Wednesday, December 24, 2014

በነ ሀብታሙ አያሌው የክስ ጉዳይ የተሰየመው ችሎት ‹አስገራሚ› ውሎ፣ ተከሳሾቹ ‹‹ዘረፋ›› ተፈጽሞብናል ብለዋል

December 24, 2014

∙ተከሳሾቹ ‹‹ዘረፋ›› ተፈጽሞብናል ብለዋል !! ∙‹‹ለማን አቤት ይባላል?›› ሀብታሙ አያሌው
ዛሬ ታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር፡፡ የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ተሟልተው ፍርድ ቤት ተገኝተዋል፡፡

ችሎቱ የተሰየመው ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ተከሳሾች በቀረበባቸው የሽብር ክስ ላይ የሰጡትን መልስ በተመለከተ 7ኛ ተከሳሽ መልስ በዕለቱ ባለማቅረባቸው አሟልተው እንዲቀርቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ስለነበር ይህን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ማብራሪያውን ለመስማት ነበር፡፡

የተከሳሾች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች በጥየቃ ወቅት በተለየ መዝገብ ይመዘገባሉ የተባለውን አቤቱታ በተመለከተ፣ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደብዳቤ መልስ መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ‹‹ማረሚያ ቤቱ በሰጠው መልስ እስረኞች ከሌሎች በተለየ የደረሰባቸው ችግር የለም›› ማለቱን ገልጾ ይህንኑ መልስ ሙሉ ለሙሉ መቀበሉን አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በዛሬው የችሎቱ ውሎ ላይ ተከሳሾች ለየት ያለ አቤቱታ በጠበቆቻቸው በኩል አቅርበዋል፡፡ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ለችሎቱ እንዳስረዱት ደንበኞቻቸው ከሌሎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ አቶ ተማም አባቡልጉ በታህሳስ 12 ለ13 ቀን 2007 ዓ.ም አጥቢያ ሌሊት ስምንት ሰዓት ጀምሮ ደንበኞቻቸው ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ የግል ማስታወሻዎቻቸው፣ ገንዘብ እና በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ እያዘጋጁት የነበረው መቃወሚያና መከራከሪያ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹ደንበኞቼ ላይ እየተደረገ ያለው ጉዳይ ለህይወታቸውም የሚያሰጋቸው ነው፡፡ በማረሚያ ቤቱ በሌሊት ፍተሻ ያደረጉባቸው ሰዎች ቀደም ሲል በምርመራ ወቅት ‹ህገ-ወጥ› ተግባራት ሲፈጽሙባቸው የነበሩ የፌደራል ፖሊስና የደህንነት አባላት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች ደንበኞቼ ያውቋቸዋል፡፡ ስለሆነም ፍተሻው የተከናወነው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አልነበረም ማለት ነው፡፡ 
ድርጊቱ የተፈጸመው የተለየ የስም ዝርዝር ተይዞ ከሌሎች በተለየ መልኩ ነው፡፡ ለአብነት ደንበኞቼ አቶ አብርሃ ደስታና በሌላ የክስ መዝገብ የተከሰሰው አብዱራዛቅ አክመድ ላይ የሆነው ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ነው፡፡ ፍተሻው ስለት ነገር አልያም ሌላ ህገ-ወጥ ቁሳቁስ ለመያዝ የተደረገ አለመሆኑን ከተወሰዱት ንብረቶች ማየት ይቻላል›› ሲሉ አቶ ተማም ለፍርድ ቤቱ በደንበኞቻቸው ላይ የተፈጸመውን ድርጊት አስረድተዋል፡፡

ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ‹‹ማረሚያ ቤቱ መንግስት ዜጎች ታንጸው እንዲወጡ ያሰራው ነው፡፡ ይህን አሰራር ለመጠበቅም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ ስራዎችን ሊሰራ ይችላል፡፡ እየቀረበ ያለው አቤቱታም ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ነው›› ብለዋል፡፡

ጠበቃ ተማም የደንበኞቻቸውን አቤቱታ ከህግ አንጻር ያስረዱ ሲሆን፣ ‹‹በመሰረቱ ፍተሻ ሊካሄድ መቻሉ ላይ አይደለም አቤቱታው፡፡ የተካሄደው ፍተሻ ግን ህገ-ወጥ ነው፤ ምክንያቱም ፍተሻው የተከናወነበት ሰዓት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ሳይሆን ሌሊት 8 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ይህ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ፍተሻው በማረሚያ ቤቱ ፖሊሶች አይደለም የተከናወነው፡፡ በደህንነቶችና የፌደራል ፖሊሶች ነው ፍተሻው የተደረገው፡፡ ይህም ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ብቃቱ እንደሌለው ያሳያል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ይህን መሰል ድርጊት የፈጸሙት አካላትና በማን ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ምርመራ እንዲካሄድ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡

ጠበቃ ተማም በተጨማሪ ከደንበኞቻቸው ላይ በፍተሻው ወቅት የተወሰዱባቸው ንብረቶችና ማስታወሻዎች እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ‹‹የተለየ ከፍተኛ በደል ደርሶብኛል›› በሚል ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው የነበሩት 3ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የጠየቁት የመናገር እድል ሳይፈቀድላቸው ቀርቷል፡፡

በጠበቆቹ አማካኝነት የቀረበው አቤቱታን በተመለከተ ችሎቱ አስተያየት የሰጠ ሲሆን በተለይ ጠበቃ ተማም አቤቱታውን ባቀረቡበት ወቅት ‹‹ማረሚያ ቤቱ ደንበኞቼን ለመጠበቅ ፍላጎትም ብቃትም የለውም›› ያሉት አገላለጽ ተገቢ ስላልሆነ እንዲታረሙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በቃል የገለጹት የመሐል ዳኛው፣ ‹‹እንዲህ አይነት አገላለጽ ማረሚያ ቤቱ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋ እንዳይሆን…›› በማለት ሌላ አስገራሚ መነጋገሪያ ከፍተዋል፡፡

ይህን የዳኛውን ንግግር ተከትሎ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ሀብታሙ አያሌው የመናገር እድል ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ ለአጭር ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡ እናም፣ ‹‹እርስዎ እያሉት ያለው ነገር ተገቢ አይደለም፡፡ በህይወቴ ላይ የደህንነት ስጋት አለብኝ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ይህንን ስጋቴን ለችሎት እያስረዳሁ ነው፡፡ ግን እርስዎ ‹የበቀል እርምጃ› እንዲወሰድብን ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ በእርግጥ አሁንም የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድብን ማረጋገጫ የለንም፡፡ እሺ ለማን አቤት ይባላል? የደረሰብንን በደል ለፍርድ ቤት ከማስረዳት ውጭ ለማን አቤት እንላለን….አሁን እኮ ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤቱ ጋር መወገኑን ነው እያየን ያለነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የእኛን አቤቱታ እየሰማ አይደለም፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ ለማን አቤት እንበል?›› ሲል አቤቱታውን በስሜት ውስጥ ሆኖ አስረድቷል፡፡

የሀብታሙን ንግግር አዳምጠው አንደኛ ዳኛ ‹‹እኛ ሳንሆን ህጉ ነው ይህን እንድንል የሚያደርገን›› በማለት አጭር መልስ ሰጥተዋል፡፡


በዚህ መልኩ ቀጥሎ የዋለው ችሎት በተከሳሾች በኩል የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ፍርድ ቤቱ ይህን ጉዳይ የማየት ስልጣን አለው ወይስ የለውም በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት፣ እና መደበኛ ክሱን ለማየት ለታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተጥቷል፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/37482

No comments:

Post a Comment