(ዘ-ሐበሻ) በጎንደር ክ/ሃገር ሳንጃ ወረዳና አካባቢው ሕዝብን ሲያሰቃይ ነበሩ የተባለት የልዩ ሃይል አዛዥ ሻለቃ ቀለሙ ክብረት መገደሉ ተሰማ። የአርበኞች ግንባር ለግድያው ሃላፊነቱን ወስዶ “ግለሰቡ የተገደለው በጥር 21-2006 ዓ.ም ከቀኑ 12 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰርጎ ገቦች ማሰሮ ደንብ የተባለ ቦታ በጥይት ተደብድቦ ቆስሎ ወዲያውኑ ወደ ጎንደር ቸቸላ ሆስፒታል ቢወሰድም በማግስቱ ማለትም በጥር 22-2006 ዓ,ም ህይወቱ አልፏል።” ብሏል።
(የአርበኞች ግንባር ወታደር – ፎቶ ፋይል)
እንደ አርበኞች ግንባር ገለጻ ከሆነ “ይህ ግለሰብ በወረዳው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአርበኞች ደጋፊ ናችሁ በሚል ሲያሰቃይ የነበረ ሲሆን፣ ብዙ ንፁሃን ግለሰቦችን በድርጅቱ ደጋፊነት ስም እየፈረጀ እንደገደለ፣ እንዳሰረና እንዲሰደዱ ሲያደርግ የነበረ መሆኑ ይታወቃል ። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ግለሰቡ ከድርጊቱ ታቅቦ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር ካልሆነ ግን አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድበት የፅሁፍ መልዕክት የደረሰው ቢሆንም ሊታረም ባለመቻሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰርጎ ገቦች እርምጃ እንዲወስዱበት ተደርጓል።” ብሏል።
(የአርበኞች ግንባር ሠራዊት በምረቃ ላይ – ፎቶ ከፋይል)
“በጎንደር አካባቢ ምንም አይነት ወታደራዊ እርምጃ በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ሲወሰድ የአካባቢውን ሕዝብ ማንገላታቱ የተለመደ ቢሆንም ሻለቃ ቀለሙ ክብረት ከሞተበት ከትናንት ጀምሮ ግን በህዝቡ ከፍተኛ ስቃይ እያደረሰበትና ገዳዮቹን ታውቃላችሁ እናንተ ናችሁ እየደበቃችሁና ቀለብ እየሰፈራችሁ የምታስጨርሱን በሚል ብዙ ሰዎች እንደታሰሩ ታውቋል።” የሚለው የአርበኞች ግንባር ዜና “የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ወታደራዊ መምሪያ በበኩሉ ወደፊትም ቢሆን ወያኔና ተላላኪዎቹን ከዚህም በከፋ ሁኔታ አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣ አስታውቆ ሕዝቡም ከመሬቱና ከንብረቱ እየተፈናቀለ መኖሩ ያበቃ ዘንድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ይህን አፋኝ ስርዓት ለመገርሰስ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ብሏል።
በዚህ ዜና ዙሪያ የመንግስትን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/12396
No comments:
Post a Comment