Thursday, June 11, 2015

በቴፒው ግጭት በርካታ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ መሆናቸውን መረጃዎች አመለከቱ

ሰሞኑን የቴፒ ወጣቶች ቡድን በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ የወሰደውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ ሶስት ፖሊሶች ከተገደሉና በርካታ እስረኞች ካመለጡ በሁዋላ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት

ታጣቂዎች መሽገውበታል ወዳለው አካባቢ በመሄድ ውጊያ የከፈቱ ሲሆን፣ ወጣት ታጣቂዎች አስቀድመው ዝግጅት አድርገው በመቆየታቸው በርካታ ወታደሮች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።


የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት በርካታ ወታደሮች ሙትና ቁስለኛ ሲሆኑ፣ ቀላል የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸው በአማን ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ፣ ከባድ ቁስለኞችና ሟቾች ደግሞ በሄሊኮፕተር ተወስደዋል። መካለከያ ሰራዊቱ የደረሰበትን ጉዳት ከህዝብ ለመደበቅ አማን ሆስፒታልን በልዩ ሁኔታ ሲያስጠብቅ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል። የመከላከያው አዛዥ መገደሉንም ምንጮች አክለዋል።

በደረሰው ጉዳት የተበሳጩት ወታደሮች የቡድኑን ታዋቂ ተዋጊ የሆነውን ተካ ጣመን ከገደሉ በሁዋላ አስከሬኑን መንገድ ላይ እየጎተቱ መንገድ ላይ ጥለውታል።


ለሟቹ አድናቆታቸውን ወይም ሀዘናቸውን ሲገልጹ ታይተዋል የተባሉ የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ተይዘው መታሰራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል። ሮዛ ሙራ የተባለች ነዋሪ “ጀግና ሞተ” በማለት በመናገሩዋ ወደ እስር ቤት የተወሰደች ሲሆን፣ ከሁለት
ቀን እስር በሁዋላ በማስጠንቀቂያ ተለቃለች። ሌሎች ነዋሪዎች ግን አሁንም በእስር ላይ ናቸው።


ከግጭቱ በሁዋላ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አዝመራውና እና የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሾሎ ከግጭቱ ጀርባ እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው በቁም እስር ላይ ናቸው። ወታደሮች ከታጣቂዎች ጀርባ አሉ ያላቸውን ባለስልጣናት ለመያዝ
እየተወያዩ ነው።


ባለፉት 3 ቀናት ተጨማሪ ወታደር ወደ አካባቢው የተላከ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች የላኩት ማስጠንቀቂያ ነዋሪዎች እጅ መግባቱንና መነጋጋሪያ መሆኑንም የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።


መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር በአካባቢው ያሰፈረ ሲሆን፣ ውጥረቱ አሁንም እንዳለ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።


የቴፒ ወጣቶች የመብት ጥያቄዎችን ካነሱ ከአንድ አመት በላይ ሆኖአቸዋል። የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና እስር ቤት ሰብረው እስረኞች እንዲጠፉ ያስደረጉ 5 ሽፍቶች ተገድለዋል በማለት ዘግቧል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው 2
አባሎቻቸው መገደላቸውንና በመንግስት በኩል ደግሞ 33 ወታደሮች መሞታቸውን ይናገራሉ።


http://satenaw.com/amharic/archives/7653

No comments:

Post a Comment