ ወረቀቱ ማህተም የተደረገበት ቦታ ተቀዶ መውጣቱን በችሎቱ ለነበሩ ታዳሚያን በግልፅ ታይቷል፡፡

3ኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃ ደስታም ከታሰሩ በኋላ ማስረጃ ሲፈልግባቸው እንደነበርና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ የሚቀርብ መረጃ በፍ/ቤት ሳይመዘን ሙሉ ለመሉ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ ተቋሙ ከሳሽም፣ መስካሪም፣ ዳኛም ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ ደግሞ ፍ/ቤት መምጣትም አያስፈልግም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በክሱ ላይ ለኢሳት ቴሌቪዥን ቃለምልልሰ ሰጠ ተብሎ የቀረበው ክስ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲያስረዱ፡- ‹‹እኔ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደመሆኔ መጠን የኢህአዴግን ጭቆና ማጋለጥ ግዴታዬም መብቴም ጭምር ነው! ይህን ካላደረጉ ምኑን ተቃዋሚ ሆንኩ?›› በማለት ለፍ/ቤቱ የገለፁ ሲሆን፤ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ሃሳባቸውን ሲገልፁ የነበሩትም የኢህአዴግን ጭቆናን ማጋለጥ መብታቸው በመሆኑ እንደሆነ ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡

4ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በእሳቸው ላይ የቀረበ አንድም የሰው ምስክር እንደሌለ ገልፀው፤ ማዕከላዊ በነበሩበት ወቅትም በምርመራ ላይ አንድም ቀን ስለግንቦት ሰባት ተጠይቀው እንደማያውቁ ምርመራ ላይ ሲጠየቁ የነበሩትም ስለ ሰማያዊ ፓርቲ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ የሺዋስ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ አያሌ መከራዎችን እየተጋፈጡ እንደሚገኙ ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ያለፉትን 6 ወራት በማንም አለመጎብኘታቸውን ለፍ/ቤቱ ገልፀዋል፡፡

ፍ/ቤቱ የቃል ክርክሩ በፅሁፍ ተገልብጦ ከቀጣይ ቀጠሮ በፊት ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌው የሚገኙበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ታህሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም መልስ እንዲሰጥ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የማረሚያ ቤት ተወካዩ በተጠቀሰው ቀን አቶ ሀብታሙን ይዞ እንዲቀርብ ፍ/ቤቱ አዟል፡፡
የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር መዝኖ ውሳኔ ለመስጠት ለታህሳስ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ እነ ሀብታሙ አያሌው ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ከተመሰረተባቸው የሽብርተኝነት ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/49442




No comments:

Post a Comment