በትናንትናው እለት ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይና በሌሎች
የከተማው አካባቢዎች በተቃዋሚ ድርጅቶች በተጠራው የ24 ሰአት የአደባባይ የአዳር ተቃውሞ
ሰልፍ ላይ በመገኘት ተቃውሞቸውን ለማሰማት በተንቀሳቀሱ ዜጎች ላይ የወያኔ የፀጥታና የፖሊስ
ኃይሎች ያደረሱት አፈናና አሰቃቂ ድብደባዎች ሁሉም ሰላም ወዳድና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች
በሙሉ በጥብቅ ሊያወግዙት የሚገባ ነው። የዚህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት ሰላማዊ የተቃውሞ
እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ዜጎች ላይ ቀደም ብሎም የደረሰና ወደፊትም ሊደርስ የሚችል መሆኑ
የሚታወቅ ቢሆንም በምንም አይነት መንገድ ይህ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።
ከስፍራው የደረሰን ዜና እንደሚያመላክተው የተቃውሞ ስብሰባውን ያዘጋጁ የተቃዋሚ ድርጅቶች
አመራር አባሎች እንዲሁም ተቃውሟቸውን ለማሰማት በሥፍራው የተገኙ በርካታ ዜጎችና
የመንገዱ አላፊ የሆኑ ንፁሃን ሳይቀሩ በጅምላ ፍፁማዊ ጭካኔ በተሞላበት ሁናቴ በሰደፍና በቆመጥ
ተደብድበዋል፤ ለእስርም ተዳርገዋል።
እንደ ወትሮው ሁሉ ይህ የወያኔ አረመኔያዊ እርምጃ ነፃነት በልመና የማትገኝ መሆኑን ያረጋገጠ
ብቻ ሳይሆን የወያኔ አገዛዝ በሕዝባዊ ትግል ከሥልጣን እስካልተወገደ ድረስ ቀጣይ ሊሆን
እንደሚችልም በግልፅ ያሳየ ነው። ይህ የትላንትናው ድርጊት ቀደም ባሉ አመታት በመጥፎ
ገፅታዎቻቸው በሕሊናችን ውስጥ የተቀረጹትንና በወያኔ አገዛዝ አማካኝነት የተወሰዱት አረመኔያዊና
አሰቃቂ የሆኑ ድርጊቶች በሕዝባችን መንፍስ ውስጥ የለቀቁትን ሰቀቀን ሁሉ የሚያስታውሰን ነው።
ለዚህም ነው ይህንን ድርጊት በቸልታ ልናልፈው የማይገባን።
ውሸትን በመደጋገም እውነት ይገኛል በማለት ላለፉት 22 አመታት ከንቱ ጥረት በማድረግ ላይ
የሚገኘው የወያኔ አገዛዝ የሕዝቡን ዴሞክራሲዊና ሰብአዊ መብቶች መቼም ቢሆን መቼ በተግባር
ሊያረጋግጥ እንደማይቻለው ይህ የትላንትናው ድርጊቱ እንዳለፉት ሁሉ በራሱ ላይ
መስክረውበታል። በሕዝብ ልቦና ውስጥ ተቀባይነት ያጣና ምንም አይነት ሕዝባዊ ድጋፍ የሌለው
መሆኑም የተረጋገጠበትና ለከፋ ውግዘትም የዳረገው እንደሆነ ግልፅ ነው። ኢሕአፓ ይህንን
ድርጊቱን አጥብቆ በማውገዝ የታሰሩት የድርጅት አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች
በአስቸኳይ እንዲፈቱ፡ ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት እንዲደርሳቸው
ይጠይቃል። እንዲሁም ስልፉ የተደረገበት ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ሳይቋረጥ ትግሉ
መቀጠል ያለበት መሆኑንም ያስገነዝባል።
የወያኔ አገዛዝን ከሥልጣን በሕዝባዊ ትግል በማስወገድ፡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርአት
ለመገንባት ይቻል ዘንድ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ኃይሎች ትብብር
ከምንጊዜውም በበለጠ ሁናቴው እየጠየቀ ያለበት መሆኑን ተገንዝበው ከዴሞክራት ኃይሎች ጉያ
በመሸጎጥ ትግሉን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ክፍሎችን በመታገልና በማስወገድ ለዚህ ቅዱስ አላማ
ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጡ ኢሕ አፓ በዚህ አጋጣሚ የከበረ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !
በጋራ ትግላችን የወያኔ አገዛዝ ይወገዳል።
http://www.assimba.org/Articles/EPRP_Pressrelease%20Dec7_2014.pdf
No comments:
Post a Comment