ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚያደርጓቸው የተቃውሞ ሰልፎች ተደጋጋሚና መንግስት አቋም የያዘባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱ እንደሆኑ የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ መንግስት ለእያንዳንዱ ሰልፍ ጥበቃ ማድረግ ስለማይችል ሰልፎቹ በተለመደው መልኩ ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች የራሳቸው የፓርቲዎቹ ሳይሆኑ የሌሎች ሃይሎች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ሰልፍ ማካሄድ ህገመንግስታዊ መብታቸው መሆኑን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስት በተደጋጋሚ ጥበቃ ሲያደርግ ቢቆይም፣ በሰልፎቹ የሚነሱት ጥያቄዎች ፋይዳ ቢስ ከመሆናቸውና ከፓርቲዎቹ ብዛት አንፃር መንግስት በቀጣይ ለሰልፎች ጥበቃ ለማድረግ የሚቸገርበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ መንግስት በተደጋጋሚ ምላሽ የሰጠባቸውን ጥያቄዎች መላልሰው የሚያቀርቡት በመንግስት ላይ ጫና በመፍጠር አቋሙን ለማስቀየር በማሰብ ሊሆን ይችላል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይሄ ግን በፍፁም የማይሳካ ሃሳብ ነው ብለዋል፡፡ “ግንቦት ሰባት” በቅርቡ መንግስትን ለመጣል ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ በይፋ መግለፁን በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱም፣ የፓርቲው አመራሮችና ደጋፊዎች ተጨባጭ ያልሆነ ህልም ውስጥ ሆነው የተናገሩት ነገር እንደሆነና ከህልማቸው ሲነቁ እውነታውን እንደሚገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ መከፋፈልና የሃይል መጠባበቅ አለ የሚለውን መረጃ በተመለከተም “ይህ የአንዳንድ አፍራሽ ሃይሎች ከንቱ ምኞትና ተጨባጭ ያልሆነ አሉባልታ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment