Monday, January 27, 2014

ዳር ሆነው የሚመለከቱት የጎሳ ፖለቲካ ምሱ “ደም”!!

image1


“ህወሃት” የሚባለው የትግራይ ነጻ አውጪ ትግራይን መቼና ከማን ነጻ እንደሚያወጣ በውል የተቆረጠ ቀን ባይኖርም ህገ መንግስታዊ ዋስትና ግን አለው በሚል እየተተቸ 23 ዓመታትን አስቆጥሯል። አገር እየመራም ነጻ አውጪ፣ በረሃም እያለ ነጻ አውጪ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲወከልም ነጻ አውጪ!!
ይህንን የተለመደና ግራ የሚያጋባ እውነት ያነሳነው ወደን አይደለም። ይህ የህወሃት ግልጽ መለያና ከመለያው የሚነሳው ትንታኔ ለማንም የተወሳሰበ ይሆናል ብለንም አንገምትም። ኢህአዴግ የሚባለው የ”ሎሌዎች” ስብስብ ያበጀውና የሚመራው ህወሃት ከሌሎቹ በተለየ በነጻ አውጪ ስም 23 ዓመት አገር ሲገዛ ሌሎቹ “የነጻ አውጪ” ስም አለመያዛቸው ግን ሁሌም ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ ይመስለናል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ “ነጻ” መውጣት ያለባቸው ህወሃቶች ሳይሆኑ ሌሎች የአገራችን ህዝቦች፣ የትግራይን ንጹሃንን ጨምሮ ነው። ህወሃት ሲጠነሰስ ጀምሮ የነበሩትን ቀደምት አመራሮች በሂደት እየበላ አራት ኪሎ የደረሰው፤ ህወሃት መጥበብ የጀመረው ገና ከጥንስሱ ጊዜ ጀምሮ ነው። ስለ ህዋሃት የሚወጡ የምስክሮች ሪፖርቶችና መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ህወሃት በደም የታጠበ፣ በደም የተለወሰ፣ የበርካታ ንጹሃን ደም ያጨማለቀው፣ ታሪኩ ሁሉ በደም ዙሪያ የተሰራ፣ አሁንም ከዚሁ የደም ቁማር ነጻ መሆን ያልቻለ መሆኑን ነው።
ህወሃት ግዛቱን እያሰፋ ሲሄድና አጋጣሚው ሲያመቸው ከተቋቋመለት መሰረታዊ ሃሳቡ ዘሎ “መንግስት” መሆን ሲያምረው “ኢህአዴግ” የሆነው ዓላማውን በወጉ ከ”መጥበብ ወደ መስፋት” በመቀየር ሳይሆን “በሰፍቶ መጥበብ ውስጥ” እየተጫወተ አገርና ህዝብን ረግጦ ለመግዛት ነው። ለዚህም ይመስላል ኢህአዴግን አሁን ድረስ “አገዛዝ” ከማለት በዘለለ በመንግሥትነት ሊጠሩት የማይፈልጉ የበረከቱት።
በግብር እንደታየው በህወሃት “የሰፍቶ መጥበብ” ጨዋታ ውስጥ ቅድሚያ ትግራይ መወለድ፣ ሲቀጥል የትውልድ ቦታንና ስምን በመቀየር ማጭበርበር፣ ከዛም ታማኝ መሆን፣ ከሁሉም በላይ አነስተኛ ክልል በሚል ስልታዊ አካሄድ ብርና ኮብራ እየሸለሙ ማታለል፣ የአገዛዙ መለያ ሆነ። አሁን ድረስም ይዘቱ ባይቀየርም አፈጻጸሙ ግን ከክልል ወደ አውራጃ፣ ከአውራጃም ወደ ወረዳና ቀበሌ፣ ከወረዳና ቀበሌ ወርዶ ስጋና ደም የሚቆጠርበት የስልጣን ቅርምት ደረጃ “እድገት” አሳይቶ ይገኛል።
በዚህ መልክ በተዋቀረው የህወሃት አገዛዝ ቁጥጥርና ክትትል አስቸጋሪ በመሆኑ አገሪቱ በሙስና በሰበሰች። ሙስናው ፈር ለቅቆ በድሃው ህዝብ ላይ ነገሰ። አወቃቀሩ ስርዓቱን በመታደግ ላይ የተመሰረተና የህወሃትን ባለጊዜዎች ስልጣን ማስጠበቅ በመሆኑ ሁሉም ነገር ሸተተ፤ ገለማ። ያቋራጭ ሃብታሞች ናኙ። ግንባታው ጨሰ። “ህዳሴው” ለተወሰኑ ወገኖች ፈንጠዝያ የተሰጠ ስያሜ ሆነ። ግድያ፣ እስር፣ እንግልትና አፈና እደግ ተመንደግ ተባለ። ነገሩ እንዲስተካከል ትግል የሞከሩ ተባረሩ፣ ታሰሩ፣ የተገደሉም አሉ። የተሰደዱ ጥቂት አይደሉም። አገር ውስጥ የቁም እስረኛ ሆነው ጊዜ የሚጠብቁ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
ሲጀመር በብሔር ብሔረሰቦች ስም ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩት የህወሃት መሪዎች፣ የራሳቸውን ሰዎች ሳይቀር ወረዳ እየለዩ የፈጸመባቸው ተግባር፣ በሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ላይ ከስርዓቱ መርህ በመነሳትና “በጥጋብ” የተፈጸመው በደል፤ “የገዢው መደብ ነኝ” በሚል ንጹሃንን ከስራና ከሃብታቸው ከማፈናቀል ጀምሮ የተሰራባቸው ግፍ ከጎሳ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ጋር ተዳምሮ የተካረረ ደረጃ ደርሷል።
የከፋቸው በዝተው ቂማቸው እየተናነቃቸው ይገኛሉ። የህወሃት አመራሮች ከፊታቸው ክፉ ዘመን ስለመኖሩ ብዙም የተጨነቁ አይመስሉም። የቂም በትር ቀጠሮ የለውም። ቂም ቦታ አይመርጥም። የጎሳ ፖለቲካ በባህሪው ምሱ ደም ነው። የጎሳ ጣጣ ባለባቸው አገሮች የታየው ይኸው እውነት ነው። በተለይ ህወሃቶች አሁን ባጨመላለቁት ደረጃ እንለካው ከተባለ አደጋ አለ፤ ያውም ግልጽ የሆነ አደጋ። ችግሩ ሲነሳ፣ ቂም በትር ሲሰነዝር፣ ጥላቻ ልጓሙ ሲበጠስ፣ በብርና በመሳሪያ ብዛት መታደግ የሚቻል አይሆንም። ይህንን ስንል ላገራችን ችግርና የደም አታሞ ለመምታት አይደለም። የቆምንለት ዓላማና የሙያ ቃልኪዳናችን ከጎሠኝነት ይልቅ ሰብዓዊነትን ማስቀደም መሆኑን የሚጠሉንም ጭምር ያውቁታል፡፡ በዚህ የሰፋ ራዕይ ውስጥ ስላለን የመጥበብ አደጋ ምን እንደሆነ በግልጽ ይታየናል፡፡ ስለዚህ የአደጋ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን፡፡
ዛሬ ዳር ቆመን የምንመለከተው የጎረቤታችን ደቡብ ሱዳን የጎሳና የዘር ጭፍጭፍ “እኛም ቤት እሳት አለ” ስለሚያሰኝ ነው። የሚታሰሩ፣ የሚገረፉ፣ የበይ ተመልካች የሆኑ፣ የተገደሉ፣ አሁን ድረስ በስቃይ ላይ ያሉ … ቤቱ ይቁጠራቸውና ዘመድ፣ ወገን፣ ተቆርቋሪ፣ አለኝታ፣ ታዳጊ አላቸው። ብሶት ህወሃትን ብቻ አይወልድምና ሁሉም ረጋ ብሎ ያስብ። ህወሃት ብቻ የብሶት የበኩር ልጅ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ሲያሻ ህግ እየተጠቀሰ፣ ሲያሻ በተቀነባበረ ድራማ፣ ሲፈለግ በተፈለገው መንገድ የሚፈነጭበት ጊዜ ሳያረጅ ለሰላም ሁሉም እጁን ያንሳ!! የጎሳ ፖለቲካ ምሱ ደም ነውና ሃዘን ሳይመታን በእውነተኛ እርቅ ጊዜው ሳያልፍብን የጎሳ ፖለቲካን ምስ እናምክን!! ተቃዋሚዎችም ጭምር!!
    http://www.goolgule.com/the-result-of-ethnic-politics/

No comments:

Post a Comment