Wednesday, December 24, 2014

መንግስት ተጠለፈብኝ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሔሊኮፕተር አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ

መንግስት ሄሊኮፕተሬ ተጠለፍብኝ ካለ በኋላ ሪፖርተር ጋዜጣም ዛሬ የሚከተለውን ዜና አስነብቧል:: ለግንዛቤ ይረዳዎታል ያንብቡት::


የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንብረት የሆነ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ባለፈው ዓርብ ተጠልፎ ኤርትራ ግዛት አሰብ ማረፉ ተረጋገጠ፡፡ የዘወትር የበረራ ልምምድ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሩሲያ ሠራሽ ኤምአይ 35 ተዋጊ ሔሊኮፕተር ይዞ ወደ ኤርትራ የኮበለለው ዋና አብራሪ ሻምበል ሳሙኤል ግደይ፣ ይህንን ዓይነት ተግባር ይፈጽማል ብለው እንደማያስቡ ባልደረቦቹ ገልጸዋል፡፡

ከሻምበል ሳሙኤል ጋር በኢትዮጵያ አየር ኃይል አብረው የሠለጠኑና የሠሩ የሥራ ባልደረቦቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግለሰቡ መልካም ባህሪ ያለውና በፖለቲካ አቋሙ ገለልተኛ የሚባል ነው፡፡ ‹‹እጅግ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚ አልነበረም፡፡ ራሱን ከፖለቲካ ጉዳዮች የሚያገል፣ ሥራውን ብቻ የሚሠራና ልጆቹን በኃላፊነት የሚያሳድግ ሰው ነበር፤›› ብለው በድርጊቱ ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በትንሽ ነገር የሚከፋና የሚደሰት፣ በቅጽበት የሚለዋወጥ ባህሪ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በግል ሕይወቱም የሚበሳጭበት ጉዳይ እንደነበርና አልፎ አልፎም በዚሁ ጉዳይ ይደበት እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ ሻምበል ሳሙኤል ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል የገባው በ1994 ዓ.ም. ሲሆን፣ የቅጥር ውል የፈረመው በታህሳስ ወር 1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ለ12 ዓመታት አገልግሏል፡፡ በ2003 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ወደ ዳርፉር ሱዳን ያሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል በመሆን ለአንድ ዓመት ያህል እንዳገለገለና በዚያም ተልዕኮ ዳጐስ ያለ ዶላር ይዞ መመለሱን ባልደረቦቹ ተናግረዋል፡፡

ሻምበል ሳሙኤል ተወልዶ ያደገው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ መሆኑን፣ ወላጆቹ የመቀሌ ነዋሪ መሆናቸውን ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ቢሾፍቱ እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለፈው ዓርብ ማለዳ ከረዳት አብራሪው መቶ አለቃ ቢልልኝ ደሳለኝና የበረራ ቴክኒሺያን ፀጋ ብርሃን ግደይ ጋር በኤምአይ 35 ተዋጊ ሔሊኮፕተር የዘወትር የልምምድ በረራ ለማድረግ ከጠዋቱ 2፡35 ሰዓት ድሬዳዋ ከሚገኘው የአየር ኃይል ቤዝ እንደተነሱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዋና አብራሪው ከአጭር ጊዜ በረራ በኋላ የበረራ ከፍታውን በመቀነስ ወደ ኤርትራ በማቅናት ሔሊኮፕተሩን አሰብ ማሳረፉን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ ተዋጊ ሔሊኮፕተሩን ዋና አብራሪው ይዞ ወደ ኤርትራ መኮብለሉን አምኗል፡፡ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ዋና አብራሪው ቴክኒሺያኑንና ረዳት አብራሪውን በማስገደድ ኤርትራ ማረፉን አስታውቋል፡፡

ሔሊኮፕተሩ ባለፈው ዓርብ ከጠዋቱ 2፡35 ሰዓት ጀምሮ በመደበኛ የሥልጠና ልምምድ ላይ እንደነበር ጠቅሶ፣ ሔሊኮፕተሩ ከግንኙነት ውጪ በመሆኑ ሠራዊቱ በአካባቢው ማኅበረሰብና አጋሮች ለተከታታይ ቀናት ፍለጋ ሲደረግለት መቆየቱን አትቷል፡፡

‹‹ሆኖም ሔሊኮፕተሩ በከሀዲው ዋና አብራሪ አማካይነት ቴክኒሻንና ረዳት አብራሪውን በማስገደድ ኤርትራ ማረፉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፤›› ብሏል፡፡ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች ዋና አብራሪው የሔሊኮፕተሩ አዛዥ በመሆኑ የትም ወስዶ ሊያሳርፈው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

‹‹ረዳት አብራሪው ጀማሪ ነው፡፡ የበረራ ቴክኒሺያኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን መከታተል ነው፡፡ ዋና አብራሪው ረዳት አብራሪውና ቴክኒሺያኑ እያወቁም ወይም ያለነሱ ዕውቅና የፈለገበት ወስዶ ሊያሳርፍ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ወር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ጠንከር ባለ ግምገማ ተወጥረው መክረማቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር መትረየስና ተወንጫፊ ሮኬቶች የተገጠሙለት ዘመናዊ ተዋጊ ሔሊኮፕተር ነው፡፡ ከኋላው ስምንት ወታደሮችን ወይም ሁለት የቁስለኛ አልጋዎችን መያዝ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኤምአይ 17 እና ኤምአይ 8 የትራንስፖርት ሔሊኮፕተሮች ሲኖሩት፣ ለውጊያ የሚጠቀምባቸው በደርግ ጊዜ የተገዙ ኤምአይ 24 ሔሊኮፕተሮችን ነበር፡፡

 በግንቦት 1990 ዓ.ም. የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር አሥር ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተሮች የተገዙ ሲሆን፣ በጦርነቱ ወቅት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

የ1997 ዓ.ም. ሦስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ተከትሎ የተነሳውን ግርግር ተከትሎ ሁለት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች (ሻምበል አብዮት እና ሻምበል በኃይሉ) አንድ ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር ይዘው ወደ ጐረቤት አገር ጂቡቲ መኮብለላቸው ይታወሳል፡፡

ብዙም ሳይቆይ የጂቡቲ መንግሥት አብራሪዎቹን አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጠ ሲሆን ሔሊኮፕተሩንም መልሷል፡፡

 አብራሪዎቹ የጦር ፍርድ ቤት ቀርበው በአሁኑ ወቅት በእስር እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ ወቅት በቤላሩስ በሥልጠና ላይ የነበሩ ሰባት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኤስዩ 27 ተዋጊ ጀት አብራሪዎች ከድተው ጥገኝነት መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ አብራሪዎቹ በተለያዩ የምዕራብ አገሮች ጥገኝነት ማግኘታቸው ይነገራል፡፡

ቀደም ሲል ሻምበል ተሾመ ተንኮሉ የተባለ የአየር ኃይል ባልደረባ በ1995 ዓ.ም. ኤል 39 የተሰኘ የመለማመጃና ቀላል የውጊያ አውሮፕላን ለልምምድ በረራ ከመቀሌ ቤዝ ይዞ እንደተነሳ ወደ ኤርትራ ኮብልሎ ነበር፡፡


እስከ ማክሰኞ ታኅሳስ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የኤርትራ መንግሥት ስለተጠለፈው ኤምአይ 35 ሔሊኮፕተር ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጠም፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37480

No comments:

Post a Comment