Wednesday, September 7, 2016

“መንግስት በእብሪተኝነቱ ቀጥሏል! የታሳሪዎችን ደህንነት ለማወቅ የሞከሩ ቤተሰቦች ተደብድበዋል! ” ድምጻችን ይሰማ

በዛሬው እለት መንግስት ተጨማሪ የግፍ ዱላ በቂሊንጦ ታስረው በነበሩ ግለሰቦች ቤተሰብ ላይ አድርሷል፡፡ ‹‹ታሳሪ ቤተሰቦቻችን በህይወት ካሉ አሳዩን! ሞተው ከሆነም አስከሬናቸውን ስጡን!›› እያሉ በእንባ እየታጠቡ ሰልፍ የወጡ ቤተሰቦችን ጥያቄያቸውን በመመለስ ፋንታ ሰልፉን በትነው የተወሰኑትንም አስረዋል፡፡ ከታሰሩት ውስጥ የአያተልኩብራ ነስረዲንና የሺሀቡዲን፣ እንዲሁም የሙጂብ አሚኖ እናቶች ይገኙበታል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በደረሰው የእሳት አደጋ መንግስት የሀሰተኛ ሪፖርት ማውጣት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡ የሞቱትንም ሆነ በህይወት ያሉትን እስረኞችም ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥ አልቻለም፡፡ ‹‹የሞተው እስረኛ አንድ ብቻ ነው›› ሲል ከቆየ ከቀናት በኋላ 23 ሆናቸውንና ያመነ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በጥይት የሞቱት ሁለት ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል፡፡ የተቀሩት እስረኞችም ወደሌሎች ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተዛውረዋል ቢባልም የተባሉት ማረሚያ ቤቶች ግልጽ ማረጋገጫ መስጠት አልቻሉም፡፡ ይህ በቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት እየፈጠረ ሲሆን መንግስት ይህን የህገ ወጥነት መንገድ ተከትሎ መቀጠል መምረጡም ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ መንግስት የታሳሪ ቤተሰቦችን መረጃ መከልከሉና ለጥያቄያቸውም እነሱን መልሶ ማሰሩ በእርግጥም አገራችን ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ሶስት ነጥቦችንም እንድናሰምርባቸው ያደርጋል፡-

1. ለግድያው ተጠያቂው መንግስት ነው፤
2.
የቅሊንጦ ማረሚያ ቤት የጅምላ ግድያ ወንጀል የተፈፀመበት ቦታ (CRIME SCENE) ነው፤
3.
በህይወት የተረፉት ታሳሪዎች መንግስት ለፈፀመው የግድያና አግቶ ደብዛ የማጥፋት ወንጀል ምስክሮች ናቸው፤

በመሆኑም የኢህአዴግ መንግስት መረጃን በመደበቅና ጊዜን በማራዘም እሱ የሚፈልገውን ዓይነት ‹‹አዲስ እውነታ›› መፍጠር እንደማይችል አውቆ በአፋጣኝ በዛሬው ሰልፍ ያገታቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች አንዲለቅ፣ የገደላቸውን ታሳሪዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው እንዲያስረክብና አግቶ ደብዛቸውን ያጠፋቸውን ታሳሪዎች ያሉበትን ቦታ አሳውቆ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርግ እናሳስባለን፡፡ ህዝቡም መረጃ ስጡን ስላሉ ጥቃት የደረሰባቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች በመጠየቅ አጋርነት እንዲያሳይ እንጠይቃለን፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/65473

No comments:

Post a Comment