ውሸት ላግዝ ካለች
ሚስማር ካቀበለች
ጭቃ ካራገጠች
ቤቱም አልተሰራ … እውነትም አልኖረች ።
… እንደዚያ ነው በባቢሎን ዘመን ።
የአንዱ ቋንቋ ከአንደኛው ይዘበራረቃል ….. መግባባትና መረዳዳት ብርቅ ይሆናል ። በጠራ አማርኛ የተጣፈውን በጉግማንጉግኛ በመተርጐም ከውስጡ የሚፈልጉትን ብቻ አለፍ አለፍ እያሉ ያነቡታል ። እናም የራሳቸውን ትርጉም ይሰጡታል ። ፍየል ወድያ ….. ቅዝምዝምም ወዲህ ይሆናል ።
ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት መካከል ጥቂት አዛውንቶች ታሪክን ደልዘው በወያኒኛ አዲስ ታሪክ ስለ አየር ኃይሉ እንዲፅፉ በህውሃት እየተጠየቁ ነው ። እነዚህ ባለ ብዙ አኩሪ ታሪክ ባለቤት አዛውንቶች መንታ መንገድ ላይ ቆመዋል ። በዓለም ዙርያ ተበትነው ያሉት የቀድሞው አየር ኃይል አባላት ሃሳባቸውን እንዲደግፉና የእርዳታ እጃቸውንም እንዲዘረጉ ለማግባባት እየሞከሩ ነው ። እኛም የቀድሞው የአየር ኃይል አባላት እንዲህ አልን ……….
(ያም ቢሆን መፅሃፉን ካነበብን በኋላ የምንታዘበው ይሆናል … አያጣላም ።) የአየር ኃይል ቬተራን አሶሴሽንን እናቋቁማለን የምትሉትን በተመለከተ ግን ወራጅ አለ ። እጅግ ከስጋት በላይ የሆኑ ጥያቄዎች አሉን ። “ የቀድሞው አየር ኃይል ቬተራን አሶሴሽን ” እያላችሁን ከሆነ ግን እንግባባለን ።
የሚለውን ጥቅል ሃሳብ በመልዕክታችን ብንሰድላቸው በጉግማንጉግኛ በመተርጐም እኛ ፖለቲካ አንነካካም …. ፖለቲካንና ኰረንቲን በሩቁ ነው ብለናል ይሉናል ከአዲስ አባ ደብዳቤ እየፃፉ ። እነሱ ለካ የአሁኑን የህውሃትን መንደርተኛ አየር ኃይል ነው ቬተራን እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት ። በህውሃት ሰማይ ስር ጉድ ሳይሰማ አያድርም አይደል !
እኛ ድፍን የአየር ኃይል ተቋም ላይ ስለተፈፀመ ክህደት ስናወራ …. እነሱ አንድ ግለሰብ አገርንና ህዝብን ለከዳ ስርዓት ስለሚመሰርተው ዕድርና የተዝካር ግርግር ሊያስረዱን ይሞክራሉ ። እኛ እኰ የቆማችሁበት አፈር ሥር ነፍሱ ያልወጣች የምታጣጥር የገዛ ጓደኛችሁ ነፍስ አለች ነው የምንላቸው ።
መጀመሪያ ባለንጀራችሁን ነፃ አውጡት ፤ እናንተም በጐን በሾርኔ ሳይሆን በአደባባይ በህግ ነፃ ውጡ ምክንያቱም እንደ ዶሮዋ ገመዳችሁ ረዘመላችሁ እንጂ ፈፅሞ አልተለቀቃችሁም እያልን ነው ።
ህውሃት እንደሆነ በሰው ተጠቅሞና አዋርዶ እንደሚያባርር የአደባባይ ሚስጢር ነው ። ደግሞም ይህ ይጠፋችኋል ብለን አንሞግትም ፤ ….. የመሰንበት ጉጉት ህሊናን ፈፅሞ ካልተቆጣጠረ በቀር ። አየር ኃይል ለአገር አንድነት የተፋለመ ጀግና እንጂ ጨፍጫፊ ያለመሆኑን በአደባባይ ስትመሰክሩና በህግ
ስታስነግሩ ….. የአየር ኃይል ተቋም እንደ ተቋም ነፃ ሲወጣ …. እርቅ ሲወርድ ፣ አገርን ከጠላት በመከላከላቸው ብቻ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኞች በአደባባይ ነፃ ሲወጡ …. ያን ጊዜ ሁላችንም በአንድነት ነፃ እንወጣለን ። ያለበለዚያ ግን ትውልድም አገርም ላይ ይቅር የማይባል ክህደት ትፈፅማላችሁ እያልን ነው ያለነው ፤ በጠራ አገርኛ ቋንቋ ።
የቬተራን አሶሴሽንን በመወከል ያገባኛል ብለው ከአዲስ አበባ መልዕክት የሰደዱልን ሰው በፍፁም ሃሳባችንና ሥጋታችንን በትክክል የተገነዘቡ አይመስሉም ወይንም ዛሬ ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚከታተሉም መሆናቸውን እንድንጠራጠር እያደረገን ነው ። ድንገት ዘንድሮ ጆሮዋቸውም ዓይናቸውም የተከፈተላቸው ይመስል በቃል ያጠኑትንና ስለ አየር ኃይሉ የሚገምቱትን በጐ ፍላጐት ለመተግበር የተነሱ ይመስላል ።
የህውሃት አስተዳደር አዛውንት የአየር ኃይሉን አባላት በማምሻ እድሜያቸው ታሪክን ደልዘው የእራሱን የተንጋደደና የተንሸዋረረ ታሪክ እንዲፅፉለት እየተጠቀመባቸውና ከጠራ ታሪካቸው አንስቶ ከራሱ ቆሻሻና ስውር ፍላጐት ሥር እያንደባልላቸው ያለ ይመስላል ። አየር ኃይሉ በአዋጅ ሙሉ ለሙሉ ከስራ ውጪ በተደረገበት ዘመን ላይ ፤ ጨፍጫፊ ተብሎም ቅፅል ስም ወጥቶለት ወደ ከርቸሌ መጋዙንና በመንደርተኛ ፓይለቶች እየተተካ መሆነኑን ትንፍሽ እንዳይሉ በዚሁ በምሽት እድሜያቸው እየተደለሉ ናቸው ። እንዲያውም ሙዝየም እስከ መክፈት የዘለቀ ህልምም እንዳላቸው እየጠቀሱ ነው ። አገር ቢኖረንማ ኖሮ ለትውልድ የሚቀር ፣ ታሪክን የሚዘክር ሙዝየም ማቆም እንዴት የተባረከ ህልም ነበር ? ነገር ግን አገርም ዜግነትም በተዋረዱበትና እድሜያቸውን ሙሉ ለአገር አገልግሎት ያበረከቱ አንጋፎች እንደ አሮጌ ቁና በውርደት እንዲኖሩ በአደባባይና በአዋጅ ባይበየን ኖሮ ፣ ትውልድም በበጐ መሰረት ላይ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ …. ሁሉም አላማ በጐና ለአገርም ሆነ ለትውልድ የሚጠቅሙ ይሆኑ ነበር ።
እንግዲያውስ እነዚህ በህውሃት እየተደለሉ ያሉት የአየር ኃይሉ ነባር አዛውንቶች እርማቸውን ያውጡ ። ህውሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ወዲህ ያለውን አየር ኃይል ተብዬ እንጂ የቀድሞውን ታሪክ ምናምኒት አሻራ እንኳ አያገኙም ። አጠቃላይ ሰፈሩና ቢሮዎቹም ጭምር በአይጥ መንጋ እንደተመታ ባድማ ዶክመንቶች ተፈርፍረው ድምጥማጣቸው መጥፋቱን አይጠራጠሩ ። የአየር ኃይሉን የታሪክ አሻራ ሊያስረዱ የሚችሉ የተለያዩ አውሮፕላኖችን ማናምኒት ሳያስቀር አቧራቸውን እያራገፈ የህውሃቱ አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ መቸብቸቡን እንዴት ሳይነግራቸው እንደቀረ ይገርመናል ? ይህ ቀበኛ ሽፍታ ለጌጥና ለታሪክ በአየር ኃይሉ ጠ/መምሪያ ፊት ለፊት እንኳ ተቀምጣ የነበረችውን ገብሬ ቦላሌን ሳይቀር አንጠፍጥፎ መሸጡን ለምን ደበቃቸው ? ታሪክ በመስራት አገራችንን ያስከበረችውን ኤፍ-5 አውሮፕላንንስ አንዲት ሳያስቀር መቸብቸቡንስ ?
በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር የሚመራውን የአሁኑን ሥርዓት አያውቁትም እንበል ወይስ የክፋትና የብቀላ ምግባሩን ሁሉ ትተው በጐ ተክለ ሰውነት ሊገነቡለት እየሞከሩ ይሆን ? ታዲያ ይህንን እየሰሩ እንዴት ፖለቲካ አንነካካም ይሉናል ? በእነርሱው አመራር ስር የተገነባው የአየር ኃይል ሰራዊት እኰ በጅምላ ጨፍጫፊና ወንጀለኛ ተብሎ እድሜውን ሙሉ ከአቀናው መስሪያ ቤት በውርደት ተባሮ ቤተሰቡ ተበትኖ በረሃብና በችጋር እንዲያልቅ ተፈርዶበታል ! እውነተኛዎቹ የአየር ኃይሉ አርበኞች ድፍን 22 ዓመታት ሙሉ ተሸማቀውና አንገታቸውን ደፍተው መሃል ደ/ዘ ውስጥ (በቀለ ሞላ ሆቴል ፊት ለፊት) በጠጠርና በቆርኪ ዳማና ቼዝ ሲጫወቱ የአዛውንቶቻችን መንግስት የት ነበር ? ለዚህ ሁሉ ግፍና በደል ተጠያቂው ማነው ? እነዚህንና ሌሎች በደሎችን እንዴት ነው የሚያስታርቁት ? በምንስ መመዘኛ ቀበኛ ሽፍታ የመሰረት ድንጋይ እንዲያነጥፍላቸው ያደርጋሉ …. ! ከረገጡት ምድር ስር
የባልንጀሮቻቸው የምትቃትት ነፍስ ምን ትላቸው ይሆን ? ፖለቲካ … ፖለቲካ …. ለምን እንደሚሉን አልገባንም ። ፖለቲካ ምንድነው ?
ለዘመነኖቹ የመንግስት ባለስልጣናት ማደር ? ለስብሰባ ሲጠሩ ፈጥኖ ሸገር ላይ መከሰት ? ወይስ ሲመሩት የነበረውን ሰራዊት አስማርኰና ክዶ ለትግራዩ የነፃነት (ተገንጣይ) ግንባር በፈቃደኝነት መገበር ? እኛ ፖለቲከኞች እያሉን የሚያበሻቅጡን ከአገር በግፍ ተገፍታሪ ስደተኞች በሰላም ተከባብረንና ተዛዝነን ድፍን 20 ዓመታትን እንዳሳለፍን በአለፈው የበጋ ወቅት በዋሽንግተን ከተማ ተገኝተው መታዘባቸውን እናውቃለን ። አየር ኃይል ማለት ለኛ መታወቂያችን ፣ ማንነታችንና ዜግነታችንም ጭምር ነው ። በህብረት ተደጋግፈን እንኖራለን ፤ የተቸገረን እንረዳለን ፣ የታመመን እናስታምማለን … እንጠይቃለን ፣ እስከወዲያኛው የሚሰናበተንንም በኃዘን እንሸኛለን ።
ጀግኖቻችንን ከተጣሉበት እያስታወስንና እያነሳን እናከብራቹኋለን እንላለን ። በየዓመቱም የአየር ኃይል ቀን በማለት በህብረት ዩኒፎርማችንን ለብሰን ባንዲራችንን ከፍ አድርገን እያውለበለብን ኢትዮጵያ ሃገሬን እንዘምራለን ….. ። ይህንን ባንዲራና ዝማሬ የአሁኑ መንግስት አይወደውም ። በዘር ከፋፍሎ እኛ እና እነርሱ ፣ የቀድሞውና የአሁኑ ፣ ጨፍጫፊና ዲሞክራቲክ በማለት እየለያየ አጥፍቶናል ። አሁን ደግሞ እዚሁ ያለንበት አገር ድረስ ክንዱን እያረዘመ መካከላችን ሊገባ እየተቅበዘበዘ እንደሆነ ይገባናል ። እባካችሁን አዛውንቶቻችን ለዚህ መንደርተኛ ስርዓት ክርንና ጅማት እየሆናችሁ ህውሃት ጣቱን እቤታችን ድረስ እንዲያረዝም እየረዳችሁ መካከላችን እንዲገባ አታድርጉ ፤ በማህበራችንም በኩል አትምጡ ።
በግል እኰ መፅሃፍ አይደለም ኤግዚቢሽንም መክፈት ትችላላችሁ ። አሁን እየመጣችሁበት ያለው መንገድ ግን የሁሉንም ምክር ፣ የብዙሃንን ይሁኝታ ይጠይቃል ። እናንተ ደግሞ እዚያው አገር ቤት ያሉትን እውነተኞቹን አርበኞች አንድ በአንድ ሲያልቁ ጠብቃችሁ ፣ በህይወት የተረፉትንም ንቃችሁና ገፍትራችሁ ቀበኛ የሃገር ጠላት የሆኑትን ቱባ የህውሃት ባለስልጣናትን በጀርባችሁ አዝለችሁ አትላንቲክን በማቆራረጥ ልታነታርኩን ትሞክራላችሁ። ለምን ድምፃችሁን አጥፍታችሁ ታሪክ መፃፍም ሆነ ዕድር ማቋቋም አልመረጣችሁም ? በማህበራችን በኩል ለመምጣት ለምን መረጣችሁ …. ? በብዙሃን ስደተኛና በውርደት ተባራሪ ስም በየሸራተኑ ከበሮ መደለቁንስ ምን አመጣው ?
እንግዲያውስ ለሁለተኛ ጊዜ ምክር እንለግስ ……….
ሰው ባለቀ እድሜው ላይ ለኑዛዜ ይመቻቻል ….. እውነትን ተናግሬ ካልሞትኩ ብሎ ከህሊናው ጋር ትንቅንቅና እልክ ይጋባል ….. እውነቱን አፍርጦ በመሸበት ያድራል … እንጂ ለዳግም ምርኰ እራሱን አሳልፎ አይሰጥም ። በዚህ እድሜ እኰ ግጥም ብሎ ከሞላ የውስኪ ባንኰኒ ላይ የምንጭ ውሃ ካልሆነ ንክች አላደርግም .. ፣ ከተትረፈረፈ ጮማና ቁርጥ መሃል ቲማቲምና ቅጠላ ቅጠል ካልሆነ ምናምኒት አልቀምስም እየተባለ የሚኖርበት እድሜ ነው ፣ ብዙ የሚያጓጓ ህይወት የለም ። ታዲያ ምንድነው በዚህ በኪኒኒ ተደግፎ በሚኬድበት የምሽት እድሜ ላይ ሆኖ ውሃና ዘይትን ለመቀላቀል መሞከር ? በዚህ ምግባር ትውልድ አይደለም ከአብራክህ የወጣ ልጅ ይጠየፍሃል ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
ታዛቢዎች በህብረት !
ከቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በያሉበት ።
https://www.zehabesha.com/amharic/archives/12019
No comments:
Post a Comment