October 10, 2013 03:28 pm
በኢትዮጵያ ባሏቸው ኢንቨስትመንቶች መልከ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው የሚነገርላቸው ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በዕዳ የተያዘውን የካሩቱሪን የእርሻ መሬት ለመግዛት ከድርድር ላይ ናቸው ተባለ። ድርድሩ በስምምነት ከተቋጨ የሳዑዲን የምግብ አቅርቦት ለመሸፈን የሚንቀሳቀሱት “ባለሃብት” በጋምቤላ ብቻ ከ230 ሺህ ሄክታር በላይ ድንግል መሬት ባለቤት ይሆናሉ። በድርድሩ መሰረት እስከዛሬ ከወሰዱት በተጨማሪ ብድርም ከንግድ ባንክ ያገኙበታል።
የሳዑዲን የምግብ ኮታ ለመሸፈን ታስቦ እንደተመሰረተ የሚነገርለት የሳዑዲ ስታር አግሮ ኢንዱስትሪ በ2001 ዓ ም 10ሺህ ሄክታር መሬት ተረክቦ በጋምቤላ ስራ ሲጀምር ተጨማሪ 500 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚሰጠው ቃል ተገብቶለት እንደነበር በወቅቱ የተለያዩ መገናኛዎች ዘግበው ነበር።
ሳዑዲ ስታር የስራ አቅሙ ተገምግሞ መሬት እንደሚጨመርለት ቃል ቢገባለትም የወሰደውን 10 ሺህ ሔክታር በቅጡ አልተጠቀመም በሚል የግብርና ኢንቨስትመንት ሃላፊዎች ተጨማሪ መሬት ለመስጠት ሲያቅማሙ ቆይተው ነበር። ሆኖም ግን በአቋማቸው መዝለቅ ያልቻሉት ሃላፊዎች ለሳዑዲ ስታር ተጨማሪ 120 ሺህ ሔክታር መሬት ፈቅደዋል። በቅርቡ ከወራት በፊት በተካሄደ ግምገማ አነስተኛ የስራ ትጋት ውጤት ያስመሰዘገበው ሳዑዲ ስታር አዲስ ጥያቄ ማቅረቡን በጋምቤላ የሚኖሩ የድርጅቱ ባልደረቦች ለጎልጉል ገልጸዋል። ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊም በሰራተኞቹ የተጠቆመውን ዜና አጠናክረው አምነዋል።
በዚሁ መሰረት ንግድ ባንክ 62 ሚሊዮን ብር እዳ እንዳለበት፣ እዳውም በገባው ውል መሰረት እንዳልከፈለ፣ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም አለመሰካቱን፣ በዚህም የተነሳ ንብረት ለመውረስ መመሪያ መተላለፉንና ጉዳዩ ወደ ህግ መመራቱ ይፋ የሆነበትን ካሩቱሪ በተረከበው ማሳ ላይ ያስቀመጠው ንብረት ካለበት የሊዝ ዕዳ፣ የተለያዩ ክፍያዎችና የክልሉ ዓመታዊ ክፍያዎች ጋር ተዳምሮ እዳውን ይሸፍናል ተብሎ እንደማይገመት ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ።
በክልሉ ኢህአዴግ በጠመንጃ ሃይል እየተተገበረ ያለው የመሬት ንጥቂያ ጉዳዩን በውል የሚያውቁ ዜጎችን፣ እንዲሁም የክልሉን ነዋሪዎች ቁጭት ላይ የጣለ መሆኑ “ባለሀብቶች” ተብለው በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩትን በሙሉ እረፍት እንደማይሰማቸው የሚጠቁሙት የጎልጉል ምንጮች “ካራቶሪን በሳንቲም ሂሳብ ተቸብችቦለት ከባንክ ብድር ጋር የተረከበውን መሬት መልሶ ለመውሰድ ከፍተኛ ኪሳራ አለ። ኪሳራው የአገርና በተለይም ለዚህ ፋይዳ ለሌለው ኢንቨስትመንት ንብረቱንና ቀዬውን በጠመንጃ የተነጠቀው የክልሉ ሰላማዊ ህዝብ ነው” በማለት ቁጭታቸውን ይገልጻሉ።
“በአካባቢው ሕዝብ ተቀባይነት ያላገኘ ኢንቨስትመንት፣ በተለይም ሰፋፊ እርሻዎች ሁሌም አደጋ ላይ ናቸው” በማለት አሁንም ኢህአዴግና ባለህብቶች ከቀድሞው ጥፋታቸው እንዲማሩ የሚመክሩ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት “ካራቱሪ ከቀረጥ ነጻ ሲነግድና የተፈጥሮ ደን ሲያወድም ቆይቶ በእዳ ፋይሉ ሲዘጋ መሬቱን ለሳዑዲ የምግብ ዋስትና እንዲውል እየተደረገ ያለው ሩጫ ዳግም ስህተት እንዳይሆን” ሲሉ ይመክራሉ።
3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማዘጋጀት የአገሪቱን ምርት 39 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ አቅዶ እንደነበር የሚገልጸው ኢህአዴግ ባለበት እየረገጠ እንደሆነ ማስረጃ በማጣቀስ የሚተቹት ብዙዎች ናቸው። በተለይ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ክልል ያለውን ድንግል መሬት ከነዋሪዎቹ ጋር በመስማማት ለአገሪቱ ሕዝብ የምግብ ዋስትና ሊያውለው እንደሚገባ የግብርና ባለሙያዎች በየጊዜው የሚወተውቱት ጉዳይ ነው።
የጎልጉል ምንጮች አጠንክረው እንደሚናገሩት ካሩቱሪ የውጪ አበዳሪዎቹና የአክሲዮን ደንበኞቹ ስለከዱት ከጋምቤላ ለቅቆ ይወጣል። ካራቱሪ ቀደም ሲል 300 ሺህ ካሬ ሄክታር መሬት የነበረውና በሂደት ተቀንሶበት 100 ሺህ ሔክታር እንደቀረው፣ ከዚሁ ላይ ማልማት የቻለው አስር በመቶ ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment