Monday, December 1, 2014

ህጋዊ ተቃዋሚዎችን በአክራሪነት ሰበብ ለመምታት የሚያስችሉ ሃሳቦች ቀረቡ

ኀዳር ፳፪(ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በሃገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ 31 መሰረት በህጋዊ መልኩ ተመዝግበው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቃስቃሴ የሚያደርጉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን በሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነት በመፈረጅ የጥቃት ኢላማ ለማድረግ መታሰቡን ኢሳት የፌደራል መንግስት የጸጥታ ጉዳዮች ሰሞኑን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር  ካካሄደው ውይይት ለመረዳት ተችሎአል፡፡

የትግራይ፣ቤንሻንጉል ጉሙዝና አማራ ክልል ሃላፊዎች ሰማያዊ ፣አንድነትና መኢአድ ፓርቲዎች ጽንፈኞች በመሆናቸው በአክራሪነት ሲሳተፉ የነበሩ ወጣቶችን በማሰባሰብ ለሽብር እያዘጋጁ ነው በማለት የገዢውን መንግስት ፖሊሲዎች በሰላማዊ መንገድ የሚቃዎሙትን ፓርቲዎችን በወንጀለኛነት ሲፈርጁ ተደምጠዋል፡፡

መልካም ተሞክሮ ነው በማለት በየክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊዎች የቀረበው ሪፖርትና የወደፊት እንቅስቃሴ በመጭው ምርጫ 2007 የተፈረጁት ፓርቲዎች የህዝብ ድምጽ በማግኘት የገዢው መንግስት ስጋት እንዳይሆኑ ከማሰብ የተነሳ መሆኑን የውስጥ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡

በሃገሪቱ በትጋት ከሚንቀሳቀሱና የህዝብ ድጋፍ በብዛት እያገኙ ከመጡት የተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል የሚመደበው የሰማያዊ ፓርቲን እንቅስቃሴ ለማስቆም እና የምርጫ 2007 ስጋት መሆናቸውን ለማክተም ገዢው መንግስት በየአካባቢው የሚከሰቱ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ማገናኘት መጀመሩ ሆን ተብሎ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን ለመምታት የተዘጋጀ መሆኑን ምንጮች ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሴ አሰሜ  “በክልሉ አክራሪነት አሁን ያለበት ደረጃ ሲገመገም አሁንም ስራ የሚጠይቅ ነገር እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ አሁን አሸንፈናል ሙሉ በሙሉ አስወግደናል ብለን አንወስድም፡፡በማለት አክራሪነት   መልኩን እየቀየረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በደቡብ ወሎ ቃሎ አካባቢ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ ፣አንድነትና መኢአድ የተባሉት ጽንፈኛ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያካሂዱት የአባላት ምልመላ ከምርጫ ጋር በማገናኘት በጽንፈኝነት አስተሳሰብ እየተጓዙ በመሆኑ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገን መጓዝ አለብን፡፡በማለት የተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ለማሸማቀቅ የሚያስችል እንቅስቃሴ እንዲጀመር ሃሳብ አቅርበዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊም  የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ይፈቱ ብለው ያቀረቡትና በሚዲያ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ አባሎች የአክራሪነትና ጽንፈኝነት አስተሳሰብ የያዙ ናቸው በማለት ለተሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

በአማራ በቤንሻንጉልና በትግራይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ክልሎችና ልዩ ልዩ አስተዳደሮች ተጠናክሮ ሊተገበር እንደሚገባም በስብሰባው ላይ ሃሳብ ተሰጥቷል፡፡

ፓርቲዎቹ እስካሁን ድረስ ህዝቡን ለማደራጀት አቅም ባለመፈጥራቸው አስፈሪ አለመሆናቸውን የገለጹት አንድ ባለስልጣን፣ በሂደት ሃቅም እያጎለበቱ መሄዳቸው ስለማይቀር እስከሁን እንደተወሰደው ያለ ኢርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።


ኢሳት የፌደራል መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ያደረጉትን ስብሰባ በተመለከተ ተጨማሪ ዘገባዎችን ሰሞኑን ያቀርባል።

http://ethsat.com/amharic/%E1%88%85%E1%8C%8B%E1%8B%8A-%E1%89%B0%E1%89%83%E1%8B%8B%E1%88%9A%E1%8B%8E%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8A%AD%E1%88%AB%E1%88%AA%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%88%B0%E1%89%A0%E1%89%A5-%E1%88%88/

No comments:

Post a Comment