Thursday, September 8, 2016

” . . . . . የደም እንቁጣጣሽ . . . . . .”

በዝናም ማበቡ: ዘመን ተሽሮብሽ፣
ያልተለመደ ግብር: ዘንድሮ አየንብሽ፣
ያፈራሽውንም: አንችው ትበያለሽ፣
ምንድነው የሆንሽው: እስኪ ልጠይቅሽ
አብቅለሻል አሉ: የደም እንቁጣጣሽ።

ነሐሴን ስጠብቅ: ጳጉሜም ስትገባ፣
ጋራውን እያየሁ: ስወጣ ስገባ፣
ላዲስ ዓመት ልቆርጥ: የአደይ አበባ፤
አልፈነዳ ብሎ: የቋጠረው እምቡጥ፣
ዓይኖቸን ሳማትር: ሸለቆውን ስረግጥ፣
የደም እንቁጣጣሽ: አየሁ በጎንደር ገጥ።
የደም እንቁጣጣሽ: አየሁ በጣና ፈርጥ።
የደም እንቁጣጣሽ: አየሁ ኦሮሞ ውስጥ።

አባይ ቀልቶ አይቸው: ሲወርድ እያጎራ፣
ትቶት የነበረው: ሲፎክር ሲያቅራራ፤
ምን ሆነሃል ብየ: ብጠይቀው ሲመሽ፣
ባልጣመው ነገር ላይ: አልሰጠኝም ምላሽ፣
እንኳን አደረሰህ: ሳይለኝ አለ ገሸሽ፣
ለካ እሱም ይዟል: የደም እንቁጣጣሽ።

ወይ ሰኔና ሰኞ: ያመጣብን ጣጣ፣
እኔስ ትቸዋለሁ: አበባ ቆረጣ፣
የደም እንቁጣጣሽ: እደጀ ሳላጣ።
በሉ ቂጣ ብሉ: ግዳይ የጣላችሁ፣
ሰውንም ዱሩንም: እንዲህ መንጥራችሁ፣
ዘመን ለሁሉም ነው: እኛም አናጣችሁ፣
የደም እንቁጣጣሽ: ከርሞ እስክንላችሁ።

ተይው አትሳቂ: ምድር አታብቢ፣
አመትባል አይደምቅም: በደም ስትቀቢ።
ሌሊት በፀበሉ: መታጠብ ቀፈፈኝ፣
የደም እንቁጣጣሽ: ነክቶታል መሰለኝ።
አልጠብስም በእሳት: በግ ስጋ ዘልዝየ፣
በሳት የሞቱትን: ይዞ ህሊናየ፣
አከብራለሁ እንጅ: እንዲሁ ዝምብየ፣
የደም እንቁጣጣሽ: አድርጌ ችቦየ፣
ሁለት ሽህ ዘጠኝ: ቢታየኝ ጤናየ።
… … … … … “
የደም እንቁጣጣሽ … … … … … … …
… … …
ባንድም በሌላም ምክንያት ባሳለፍነው ዓመት ለእውነትና ለሃገር ሲሉ ህይወታቸውን ለገበሩ እህት ወንድሞቻችን መታሰቢያ … … 

http://www.satenaw.com/amharic/archives/20778


No comments:

Post a Comment