Wednesday, January 22, 2014
በሶሴፕ ፕሬዘዳንት በአቶ አሊ ሁሴን ላይ የተቃጣውን የግድያ ዛቻ ማውገዝ ይጠበቅብናል
ሲራክ ክሚድ ዌስት
በኢትዮጵያውያ የፓለቲካ እስረኞች ተከራካሪ ድርጅት (ሶሴፕ) ፕሬዘዳንት ላይ የወያኔ የግድያ ዛቻ ማድረጉን ያነበብኩት ከሶሴፕ ልሳን ላይ ነው፡፡ ዛቻው ብዙም አያስደንቅም፡፡ የሚያስደንቀው ግን አንዳንድ ሚዲያና ድርጅቶች ስለዛቻው ግድ ማጣትና ሊያወሩት ያለመፈለጉ ጉዳይ ነው፡፡ እስቲ በቅድሚያ ስለ ኣቶ አሊ ጥቂት ሃቆችን ልናገር፡፡
አሊ ሕይወቱን የሰጠው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ለመታገል ነው፡፡ የትግሉ ጉዞ ከ40 አመታት በላይ አስጉዞታል፡፡ አልደከመም፡፡ አልተሰላቸም፡፡ ለትግሉ ቤተሰቡን ሳይቀር አሰማርቷል፡፡ ጠጋ ብሎ ቤተሰቡን ላየ ራሱ አሊ ባለቤቱና ልጆቹ ፍቅር ናቸው ፡፡ ልበ ሩሩሕ በመሆኑ በሰዎች ችግር ላይ ፈጥኖ ይደርሳል፡፡ አሊ ሁሴን በተገኘበት ቦታ ሁሉ ሕዝብን የማዝናናትና የማሳቅም ፀጋ አለው፡፡ ገጣሚ ሲሆን ግጥሞቹ ሁሉ መልዕክት የተሸከሙ ናቸው፡፡ የደርግን ዘመን እስርቤት ግፍ የሚዘክር ዶክሜንተሪ ቪዲዮ ቅንብር አውጥቶ ድንቅ ተብሎበታል፡፡ ቤቱ ሁሌም ለስደተኞች አንደ አብርሃም ቤት ክፍት ነው፡፡ ከአንድ መቶ በላይ ስደተኞችን ከሱዳን ከኬንያና ከሌሎችም ስፍራዎች የስደት ውጣውረዱን አስፈጽሞ ለነፃነት አብቅቷቸዋል፡፡ ሶሴፕ በካናዳ እጅግ በጣም የተከበረ የሰበአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት እንዲሆን የበቃ ጀግና ነው፡፡ ያስተዋልኩት ጉዳይ በመሆኑ ብዙ ልናገርለት እችላለሁ፡፡ ስለመልካም ስራው የተሸለመው ሰርቲፊኬቶች በርካታ ናቸው፡፡
በአሊ ላይ የነብስ ግድያ ዛቻ እንደደረሰበት ሶሴፕ በልሳኑ ላይ ግልጽ ካደረገ ቀናት ተቆጥሯል ጉዳዪ አሳዛኝ ቢሆንም ሚዲያዎችና ድርጅቶች አለመቆርቆራቸው አስገርሞኛል፡፡ ያኔ በወያኔ እስር ላይ ሲማቅቁ ለነበሩት ሁሉ ሶሴፕ ኢትዮጵያውያንና አለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጉኣች ድርጅቶች እንዲያውቁትና እንዲሟገቱላቸው ሳይታክት ሰርቷል፡፡ አሁንም የሚያኮራ ስራ በመስራት ላይ ነው፡፡
የማስፈራራቱን ዛቻ የካናዳ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት በጉዳዪ ላይ ክትትል እያደረገ ነው፡፡ አንድም በግለሰብነቱ አንድም በሶሴፕ ፕሬዘዳንትነቱ፡፡ አለም አቀፍ የሰበአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ በዲያስፖራ ካሉት በርካታ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ጥቂቶቹ ብቻ ትኩረት ሲሰጡት በርካታዎቹ አልሰማንም ያሉ ይመስላል፡፡ ወያኔ በማንኛውም ኢትዮጵያው ላይ የሚሰነዝረውን ማስፈራሪያ ሰው ከሰው ሳንመርጥ መኮነን ይገባናል፡፡ ላንዱ ተከራክረን ለሌላው አያገባንም የሚል ድርጅት ወይም ሚድያ ካለ በጣም ተሳስቷልና በቶሉ እርምት ማድረግ አለበት፡፡በሶሴፕ ፕሬዘዳንት አቶ አሊ ላይ የተወረወረው ዛቻ በሁላችንም ላይ የተደረገ ዛቻ ነውና ባንድነት ልንዋጋው ይገባናል፡፡ ዛሬ በአሊ ላይ የተቃጣውን ማስፈራሪያ ዝም ካልኩ ነገ ዛቻ ብቻ ሳይሆን ግድያውም በኛላይ ይደረጋልና ጎበዝ በግዜ እንንቃ፡፡
http://assimba.org/Articles/Ali_Husien_Masferaria.pdf
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment