Wednesday, September 2, 2015

ኮንቴይነር በተገኘ ቁጥር ‹‹ኢትዮጵያዊ ተደብቋል› ›መባል ተጀምሯል – የ10 ዓመት ታዳጊ ይገኝበታል


በዛምቢያ ሴሬንጄ በተሰኘች ግዛት ፖሊስ 100 ኢትዮጵያዊያንን በመኪና ተጭነው ሲያመሩ መያዙን የአገሪቱ ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

ስደተኞቹ ከናኮንዴ ሳይነሱ እንዳልቀሩ የጠቀሰው ፖሊስ ካኖና በተባለ የፍተሻ ኬላ በመኪናው ላይ በተደረገ ፍተሻ ሰዎቹ ተደብቀው መገኘታቸውን ጠቅሷል፡፡መኪናው በጫነው ኮንቴይነር በዛምቢያ ተወዳጅ የሆነውን ካፔንታ (የደረቀ አሳ) ሲያመላልስ የነበረ መሆኑን ጋዜጣው አውስቷል፡፡


ፖሊስ በናኮንዴ ድንበር አቋርጠው ኢትዮጵያዊያኑ ያለ ህጋዊ ፈቃድ በመግባታቸውና እነርሱን ለማዘዋወር ክፍያ የተፈጸመላቸውን ዛምቢያዊያንን እንደሚከስም ፖሊስ ነገረኝ ያለው ጋዜጣው ዘግቧል፡፡


ሎምቤ ካሙኮሺ ኮሚሽነር ናቸው ለጋዜጣው ‹‹100 ህገ ወጥ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ያሳፈረ መኪና መያዛችንን አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ከእኛ ጋር በመስራት ላይ የሚገኘው የስደተኞች መስሪያ ቤታችን ስደተኞቹን የኢቦላ ምርመራ ያደረገላቸው ሲሆን ሌሎች ምርመራዎችንም እያደረገ ይገኛል››ብለዋል፡፡



ኮሚሽነሩ ህገ ወጥ ያሏቸውን ስደተኞች ያዘዋወሩ ያሏቸውን ሶስት የአገራቸውን ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም አስረድተዋል፡፡ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ከ10 -50 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ የሚበዙት ወጣቶች ናቸው ማለታቸውን ጋዜጣው አስፍሯል፡፡


100ዎቹ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በዛምቢያ ሙኮቤኮ በተባለ ወህኒ ቤት ይገኛሉ ተብሏል፡፡በቅርቡ በሞያሌ ድንበር በማቋረጥ ወደ ኬንያ የገቡ 100 ስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን የአገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ስደተኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማምራት የተንቀሳቀሱ መሆናቸውም ይነገራል፡፡ከኬንያ እስከ ደቡብ አፍሪካ መዳረሻ ያሉ አገራት ኮንቴይነሮችን የጫኑ መኪኖችን በድንበር አካባቢ ሲያገኙ‹‹ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ››በማለት ጠንከር ያለ ፍተሻ ማድረግ መጀመራቸውን በሂደቱ የተሳተፉ ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46364

No comments:

Post a Comment