Friday, September 4, 2015

ሀብታሙ አያሌው ቂሊንጦ እስር ቤት ላይ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

‹‹ችሎቱ ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው›› አቶ ሀብታሙ አያሌው

አቶ ሀብታሙ አያሌው ነሀሴ 14/2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከተከሰሰበት የሽብር ወንጀል ነጻ ነው በማለት ከእስር እንዲፈታ የሰጠው ትዕዛዝ ተከብሮ እንዲፈታ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደርጓል፡፡


ዛሬ ነሀሴ 29/2007 ዓ.ም ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው እና መልስ እንዲሰጥ የተጠራው የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ተወካዮች ሲሆኑ፣ የእስር ቤቱ የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ ሱፐር ኢንቴንደንት ጣዕመ ደምሴ አቶ ሀብታሙ አያሌውን ለምን ከእስር እንዳልለቀቁ አስረድተዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚሉት አቶ ሀብታሙ ከቂሊንጦ እስር ቤት ያልተፈታበት ምክንያት እስር ቤቱ ከአቃቤ ህግ ይግባኝ እንደተጠየቀበት እና ይህን ተከትሎ ተያይዞ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጻፈ የእግድ ትዕዛዝ ስለደረሳቸው ነው፡፡

ሱፐር ኢንቴንደንት ጣዕመ ደምሴ እንደገለጹት የመፈቻ ደብዳቤው እና የእግድ ትዕዛዙ የደረሳቸው ነሀሴ 15/2007 ዓ.ም ሲሆን፣ አቶ ሀብታሙ ግን ከእስር መፈቻ ትዕዛዙ የተጻፈለት ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ነጻ ናችሁ የሚል ብይን በተሰጠበት ዕለት፣ ማለትም ነሀሴ 14/2007 ዓ.ም ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ ሀብታሙ የማስፈቻ ደብዳቤው እንደተጻፈለት ከእስር ሊለቀቅ ይገባ ነበር፡፡ በእርግጥም የማስፈቻ ደብዳቤው በ14/2007 ዓ.ም እንደተጻፈ ነገረ ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች፡፡

በሌላ በኩል አቶ ሀብታሙ አያሌው ይግባኝ እንደተጠየቀበትና የእግድ ትዕዛዝ ለቂሊንጦ እንደተጻፈ በወቅቱ በደብዳቤ ጭምር መረጃ የጠየቀ ቢሆንም እንዳልተነገረው ለተረኛ ችሎቱ አስረድቷል፡፡ በዚህም ቤተሰቦቹ ለእንግልት፣ አቶ ሀብታሙ ደግሞ ለሞራል ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግሯል፡፡ ቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ግን ይህን ባለመቀበል በጊዜው መረጃ መስጠቱን ይከራከራል፡፡

ተረኛ ችሎቱ የቀረበለትን አቤቱታ እና የአስተዳደሩን መልስ ከሰማ በኋላ ቂሊንጦ እስር ቤት ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሰውን ትዕዛዝ እንዳስፈጸመ በመጥቀስ ትክክለኛ ነው ሲል በይኗል፡፡ በመሆኑም አቶ ሀብታሙ አያሌው በእስር ቆይቶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ብይን እንዲጠብቅ ታዝዟል፡፡ አቶ ሀብታሙ የተረኛ ችሎቱን ብይን ከሰማ በኋላ ‹‹ይህ ችሎት ታሪካዊ ስህተት እየሰራ ነው፤ የውሳኔ ግልባጩ ይሰጠኝና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው አደርጋለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡

አቶ ሀብታሙ አያሌው ከሌሎች አራት ተከሳሾች ጋር መስከረም 21/2008 ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46408

No comments:

Post a Comment