የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ አደረጉ
የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስላሴ መንፈሰሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ከመጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የትምህርት ማቆም አድማ ላይ እንዳሉ የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፁ፡፡
እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ተማሪዎቹ በአመራር ላይ ያለው አስተዳደር ብቃት የለውም፣ የምግብ አቅርቦትና ጥራት ችግር አለ፤ ምላሽ ግን የሚሰጥም ሆነ ለማነጋገር ፈቃደኛ የሆነ አካል የለም በማለት የኮሌጁ የቀን ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ ለማድረግ ተገደዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለኮሌጁ አስተዳደር ካነሷቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ፣ በኮሌጁ በርካታ ኃይማኖታዊ የአሰተዳደር ችግር እንዳለ ቢጠቅሱም በአስተዳደሩ ምላሽ አለመሰጠቱን ገልፀውልናል፡፡
በነዚህ ምክንያቶች ተማሪዎቹ ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ድረስ ትምህርት እንዳቆሙና አንዳንድ ተማሪዎችም መልቀቂያ (ክሊራንስ) እየሞሉ መውጣታቸውን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የማታ ተማሪዎችም ከሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለኮሌጁ ደህንነት በሚል በአስተዳደሩ ትምህርት እንዲያቋርጡ መደረጋቸውን ተማሪዎቹ ለፍኖተ ነፃነት አረጋግጠዋል፡፡
የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የኮሌጁ ትምህርት የተቋረጠበትን ምክንያትና ተማሪዎቹ አነሷቸው የተባሉትን ጥቄዎች በተመለከተ የኮሌጁን አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ፀሐፊ ብፁዕ አቡነ ህዝቄልን ጠይቀናቸው “ትምህርት መቋረጡን ገና ከእናንተ አሁን መስማቴ ነው፤ የደረሰኝ መረጃ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ምንም እንኳ ከጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ፅህፈት ቤት እስከ ኮሌጁ ድረስ ያለው እርቀት በግምት ከ600 ሜትር ባይበልጥም የቤተክህነቱ ዋና ፀሐፊ ስለትምህርት ማቆም አድማው የሰሙት እንደሌለ ገልፀውልናል፡፡
ይህ መረጃ እስከተዘገበበት መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በኮሌጁ ትምህርት እንዳልተጀመረ አረጋግጠናል፡፡
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment