ለማያዉቅሽ ታጠኚ
ማስረሻ መኮንን ነኝ ከቃሊቲእንደምን ሰነበታችሁ ግንቦቶች - እቺ ደብዳቤዬ እንደምትደርሳችሁ አልጠረጠርም፤ ካልደረሰችም እርግጠኛ ነኝ እናንተዉ ፈልጋችሁ ታገኟታላችሁ። ለመሆኑ እንደምን ከረማችሁ? ዘረኞቹ የወያኔ ካድሬዎች በዚያ ሰሞን ዉጭ አገር ካሉ ሽብርተኞች ጋር ትገናኛለህ ብለዉ ዘብጥያ ወርዉረዉኝ ይሄዉና ሳላናግራችሁ ሳታናግሩኝ ድፍን አንድ አመት አለፈን። መቼም የማይለመድ ነገር የለም መታሰርም ኑሮ ሆኖ ይሄዉና እስር ቤቱን ለመድኩት። ደሞስ የወያኔ እስር ቤት ለምን አይለመድ! ባልታሰር የማላገኛቸዉን ጓደኞቼን፤ ምሁራንንና፤ የእስልምናና የክርስትና እምነት ሊቃዉንትን እዚህ እስር ቤት ዉስጥ ነዉ እንዳሰኘኝ የማገኛቸዉ። ለሁሉም ምን አለፈችሁ ምን አነበብክ፤ ምን ጻፍክ፤ ምን አሰብክ፤ ማንን አሳደርክ እያለ የወያኔ ካድሬ በየቀኑ ከሚጨቀጭቀኝ እዚህ የአገሪቱ ምሁርና አዋቂ የበዛበት እስር ቤት ዉስጥ ብኖር ይሻላል ብዬ አትፍቱኝ ብያቸዋለሁ . . . . . . . የሚሰሙኝ ከሆነ!
ግንቦቶች የዛሬዉ ጉዳዬ የእስር ቤት ኑሮዬን መተረክ አይደለም፤ ጉዳዬ ሌላ ነዉ። ግን ስለ ልጅነት ጓደኛዬ ስለ ታሪኩ ሳልነግራችሁ ባልፍ ቅር ይለኛል። ታሪኩ የወያኔን ፖሊሶች ግልምጫ ከምንም ሳይቆጥር ሁሌ እየመጣ የሚጠይቀኝ የልጅነት ጓደኛዬ ነዉ። ታሪኩ የሚበላ ምግብ ብቻ ሳይሆን የሚነበብ ጸሁፍም ይዞልኝ ይመጣል፤ እኔም የጻፉኩትን ለአንባቢ ያደርስልኛል። የሚገርመዉ ታሪኩ የኮድ ስሙ ሳይሆን እናቱ ያወጡለት ትክክኛ ስሙ ነዉ፤ ስሙን ልደብቅለት ስሞክር . . . ስሜን ይወቁት ምን ያደርጉኛል ብለህ ነዉ . . . . አንተዉጋ ነዉኮ የሚያመጡኝ. . . . . . ደግሞስ በየቀኑ ከምመላለስ አንዱኑ አብሬህ ብታሰር ይሻላል የሚል ቆራጥ ሰዉ ነዉ ታሪኩ።
ጓደኛዬ ታሪኩ በዚህ ሳምንት ይዞልኝ የመጣዉ መጣጥፍ ገና ገልጬ ሳላየዉ ያ እጅ እጅ ያለኝ የኢህአዴግ አርማ ከሩቁ ታየኝና ቀና ብዬ ምነዉ ታሪኩ አልኩት። አንብብ አለኝና ድምጹ ራቀኝ። ምን ሆነ ብዬ ቀና ብዬ ስመለከተዉ ፖሊሶቹ እየገፈታተሩ ከእንግዳ መቀበያዉ ክፍል አስወጡትና ሳይሰናበተኝ ዝም ብሎ ሄደ። እኔም ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁና መጣጥፉን ማንበብ ጀመርኩ። ታሪኩ ሰጥቶኝ የሄደዉ ወረቀት የሚጀምረዉ የኢህአዴግ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ “በመለስ አስተምህሮዎች፤ ጠንካራ ድርጅትና የልማት ሀይሎች ንቅናቄ ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ባህርዳር ዉስጥ ይጀምራል እያለ ነዉ። ወረቀቱ ላይ የሰፈረዉ የዉሸት ብዛት እንኳን እኔን አንባቢዉን ጽሁፉን የተሸከመዉን ግዑዙን ወረቀትም የሚቀፍፈዉ ይመስለኛል። ዮሐንስ ወንጌል ላይ የዉሸቶች ሁሉ አባት የተባለዉ ዲያቢሎስ ትዝ አለኝ። እርግጠኛ ነኝ ወያኔ ያኔ ቢኖር ኖሮ ዉሸት ሌላ አባት ይኖረዉ ነበር። በሦስት ገጾች ተቋጥሮ ከተቀመጠዉ የወያኔ የዉሸት ድሪቶ ዉስጥ አይኔ ያረፈዉ “በመለስ አስተምህሮዎች”፤ “ጠንካራ ድርጅት” ና “የልማት ሀይሎች ንቅናቄ” በሚሉ ሦስት ቱባ ቱባ ዉሸቶች ላይ ነበር። የወያኔዎች ነገር አንዳንዴ በጣም ይገርመኛል። ጥጋባቸዉና ትዕቢታቸዉ ሲፈጠሩ ጀምሮ የተደፈነዉን ጀሯቸዉን ጨምሮ ደፍኖታልና የኢትዮጵያን ህዝብ አይሰሙም እንበል . . . . . . ግን እንዴት የክርስትና እምነታችን መሠረት የሆነዉ ትግራይ አፈር ላይ የበቀሉ ሰዎች ፈጣሪያቸዉን አይሰሙም! እግዚአብሔር እኮ ሃያ አንድ አመት ሙሉ ታግሷቸዉ የገሀዱን አለም የመለስ ዜናዊን አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን የአባ ጳዉሎስን የመንፈሳዊ አለም አስተምህሮም ስለተጠየፈ ነዉ ሁለቱንም ሰዎች ተራ በተራ የወሰዳቸዉ። ታድያ መምህሩንና ደቀመዝሙሩን ለሀያሉ እግዚአብሔር ቁጣ ያጋለጠዉን ክፉ አስተምህሮ እንደገና እዚህ ምስኪን ህዝብ ላይ ለመጫን የሚሞከረዉ ለምንድነዉ? ለመሆኑ የመለስ አስተምህሮ ምንድነዉ . . . . . . ስድብ፤ንቀት፤ ጥላቻ፤ ዘረኝነት፤ኢትዮጵያንና ታሪኳን መጥላት፤ አማራን በየሄደበት ማሳደድ፤ የኑሮ ዉድነት፤ ስደት፤ እስር፤ ግድያ፤ የመሬት ቅርምት፤ ብሔራዊ ዉርደት፤ . . . . . . እስኪ ወያኔዎች እናንተ አራሳችሁ ንገሩኝ ምንድነዉ የመለስ ቅርስ ዬቱ ነዉ የመለስ አስተምህሮ?
ግንቦቶች እዚህ ወረቀት ላይ ካነበብኳቸዉ ነገሮች ሁሉ የሰቀጠጠኝና አይኔን ማመን ያቃተኝ . . . . . . . 9ኛዉ የኢህአዴግ ጉባኤ የአገራችን የልማትና የዲሞክራሲ ጉዞ መሐንዲስ የነበሩት ጓድ መለስ ዜናዊ የሚታሰቡበት ጉባኤ ነዉ” የሚለዉን ሳነብብ ነዉ። ሃያ አንድ አመት ሙሉ የመጻፍና የመናገር መብቶችን አፍኖ፤ የሚቃወመዉን እየገደለና በአንድ አናሳ ብሄረሰብ የበላይነት ዙሪያ 90 ሚሊዮን ህዝብን ረግጦ የገዛዉ መለስ ዜናዊን የዲሞክራሲ መሐንዲስ ማለት ወይ ዲሞክራሲን ወይም ምህንድስናን አለዚያም ሁለቱንም አለማወቅ ይመስለኛል። ደግሞም እዉነቱን ለመናገር መለስን የዲሞክራሲ መሐንዲስ ከማለት መንግስቱ ሀ/ማሪያምን የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አባት ማለት የሚቀል ይመስለኛል . . . . . . . . ትዝ የሚለን ከሆነኮ ኢትዮጵያ ዉስጥ የመጀመሪያዎቹ የክልል መንግስታት መንግስቱ የፈጠራቸዉ የትግራይ ራስ ገዝ፤ የኤርትራ ራስ ገዝ፤ የአሰብ ራስ ገዝና ኦጋዴን ራስ ገዞች ነበሩ።
ለመሆኑ. …. የመለስን ራዕይ ከግቡ ማድረስ ኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ለምን አገሩን ለቅቆ እየተሰደደ በየዉቅያኖሱና በየበረሃዉ የእሳት እራት ሆኖ ይቀራል? እሲኪ ንገሩኝ እናንተ ወያኔዎች ምርጫችን የመለስን ፈለግ መከተል ቢሆን ኖሮ ቁጥሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ለምን “ድምጻችን ይሰማ” እያለ በየአደባባዩ በእናንተ ዱላ ይደበደባል? ደግሞስ በየቀኑ ስለማሪያም ስሙኝ እያለ የማትሰሙት የኢትዮጵያ ህዝብ እሱ እናንተን ለምን ይሰማል? እናንተ ወያኔ በአምሳያዉ የፈጠራችሁ የኢህአዴግ ቡችሎች እናንተም ስሙ . . . . . . . እስኪ ምን ይሁን ብሎ ነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የናቀዉን፤ የሰደበዉን፤ ያዋረደዉን፤ የገደለዉንና በዘረኝነት አለንጋ የለበለበዉን ሰዉ ራዕይ ከግቡ ለማድረስ ቃል የሚገባዉ? ወያኔም ሆነ ኢህአዴግ ወይም አግአዚ ጆሮ ካላችሁ ስሙ . . . . . የኢትዮጵያ ህዝብ ቃል የገባዉ እናንተ በፈቃደኝነት ከተነቀላችሁለት ፈቃዳችሁን ለማክበር አለዚያም እሱ እራሱ ነቅሎ ሊያጠፋችሁ ነዉ።
ኢህአዴግ ለ9ኛዉ ጉባኤ ሲዘጋጅ መሪ ቃል ብሎ ካስቀመጣቸዉ ሦስት ትልልቅ የዉሸት ድሪቶዎች ዉስጥ ሁለተኛዉ “ኢህአዴግ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ነዉ የሚለዉ አባባል ነዉ። ነገሩ “ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ”.. . . . እንደሚባለዉ ተረት ሆኖ ነዉ እንጂ ገና ከጧቱ ሲፈጠር ጀምሮ ኢህአዴግ መች ጠንካራ ድርጅት ሆኖ ያዉቃል? የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚወክሉትን ህዝብ ብዛትና ያላቸዉን የፖለቲካ ጡንቻ ተገንዝበዉ እንቅስቃሴያቸዉን ከፖለተካ ጡንቻቸዉ ጋር ማገናዘብ ቢችሉ ኖሮ እዉነትም የኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅት ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበር፤የኛም ትግል ወያኔ የፈጠረዉን ስርአት ለመደምሰስ ሳይሆን እንማንኛዉም በሰለጠኑ አገሮች ዉስጥ እንደሚታየዉ የፖለቲካ ህደት ትግላችን በምርጫ ህዝባዊ ሀላፊነትን ለመቀበል ብቻ ይሆን ነበር።ኢህአዴግ በወያኔ አንጎል የሚያስብ፤ በወያኔ አፍ የሚናገርና የወያኔን መንገድ የሚከተል ተሳቢ ድርጅት በመሆኑ ነዉ ዛሬ አገራችን እጅግ በጣም አደጋኛ ቦታ ላይ የምትገኘዉ።
ደግሞስ ዘረኞቹ የህወሀት መሪዎች የዘረፉትን መካፈል አቅቷቸዉ ሲጣሉ፤የኦህዴድ አባላት በአራት ቡድን ተከፋፍለዉ አንዱ የወያኔ ባሪያ ሆነን እንቀጥል ሲል ሌላዉ ደግሞ ነጻነቱን ለማወጅ እየተዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ምኑ ታይቶ ነዉ የህአዴግ ጠንካራ ድርጅት ነዉ የሚባለዉ? የሚንገዳገዱና በዉስጣቸዉ በተነሳ ቅራኔ የተነሳ ለመፍረስ አንድ ሐሙስ የቀራቸዉን ድርጅቶች ያቀፈዉ ኢህአዴግ እንዴት ሆኖ ነዉ ጠንካራ ድርጅት ሊሆን የሚችለዉ?ባለፉት አምስትና ስድስት ወራት በግልጽ እንደተመለከትነዉ ህወሀትና ኦህዴድ እርስ በርሳቸዉና አንዱ ከሌላዉ ጋር በፈጠሩት ከፍተኛ ቅራኔ የተነሳ ሁለቱ ድርጅቶች የረባ ስብሰባ እንኳን ማካሄድ አልቻሉም፤ እንግዲህ ይህ ኢህአዴግ ነዉ ጠንካራ ድርጅት ነዉ ተብሎ የሚነገረዉ።
ይገርማችኋል በዘመነ ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ሆኗል። ዘላን ለክረምት እንደሰራዉ ቤት ለመፍረስ አንድ ሳምንት የቀረዉ ኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅት ተብሎ ይወደሳል፤ የኢትዮጵያ ምሁር መዋያዉ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ቀርቶ ቃሊቲ ሆኗል፤ ጋዜጠኛም መደበኛ ስራዉ መጻፍ ሳይሆን መታሰር ሆኗል።ድምጻችን ይሰማ ብሎ የጮኸ ሽብርተኛ ተብሎ ይታሰራል፤ በምሽት በር እየሰበረ ህዝብን የሚያሸብር ጀግና ተብሎ ይሞገሳል። እንግዲህ ግንቦቶች የወያኔ ጉድ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል? እንዲያዉ በደፈናዉ እነዚህ ዘረኞች አገራችንን ጉድ በጉድ አደረጓት ማለቱ የሚበቃ ይመስለኛል።
የጋምቤላን ገበሬ መሬት ለትግራይ ባለሀብት ሰጥተዉ ጋምቤላዉ መሬቴን ሲል “ግንቦት ሰባት” ነህ ብለዉ ይጨፈጭፉታል። ፋሺስት ግራዚያኒ መታሰቢያ ሐዉልት አያስፈልገዉም ብለዉ የተቃወሙ ኢትዮጵያዉያንን አስረዉ መረጃ ካልሰጣችሁንና የብሔር ማንነታችሁን ካልተናገራችሁ አትፈቱም እያሉ ይደበድቧቸዋ። የሚገርመዉ ነጮቹ ፋሺስቶች እንኳን ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያዉያንን በአንድ ጀምበር ሲጨፈጭፉ ያልጠየቁትን የብሔረ ማንነት ዛሬ ጥቁሮቹ ፋሺስቶች አባቶቻቸዉን የጨፈጨፈ ሰዉ እንዴት መታሰቢይ ይሰራለታል ብለዉ የተቃወሙ ኢትዮጵያዉያንን አስረዉ የዬትኛዉ ብሔር አባል ነህ ብለዉ መጠየቃቸዉ በእርግጥም ማርሻል ግራዚያኒ ሀዉልት ሳይሆን የቆመለት እሱ እራሱ መልኩን ለዉጦ የመጣ ነዉ የሚመስለዉ።
እንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ልብ ብለህ ነገሮችን አስተዉል . . . . . ኢነዚህ ዳግማዊ ግራዚያኒዎች ናቸዉ በየክልሉ በአምሳያቸዉ የፈጠሯቸዉን አሻንጉሊቶች አቅፈዉና እራሳቸዉን ኢህአዴግ ብለዉ ሰይመዉ ከዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ድረስ ጉባኤ፤ እድገት፤ ህዳሴ፤የመለስ ራዕይና ትራንስፎርሜሺን እያሉ እያደነቆሩህ የሚከርሙት። እነዚህ ከመልካም አስተዳደር ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑ ጉዶች ናቸዉ ሰልመልካም አስተዳደር ለሰብኩህ የሚሞክሩት። ለኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ኢህአዴግ ብዙ የሚነገረዉ ያለ አይመስለኝም . . . . . ሃያ አንድ አመት ሙሉ እንደቋጥኝ ተጭነዉበት ጀርባዉን አጉብጦታልና ያዉቀዋል። ኢህአዴግ የራሱ የሆነ ማንነት ያለዉ እዉን የሆነ ድርጅት ሳይሆን ህወሀት የራሱን እዉነተኛ ማንነት ለመሸፈን እንደብረት ቀጥቅጦ የሰራዉ የማታለያ ሽፋን ነዉ። ለዚህም ነዉ በድምሩ 439 የፓርላማ ወንበር ያላቸዉ ሦስቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች 38 ወንበር ላለዉ ለህወሀት እየሰገዱ የሚኖሩት። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አህያ ሜዳ ለሜዳ ሳሯን እየጋጠች ብትበላ ወይም እንደሰዉ ልጅ ምግብ ተሰርቶላት በሳህን ብትበላ አህያ መባሏ አይቀርም . . . . . . ኢህአዴግም እንደዚሁ ነዉ። ዘጠኝ ግዜ ቀርቶ ዘጠና ዘጠኝ ግዜ ጉባኤ እያለ ቢሰበሰብና የራሱን ብጤ ደካማና አድር ባይ ምሁራንን በየጉባኤዉ ቢያሳትፍ አህያ ለመሸከም እንደተፈጠረች ሁሉ ኢህአዴግም እንደጋሪ ለመጎተት የተፈጠረ ድርጅት ነዉና ኢህአዴግነቱን አይለቅም።ከዛሬ ጀምሮ እስከማክሰኞ ድረስ በቴሌቪዥን የምንመለከተዉ ድራማ አላማዉ አንድና አንድ ብቻ ነዉ . . . . . . እሱም አስቀያሚዉን ኢህአዴግ ሊፕስቲክና የፊት ማሳመሪያ ቅባት እየቀቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማሳየት ነዉ . . . .መቼም የወያኔ ነገር ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ እንደሚሉት ሆኖ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብማ ኢህአዴግ ገና ጉባኤዉን ሳይጀምር ነዉ .. . . . . ለማያዉቅሽ ታጠኚ ብሎ የተረተበት።
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment