Tuesday, December 2, 2014

የድምፃችን ይሰማ ወቅታዊ ጽሁፍ: ለህገወጥ በደል እምቢተኝነት በራሱ ታላቅ ድል አይደለምን?

ማክሰኞ ህዳር 23/2007

ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ የመብት ትግል ከጀመረ አንስቶ ከመንግስት የሚሰነዘርበትን በርካታ ጥቃቶች ተቋቁሞ አሁንም ድረስ በትግል ላይ ጸንቶ ቆይቷል፡፡ ሰላማዊ ትግል በባህሪው የሚወስደው ጊዜ ሊያጥርም ሊረዝምም እንደሚችል ታሪክ የሚመሰክር ቢሆንም ህዝበ ሙስሊሙ መጀመሪያውኑም ወደ ትግሉ ሲገባ በአጭር ጊዜ የሚገኝ ድል እንደሌለ አምኖበትና አውቆት እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ትግሉ በተጠነሰሰበት አወሊያ በየሳምንቱ ጁሙዐ እየተሰባሰበ ሃሳብ በሚለዋወጥበት ወቅት እንኳን ትግሉ ሊረዝም እንደሚችል እና ፈታኝም እንደሚሆን ቀድሞውኑ በቅጡ ተረድቶ ነበር፡፡ በየትኛውም የትግል ሂደት ከዋናው ድል በፊት የሚመጡ በርካታ ድሎች እንደሚኖሩም በሚገባ ተረድቷል፡፡ ለዚያም ነው በትግሉ ርዝመት ሳይሰላች መንገዱ ላይ ያገኛቸውን ድሎች እያስጠበቀ በትግሉ ሀዲድ ላይ መጓዙን የቀጠለበት፡፡ ከእነዚህ በሂደት ከተገኙ የድል እሴቶች መካከል ደግሞ የህዝበ ሙስሊሙ ለበደል እምቢተኛ መሆን አንዱ ነው፡፡

ህዝበ ሙስሊሙም ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ መብቱን ሲጠይቅ ከመንግስት በኩል እየተፈፀመበት ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት ተቋቁሞ በትግሉ መስመር ላይ ቀጥ ብሎ ተገኝቶ ለህገወጥ በደል እምቢተኝነቱን ማሳየቱ በሀገራችን የሰላማዊ ትግል መድረክ ልዩና ደማቅ ታሪክ አስመዝግቦለታል፡፡ ግና መንግስት ትግሉ ሰላማዊና ህገ መንግስታዊ መሆኑን እያወቀ ሆን ብሎ አሰቃቂ እርምጃ እየወሰደ የህዝቡን ሞራል ለመስበርና ከትግሉ እንዲወጣ ለማድረግ ሞከረ፡፡ ህዝቡ ግን አሁንም ድረስ ‹‹እምቢ ለመብቴ! ዲኔ ከሌለ እኔ የለሁምና የሚመጣውን እቀበላለሁ!›› በሚል ወኔና እምቢተኝነት ተንቀሳቅሷል፡፡ የሚጠበቅበትን መስዋእትነትም ከፍሏል፡፡

በቅርብ ዓመታት በታዩ የአገራችን ማህበረ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ መንግስት መፍትሄ ያልሰጠው አንዱ ትልቁ ጉዳይ ይኸው የህዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖት መብት ጥያቄ መሆኑንም መንግስት ራሱ ሊከደው ያልቻለው እውነታ ነው፡፡ ይኸው ህዝብ ጥያቄው ሳይመለስለት ወደኋላ እንደማይልም ከማንም በላይ መንግስት ራሱ ያውቀዋል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙም አሁንም ድረስ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም እምቢተኝነቱን በተግባር እያሳየ ነው፡፡

አዎን! መብትን አሳልፎ አለመስጠት (እምቢተኝነት) ለዋናውና ትልቁ ድላችን መዳረሻ እንደ አንድ ዋነኛ ግብዓት ተደርጎ የሚወሰድ ነውና ህዝበ ሙስሊሙ በመንግስት ጥቃቶች ሳይደናገጥ በዚሁ ህዝባዊ ፅናት ላይ መገኘቱ ድሉ ከሚገመተው በላይ ቅርብ ለመሆኑ አመላካች መሆኑ አያጠራጥርም፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!!!



ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/36734

No comments:

Post a Comment