Tuesday, June 9, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ – እስርና አፈና የምርጫውን ችግር ሊሸፍን አይችልም!!

ከሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

ገዥው ፓርቲ የ2007 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫን የመንግስትን መዋቅርና ኃብት ያለገደብ በመጠቀም የዜጎችን በነፃነት የመምረጥ መብት በመዋቅር በማፈን አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እጅግ በርካታ ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈፅም ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የለየለት የውንብድና ስራ ተቃውሞ ያላቸው ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን ቅሬታ የሚያባብስ ሊቢያ ውስጥ በስደት ላይ በሚገኙ በኢትዮጵያውያን ላይ አረመኔው የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድን የፈፀመው አሰቃቂ ግድያን አስመልክቶ መንግስት የሰጠው ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ በቋፍ ላይ የነበረውን የሕዝብ ተቃውሞ እንዲገነፍል አድርጎታል፡፡ ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም አረመኔው የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድን በዜጎቻችን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ በራሱ በመንግስት ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችን በእለቱ በአሰቃቂ ሁኔታ በኃይል ከመደብደብና ከማዋከቡም በተጨማሪ ይህንን ተቃውሞ አነሳስተውብኛል ብሎ ያሰባቸውን በቦታው ያልተገኙ ዜጎችን ጨምሮ ስጋት አድርጎ የሚቆጥራቸውን የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና መኢአድ አባላትን እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችን በገፍ አስሯል፡፡ በሐሰት ክስ የታሰሩ ወጣቶችን ከስርዓቱ አፈና ያልተላቀቁት ፍርድ ቤቶች እንኳን በነፃ ሲለቋቸው የገዥው ፓርቲ ደህንነቶች በህገ ውጥ መንገድ እንደገና እያፈኑ አስረዋቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና መኢአድ አባላትን እንዲሁም ሌሎች ወጣቶች በሰልፉ ሰበብ ታስረው በካድሬዎችና ደህንነቶች የሐሰት ምስክርነት እየተወነጀሉ ይገኛሉ፡፡ በሌሎች ላይም ተመሳሳይ ክስና የሐሰት ምስክርነት እየተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ ስርዓቱ በለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ትግሉን ለማዳከም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በሌላ በኩል ምርጫውን በሕገ ወጥ መንገድ ለማሸነፍ ቀድሞ ያሰበው ገዥው ፓርቲ ውጤቱን ተከትሎ ተቃውሞ ሊያስነሱብኝ ይችላሉ ያላቸውን የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና መኢአድ አባላትን ከየክፍለ ሐገሩ አድኖ በማሰር ተቃውሞውን ለማዳፈን እየጣረ ይገኛል፡፡ በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የስርዓቱ ካድሬዎች የሰማያዊ ፓርቲን ፖስተሮች በማባዛት ባልተፈቀዱ ቦታዎች በመለጠፍ ይህንን ያደረጉት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እንደሆኑ በማስመሰል የፓርቲውን ስም ለማጉደፍና አባላቱንም ለማጥቃት ተጠቅመውበታል፡፡ በሕጉ መሰረት ቅስቀሳ ያደረጉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እንዲሁም ዕጩዎች ለእስርና ለድብድብ ተዳርገዋል፡፡ አሁንም በሰልፉ ሰበብና በምርጫው ወቅት ጠንካራ ታዛቢ በመሆናቸው አሊያም በሰላማዊ ትግሉ ስጋት ይሆኑብኛል ያላቸውን በርካታ ወጣቶችን እያሳደደ በማሰር ላይ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ እያለ አሁንም ድረስ በሰማያዊና በሌሎች ፓርቲዎች አባላት እንዲሁም ሌሎች ወጣቶች ላይ ይህን ሁሉ እስር፣ ወከባና በደል እየፈፀመ የሚገኘው በሕዝብ ልብ ውስጥ እንደሌለ፣ በጥርነፋ እና በማጭበርበር አሸነፍኩ ቢልም እውነታው ግን ሕዝብ እንዳልመረጠውና የሕዝብንም ጥያቄ መመለስ እንደማይችል ስለተረዳ ነው፡፡ ይሁንና ይህ አፈናና እስር እስካሁን የተዳፈነውን ምሬት ይበልጡን በማባባስ ሕዝብን ለተቃውሞ ያነሳሳዋል እንጅ የስርዓቱን አጭበርባሪነት ሊሸፍን አይችልም፡፡ ከምንም በላይ ስርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባሰው በሄደ የጭቆና አገዛዝ ህዝብን ለማንበርከክ የሚያደርገው መፍጨርጨር ሐገራችንን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይወስዳት ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል፡፡

በመሆኑም ስርዓቱ የሕዝብን ተቃውሞ ለማዳፈንና የነፃነት ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖችን ቅስም ለመስበር የሚያደርገው መሯሯጥ ብዙ በደልና መገፋትን ተሸክሞ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለበለጠ ትግል እንዲነሳ ያደርገው እንደሆን እንጅ ሊያስቆመው እንደማይችል ሊረዳ ይገባል፡፡ ሕዝብ የደረሰበትን ሸፍጥ በትዕግስት ለማለፍ ቢሞክርም የገዥው ቡድን ተግባር ግን የጦር ጠማኝ ጀብደኝነትና ፀብ አጫሪነት ሐገራችንን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ቢወስዳት ለሚመጣው ጥፋትና አለመረጋጋት ገዥው ቡድን በብቸኝነት ኃላፊነትን የሚወስድ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡

በመጨረሻም በሕገወጥ መንገድ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ አባሎቻችንና ንፁኃን ኢትዮጵያውያን በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቅን በማንአለብኝነት አባሎቻችንን የሚያሳድዱ ካድሬዎችና ሰላዮች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡


ሰኔ 1 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/44162

No comments:

Post a Comment