በዛ ጉዞ ከነበረን ትዝታ ውስጥ ፈፅሞ የማይረሳን አርበኞች ግንባር ፈፀማቸው የሚባሉት ጀብዱዎች እና የአካባቢው ህዝብ ለግንባሩ የነበረው አድናቆት እና ፍቅር ነበር፡፡ ቦታው አርበኞች ግንባር አባላት ሲመቻቸው መሳሪቸውን ሳይመቻቸው ደግሞ ቀበቷቸውን ታጥቀው የሚንጎማለሉባት ስርፋ ነበረች፡፡
በአካባቢው ከሱዳን ጋር ስላለን ድንበር ጉዳይ ከመተማ ወደ ውስጥ ገብተው ያሚገኙ ገበሬዎች ጥቂት ጥቂት አጫውተውኛል፡፡
በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ድንበር ሰፊ አውላላ ሜዳ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ሲናገሩ እንደሰማነው ሁለት አይነት ድንበር አለ አንደኛው መንግስት የሚያውቀው ሌላኛው ደግሞ ህዝቡ የሚያውቀው ነው፤ እንደ ፕሮፍ አባባል …ህዝቡ ይሄ ነው ሀገሬ የሚለው እና መንግስት ይሄ ነው ካርታዬ የሚለው አንዳንዴ ይለያያል አንዳንዴ ደግሞ ይመሳሰላል፡፡
የአካባቢው ገበሬዎች ስለ ድንበሩ አካባቢ ሲያወሩ አካባቢው ለዘመናት ሲጋደሉበት የነበረ አካባቢ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የመጋደሉ መነሾ ጎንደሮች የዘሩትን የሱዳን አርብቶ አደሮች በከብት ሲያሳጭዱት በሚነሳ ግጭት መሆኑን ስሙን የዘነጋሁት ገበሬ አውግቶኝ ነበር፡፡ ገበሬው እንደነገረኝ አካባቢው ላይ ሱዳኖችም የእኛ እኛም የእኛ የምንለው ሰፊ መሬት አለ እኛ እህል እንዘራበታለን እንርሱ ደግሞ ከብት ይዘሩበታል፡፡ በዚህም የተነሳ የሀገሬ ገበሬ እና የጎረቤታችን አርብቶ አደር ማዶ ለማዶ ሆነው ይታኮሳሉ፤ ይጋደላሉም፡፡
ባለፈው ጊዜ አንድ የሱዳን ድረ ገፅ ጽፎት አንዱ ወዳጄ ደግሞ አጋርቶን እንዳየሁት ሱዳኖች ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ግጭት ደጋግሞ ሲከሰት የነበረበት አካባቢ ችግር መፈታቱን ጽፈዋል፡፡ አክለውም በአካባቢው ላይ መንግስታቸው ወደ አስራ ሰባት መንደሮችን ሊያሰፍር እቅድ መያዙን አውርተዋል፡፡
ማን መሬት ላይ ማን ይሰፍራል… ይሄ በውል አለየም፡፡ ሰዳኖች የገዛ መሬታቸው ላይ ነው ይሄንን መንደርተና ሊያሰፍሩ ያቀዱት ወይስ የገዛ አውላላ ሜዳቸውን ሊስጠብቁ ነው… (ትላንት ስለ ፕሮፍ ስናወራ ያነሳነውም ይሄንኑ ነው)
የሀገሬ ሰዎች መሬታቸው ላይ እንኳንስ መንደር መስርተውባቸው ይቅርና ሳሬ ላይ ከብት ተለቀቀ ብለው የሚታኮሱ ናቸው፡፡ መንግስታችን በአካባቢው ላይ ያለውን እንደ አርበኞች ግንባር የመሳሰሉ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር ሲል መሬቱን ለሱዳኖች “እንሆ በረከት” ሊል አይችልም ብሎ የሚከራከር ካለ እርሱ ኢህአዴግ መስተፋቅር ያሰራችበት ምስኪን አፍቃሪዋ ብቻ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን መንግስት አይምሮውን ጨለፍ አድርጎት መሬቱን ለመስጠት ሲስማማ የአካባቢው ገበሬዎች የሚያስቀምሱ ናቸው ብሎ ማሰብም ከባድ ነው፡፡
ትልቁ ቁምነገር መንግስት እንዲህ አይነት ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሲያደርግ ለህዝቡ ግልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ገንዘብ ሲቸገር ብቻ ቦንድ ግዙልኝ ብሎ ወደ ህዝቡ መምጣት ከመንግስትነት ወደ የኔብጤነት ዝቅ የሚደርግ አሰራር ነው!
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/12407
No comments:
Post a Comment