Friday, June 26, 2015

ራሱ እግር እግሩ ራስ የሆነበት፣ በአፍጢሙ የተደፋ የሕግ ስርዓት (በወይንሸት ሞላ ዙሪያ)

ላይ ላዩን ስናየው የጨለመ ቢመስለንም በርግጥ የኢትዮጵያ ትንሳኤ መድረሱን የሚያመላክቱ ብዙ ምልክቶች እያታዩ ነው። ከነዚህ ምልክቶች መካከል በዋናነት ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ፣ የሚገርሙ፣ የሚያስደንቁና ወኔ የሞላባቸው ጀግና ልጆች እየተፈጠሩ መሆናቸው ነው።
ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ስለ አሁኑ የለዉጥ ፈላጊ ትዉልድ ሳስብ፣ በፊቴ የሚደቀኑ እጅግ ወገኖች በጣም ብዙ ናቸው። ከነዚህ ወገኖች መካከል ዛሬ ስለ አንዲት እህት እጽፋለሁ። ከፍተኛ የሆነ የዘረኛው ህወሃት አገዛዝ ዱላ ያረፍባት። ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ፣ ከአንድ አመት በፊት “የማታውቋት ካላችሁ፣ በሰውነት ‹‹ቀጫጫ ነች›› ብዬ ብነግራችሁ አልተሳሳትኩም፡፡ ግን ጥንካሬዋ ይገርመኝ ነበር” ሲል የጻፈላት።


                       ወይንሸት ሞላ
ቀኑ የካቲት 30 2006 ዓ.ም ነው። እሑድ ቀን ። የሴቶች የ5000 ሩጫ ተዘጋጅቷል። በርካቶች ይሮጣሉ። ቢጫ ኬኔቴራ ለብሰዋል። ሩጫዉ እንደተጀመረ ድምጾች መሰማት ጀመሩ። የስድብ፣ የክፉ አይደለም። «የጣይቱ ልጆችን ነን፤ የሚኒሊክ ልጆች ነን፣ ለነጻነት ነው የምንሮጠዉ፣ እርቦናል፣ መብታችን ይከበር፣ የታስሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ …» የሚሉ ድምጾች። በሌሎች ሯጮች ላይ ጠጠር አልተወረወረም። የወደመ ንብረት የለም። መንገዶች አልተዘጉም። ሩጫዉ አልተስተጓጎለም። በሰላም ተጀመሮ በሰላም ነው ያለቀው። ሆኖም ሕወሃቶች ተቆጡ። ሕግ አክብረው፣ ሕግ ምንግስቱ የሚፈቅድላቸውን መብት ተጠቅመው ሰላማዊ የነጻነት ድምጾችን ያሰሙት ወጣት ሴቶችን ያዟቸው። ለሶስት ሳምንታት አስረው ከፍተኛ ግፍ ፈጸሙባቸው። እነዚህ ልጆች የጣይቱ ልጆች ተብለው ይታወቃሉ። ከነዚህ መካከል አንዷ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆነችው፣ ወይንሸት ሞላ ናት 

ብዙም አልቆየም፣ በአኑዋር መስኪድ አካባቢ በዚያ ሙስሊሞች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመታዘብ ወይንሸት በሄደችበት ጊዜ፣ እንደገና ፖሊሶች ይይዟታል። ከፍተኛ ድብደባ ይፈጽሙባታል። ጭንቅላቷ በደብደባ ተጎድቶ የተሰፋ ሲሆን፣ የቀኝ እጇን ቀጥቅጥው ሰብረዉታል። አዚዛ መሃመድ ከምትባል የአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ ፎቶ ግራፍ አንሺ ጋር, ፍርድ ቤት ትቀርባለች። ብዙ ሰቃይ ለሳምንታት ከተቀበለች በኋላ እንደገና ትፈታለች።

በአዲስ አበባ ከፍተኛ ተቃዉሞ በቀረበት በሚያዚያ 14 ቀን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ( 8 AM ) ፣ ኢያስፔድ ተስፋዬ ከሚባል የሰማያዊ ከፍተኛ አመራር ጋር በስልክ ታወራለች። ያኔ ፖሊሶች አሁን ይይዟታል። ኢያስፔድ ለአንድ ለአመራር አባላቱ ወይንሸት መታሰሯን ያሳውቃል። በሶሻል ሜዲያም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ( 9 AM) ይለጥፋል። ሌላ የሰማያዊ አመራር አቶ ወሮታው ዋሴ ወዲያው በሶስት ሰዓት ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሯን ያረጋግጣል።

የሕወሃት ፖሊሶች ወይንሽትን ጨምሮ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ማስተዋል ፍቃዱ እና ቤተልሄም አካለወርቅ የተባሉ የሰማያዊ አባላትን ብዙ ካንገላቱ በኋላ ፍርድ ቤት ያቀርቧቸዋል። “አራት ሰዓት ተኩል ላይ መስቀል አደባባይ ሲበጥብጡ ያዝናቸው” የሚል ክስ ይመሰርታሉ። ወይንሸት የተያዘችው ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት በሌላ ቦታ፤ ፖሊስ ግን በሌሎች እስረኞች ማድረግ እንደለመደው የዉሽትና የፈጠራ ክሱን አዥጎደጎደው። እንደው ተሳስትው እዉነት መናገር የማይችሉ ፍጥረቶች !!!
እነ ወይንሸት ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት፣ ተያዙ በተባሉበት ወቅት መስቀል አደባባይ ላይ እንዳልነበሩ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ያሰማሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ወረታው ዋሴን እና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ወጣት እያስፔድ ተስፋዬን በመከላከያ ምስክርነት ወይንሸት አቀረበች፡፡ ሌሎችም እስረኞች እንደዚሁ በቦታው በተባለው ወቅት እንዳልነበሩ ምስክር አቀርቡ። ፍርድ ቤቱ ለዉሳኔ ሰኔ 15 ቀን ቀጠሮ ይሰጣል። ሰኔ 15 ቀን፣ “የወንይሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤትሄልየም አካለ ወርቅ የመከላከያ ምስክሮች ተከሳሾቹ በቦታው እንዳልነበሩና ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ አላስረዱም በሚል” ፍርድ ቤቱ ጥፋተኞች ይላቸዋል። የተከሰሱበት ወንጀል እስከ 6 ወር እንደሚያስቀጣ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ እነ ወይንሸት ሞላ የሁለት ወር እስር ፈርዶባቸው፣ የታሰሩት ከሚያዝያ 14/ 2007 ጀምሮ ሁለት ወር ከአንድ ቀን ስለሆነ ከ እስር እንዲፈቱ ይወስናል።

አቅቢ ህግ ዜጎችን ሲከስ፣ ወንጀል ስለመስራቱ መረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ሆኖም በአገራችን ያለው የፍርድ ሂደት ዜጎች ሲታሰሩ ጥፋተኛ የሚባሉት፣ አቃቤ ሕግ ጥፋት ስለመፈጸማቸው በቂ ማስረጃ ሲያቀርብ ሳይሆን፣ ተከሳሾች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን መረጃ ሲያቀርቡ ነው። ራሱ እግር ፣ እግሩ ራስ የሆነበት ፣ በአፍጢሙ የተደፋ የሕግ ስርዓት !!!!!
የአገራችችን አሰቂኝና አሳፋሪ የሕግ ስርዓት ድራማ እዚህ ላይ አላበቃም። ሰኔ 15 ቀን ቄራ የሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲፈቱ ትእዛዝ ቢሰጥም የሕወሃት ፖሊሶች እንደገና የፍርድ ቤትን ትእዛዝ ጨፈለቁ። በነጋታው፣ ስኔ 16 ቀን፣ እነ ወይንሸት ሞላን እንደ ወንበዴ፣ የፍርድ ቤት መዛዣ ሳይዙ አፍነው ወሰዱ።

እንግዲህ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይችን ትመስላለች። ኢትዮጵያዉያንን ልብን በሚያደማ ሁኔታ ፣ ስልጣኔ ባልገባቸው፣ በቂምና በጥላቻ በተሞሉ ፣ ከጫካ አስተሳሰብ ባልተላቀቁ፣ ፍጹም ኋላ ቀርና ዓዉሬ በሆኑ ዘረኞች፣ አንገታችቸው ደፍተው፣ ፈርተዉ፣ ተሽማቀውና ተዋርደው፣ ጥቅሮች በአፓርታይድ ዘመን ይኖሩ እንደነበረው በባርነት የሚኖሩባት አገር !!!

ደግነቱ ግን ባርነት፣ ጭቆና በቃን ብለልው የተነሱ በብዛት ያሉበት፣ ትዉልድ ነው የአሁኑ ትዉልድ። “በሀገራችን፣ ብዙ እንስቶቻችን በፍርሃት ወጥመድ ሥር ወድቀው፣ በጣም ልስልስ የሆነ የህይወትን መስመርን ምርጫቸው አድርገውና ‹‹ፖለቲካን በሩቁ!›› በሚል መሪ ቃል የዘወትር ድግግሞሻዊ ሕይወት ውስጥ በምርጫ እየተጓዙ ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ፣ እንደወይንሸት አይነት ጥቂቶችን በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ስመለከት እንደኢትዮጵዊ ዜጋ ደስታን ይፈጥርብኝ ነበር” ሲል እንደጻፈው ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ፣ እኔም እንደ ወይንሸት ያሉ ፣ ብረትና ታንክ የማይፈሩ፣ “ነጻነቴን ከምትወስዱብኝ ሞቴን ስጡኝ” የሚሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየበዙ መምጣታቸው በርግጥ ኢትዮያጵያችን የምትታሰብበት ጊዜ መድረሱን፣ የጨቃኝ፣ ቂመኛ፣ ከፋፋይና ዘረኛ አገዛዝም ፍጻሜ መድረሱን የሚያሳይ ነው።

http://satenaw.com/amharic/archives/8107

No comments:

Post a Comment