ጀርመናዊዉ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በወያኔ ጫና ስራቸዉን ለመልቀቅ መገደዳቸዉ ተሰማ
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን ለረጂም ግዜ በፕሬዚዳንትነት የመሩት ጀርመናዊዉ ፕሮፌሰር ዩኪአም ሄርዚግ ከፍተኛ የወያኔ ባለስልጣኖች በስራቸዉ ላይ ጣልቃ እየገቡ ስላስቸገሯቸዉ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ባስገቡ በሦስት ቀን ዉስጥ መቀሌን ለቅቀዉ ወደ አገራቸዉ መጓዛቸዉን መቀሌ ዉስጥ የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን ከሰሞኑ በላኩልን ዜና ገለጹ። ፕሮፌሰሩ ለምክትል ጠ/ሚነስተር ደመቀ መኮንን ባስገቡት የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ስራቸዉን የሚለቅቁት ባጋጠማቸዉ የጤና ችግር ምክንያት እንደሆነ ቢገልጹም ለመቀሌ ዩኒቨርስቲ ቅርበት ያላቸዉ ብዙ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ፕሮፌሰር ሄርዚግ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በቅርቡ ዩኒቨርሲቲው ዉስጥ በተካሄደ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግምገማ ፕሬዚዳንቱ ሀላፊነታቸዉን አልተወጡም በሚል በተደረገባቸዉ ግፊት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።ፕሮፌሰር ዩኪአም ሄርዚግ ከዚህ ቀደም በሁለት የዩኒቨርስቲዉ ምክትል ፕሬዚዳንቶች አሿሿም ላይ ዩኒቨርሲቲውን በበላይነት ከሚመራው ቦርድ ጋር አለመግባባት መፍጠራቸው የሚታወቅ ሲሆን ሁለቱን ተሿሚዎች በተመለከተ ለቦርዱ የጻፉትን ደብዳቤ በአስቸኳይ እንዲቀለብሱ ማስገደዱ ይታወቃል። አንድ ስማቸዉ እንዳይገለጽ የጠየቁ የዩኒቭርሲቲዉ ከፍተኛ ባለስልጣን ቦርዱ ፕሮፌሰር ሄርዚግ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ያጩዋቸውን ግለሰቦች ሳይቀበልና በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥበት ለሦስት ወራት ያህል ቆይቶ አሁን ግን ሃያ አራት ሰአት በማይሞላ ግዜ ዉስጥ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ለመሾም መቿኮሉ የሚገርመና ግራ የሚያጋባ ነዉ ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ቴድሮስ ሓጎስ ለዩኒቨርስቲዉ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንደገለጹት ፕሬዚዳንት ሄርዚግ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የትራንስፎርሜሽኑን ዕቅድ በሚገባ በስራ አልተገበሩም በሚል እንደሆነ ሲሆን ከእሳቸዉ ሌላ የዩኒቨርሲቲው ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ምክትል ፕሬዚዳንት ወልፍ ቫን ፊርክስንና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ዩአኪም ሌንገርትን ቦርዱ ከኃላፊነታቸው ማንሳቱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ሁለቱም ጀርመናውያን ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያትም የአቅም ማነስና የአፈጻጸም ችግር የሚል መሆኑንም የዩኒቨርሲቲው መምህራን ገልጸዋል፡፡
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment