Saturday, March 16, 2013

በጋምቤላ፤ አሜሪካ የዜጋዋን መቃብር ከፍታ መረመረች



የጋምቤላ “አኬልዳማ” እየተደረሰ ነው
crime scene 1March 16, 2013 05:36 pm 


በጋምቤላ የመከላከያ ሰራዊት ከጨፈጨፋቸው ሰዎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አቶ ኡሞት ኡዶል ግድያ ለማጣራት ከአሜሪካ መንግስት የተላኩት የፎረንሲክ (ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉ) ባለሙያዎችን ጋምቤላ ገብተው የማጣራት ሥራ ጀምረዋል። “የጋምቤላ አኬልዳማ” እየተዘጋጀ እንደሆነም ተሰማ።
የጎልጉል የጋምቤላ መረጃ አቀባዮች እንዳሉት ጋምቤላ የደረሱት የአሜሪካ ዜጎች የሄዱበትን ጉዳይ ለማከናወን ከክልሉና ከመከላከያ ሰራዊት ባለስልጣናት ዘንድ እክል ገጥሟቸው ነበር።
(ፎቶው የማሳያ ነው)
የፎረንሲክ ባለሙያዎቹ የዜጋቸውን አሟሟት መንስኤና የጉዳት መጠን ለማጣራት ጋምቤላ እንደደረሱ አስከሬኑ በስውር የተቀበረበትን ቦታ ማወቅ እንደሚፈልጉ፣ አስከሬኑ ላይ የዲኤንኤ ምርመራ በማካሄድ የሟችን ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥ፣ የጉዳቱን መጠንና በምን ያህል ጥይት እንደተደበደበ ለማጣራት፣ ከዚያም በላይ ለምርመራ ስራቸው ይረዳቸው ዘንድ የሚፈልጉትን መረጃ ለመሰብሰብ ድርጊቱ የተፈጸመበት ቦታ መሄድ እንደሚፈልጉ ጠይቀው እንደነበር ለክልሉ መንግስት ቅርብ የሆኑ ለጎልጉል ገልጸዋል።
ጥያቄውን መቀበል የተሳናቸው የመከላከያና የክልሉ ባለስልጣናት አስከሬኑ መመርመር የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን፣ ከተቀበረ የቆየ በመሆኑ ለማውጣት አስቸጋሪ እንደሆነና እንደማይቻል ለመርማሪዎቹ ገልጸው ነበር። “ስራው የኛ ነው” ያሉት መርማሪዎቹ አስከሬኑ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቢገኝም ማየት እንደሚፈልጉ፣ ይህ አቋም እንደማይቀየር መሆኑን አመልክተው አስከሬኑ የተቀበረበት ቦታ ደርሰው የሚፈልጉትን ምርመራ ማድረጋቸው ታውቋል። አከራካሪ የነበረውና ግድያው የተፈጸመበት ቦታ የመጓዙ ጉዳይ እንደነበር የጠቆሙት የመረጃው ምንጭ፣ የቀረበው መልስ አስገራሚ እንደነበር ይገልጻሉ።
“ቦታው ላይ ደም የለም፣ ማንንም አታገኙም፣ ምን ያደርግላችኋል?” የሚሉ መከራከሪያዎችን ባለሥልጣናቱ  ቢያቀርቡም ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም። አጣሪዎቹ ወደ ስፍራው ከመሄዳቸው በፊት ካድሬዎች ሽማግሌዎችንና ያካባቢው ነዋሪዎችን በማባበል የቅስቀሳና ፊልም የማዘጋጀት ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የጎልጉል ምንጮች አመልክተዋል።
ምንጮቹ እንዳሉት የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማባበል አሳ አስጋሪዎቹ ሲጨፈጨፉ የታሰሩት የቀበሌ ሊቀመንበር ከልጆቻቸው ጋር ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ወጣት ከእስር ነጻ እንዲሆን በተላለፈ ውሳኔ መሰረት ተለቅቋል። ይህ ሁሉ የሚደረገው የአካባቢውን ሽማግሌዎች ለማባበልና “የጋምቤላ አኬልዳማ” በማለት የሚሳለቁበት ዘጋቢ ፊልም በተሳካ ሁኔታ እንዲሰራ ለመቀስቀሻነት ነው።
በጊሎ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኘው አብሌን በማምራት የበጋውን ደረቅ ወቅት ከወንዝ አሳ በማስገርና ያገኙትን በማደን ቀን እየገፉ ሳለ የካቲት 21፤2005ዓም (28/2/13) በድንገት የመከላከያ ሰራዊት ከበባ አካሂዶ ተኩስ በመክፈት አስራ ሁለት የሚጠጉ ንጹሃንን መግደሉን መዘገባችን ይታወሳል። እዚህ ቦታ ደርሶ ማጣራት ማካሄድ የሚፈልጉት የፎረንሲክ ባለሙያዎች ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ወደ ስፍራው አልተነቃነቁም።
አጣሪዎቹ አቶ ኡሞት ከአሜሪካ መቼ ወደ ጋምቤላ እንዳመሩ የሚያረጋግጥ መረጃ አላቸው። ጥርሳቸውን ሲታከሙ ከነበረበት ክሊኒክ የዲኤንኤ መለያቸውን አግኝተዋል። ተጨማሪ አስፈላጊ መረጃዎችም አሏቸው። ስማቸውን የማንጠቅሳቸው ዲፕሎማት እንዳሉት ኢህአዴግ ለመዋሸት የሚችልበት ዕድል የጠበበ ነው።
ሪፖርተር ማርች 6 ቀን 2013 “በጋምቤላ ክልል 29 ሰዎች ግድያ የሚጠረጠረው ግለሰብ ተገደለ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ዜና የፍርድ ቤት ስራ መስራቱ ብዙዎችን እንዳስገረመ የጎልጉል የአሜሪካ ዘጋቢ አስታውቋል፡፡ ስለ ህግና የህግ የበላይነት እከራከራለሁ የሚለው ሪፖርተር ያለ አንዳች የፍርድ ሂደትና ማስረጃ አቶ ኡሞትን አሸባሪ ሰፈር ማሰለፉ የሟቾችን ቤተሰቦች ቅር እንዳሰኘም ታውቋል።
የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤት “Anuak Justice Council – AJC” በሚል ስያሜ የሚታወቀውና ከዘጠኝ ዓመት በፊት ለ424 የአኙዋክ ተወላጆች ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑትን የህወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ለፍርድ ለማቅረብ የሚሠራ ድርጅትና አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው የክልሉ ተወላጆችና ፍትህ ወዳዶች አሜሪካ ለዜጎቿ የምትሰጠውን ክብር ያለማዳላት ለአቶ ኡሞት እንድትሰጥ በ11 የአሜሪካ ጠቅላይግዛቶች ተወካይ የሆኑ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባላትን (ሴናተሮችን) በማነጋገር ግፊታቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ክፍሎች አቶ ኡሞትን ብቻ ሳይሆን ደረቁን የበጋ ወቅት ለማሳለፍ ወደ ወንዝ የወረዱ ንጹሃን በግፍ የተጨፈጨፉበት ምክንያት እንዲጣራ እየጠየቁ እንደሆነም ዘጋቢያችን አመልክቷል።
የማጣራቱ ስራ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለሚደረገው ቀጣይ ተግባርና ራሱ የምርመራው ውጤት ምን እንደሚሆን በቀጣይ ምንጮቻችን እንዳደረሱን እንዘግባለን
    Posted By.Dawit Demelash

No comments:

Post a Comment