ለዘ-ሐበሻ ከባህዳር የደረሱ መረጃዎች እንዳመለከቱት ዛሬ በከተማዋ በፖሊስና በህብረተሰቡ መካከል በተደረገ የተኩስና የድንጋይ ውርውራ ልውውጥ ሰዎች ሞተዋል፤ የቆሰሉም አሉ፡፡ ፖሊስና ልዩ ሃይል በጥይት፤ ሕዝቡ በድንጋይ ባደረጉት መከታከት ከፖሊስም እንዲሁ የቆሰሉ እንዳሉ ተገልጿል፡፡
እንደ መረጃዎቹ ገለጻ በርካቶች ቆስለዋል ከፖሊስም ከህዝቡም፡፡ በኋላም ፖሊስ ህዝቡን ሲያባርር ህዝቡ እደገና ፖሊስን ሲያባርር ከቆዩ በኋላ ህዝብ ፖሊሱን ሁሉ እያባረረ ወደ መሃል ከተማው ቀበሌ አስራ ሶስት ጎፋ አካባቢ ሲደርሱ የመጣው ልዩ ሃይል ህዝቡ ላይ አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ለመበተን ቢሞክሩም ሳይችሉ ቀርተው ህዝቡ በአንድ ሆሆሆ ብሎ በመሄድ ልዩ ሃይሎችንም በድንጋይና ጠርሙስ መቀጥቀጥ ይጀምራል፡፡
በዚህ ሰዓት የሞቱና የቆሰሉ በርካታ ናቸው ለጊዜው ቁጥራቸው አልደረሰንም፤ ከባህርዳር ያለው ምንጫችን ሲልክልን ለህዝብ እናደርሳለን፡፡ ፖሊስም ግሬደር በመያዝ ችግሩ ወደተፈጠረበት አካባቢ በመሄድ አያሌው ጎበዜ የሚባለውን ሰፈር እስከ ቤት እቃዎቻቸው ድረስ ጠራርጎ በማፈራረስ እና በአካባቢው የሚንቀሳቀስን ወጣት በሙሉ ለቃቅመው በማሰር ላይ ሲሆኑ አልፎ አልፎም የተኩስ ድምፅ ይሰማል፡፡
ፖሊስ ሴቶችንም ወንዶችንም ሽማግሌ ህፃን ሳይል በማሰር ላይ የሚገኝ ሲሆን የአካባቢው ወንዶች የት እንደደረሱ የታወቀ ነገር የለም። ሚስቶቻቸው እህት እናቶቻቸው አባት ወንድሞቻቸው በአጠቃላይ እዛ አካባቢ ያለው ሁሉ ወደ እስር ቤት ተግዘዋል፡፡ ይህ ተኩስ ልውውጥ ላይ እንደ አይን እማኞች ከሆነ ከበርካታ የባህርዳር ቀበሌዎች የተሰባሰበ ህብረተሰብ ከሰፈሩ ሰዎች ጋር በመተባበር ፖሊስና ልዩ ሃይልን በጋራ ሲያባርር እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በዛሬው የባህርዳሩ ግጭት ለጊዜው የአባቱ ስም ያልታወቀ ጨመረ የተባለ ወጣት ግንባሩ ላይ በጥይት ተመትቶ አስከሬኑ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ፖሊሶች ቀምተው አስከሬኑን አንሰጥም ማለታቸውም ተሰምቷል።
ለዘ-ሐበሻ መረጃውን ያደረሱ ወገኖች እንዳሉት ይህ ግጭት ለጊዜው አሁን ትንሽ ጋብ ያለ ቢሆንም አልፎ አልፎ በዚህ ሰዓትም ተኩስ ድምፅ ይሰማል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች እና ቀበሌዎች “ለፖሊስ ኢፍትሃዊ ድርጊት አንገዛም፤ ላቤን ጠብ አድርጌ አፈር ቆፍሬ ደክሜ የሰራሁትን ቤት ሲያሰኝህ እየመጣህ ልታፈርሰው አትችልምም፣ ፈቃድ አውጥቼ ስንት ጊዜ በሙሰኛ ባለስልጣናት ተበዝብዤ የሰራሁትን ቤቴን ሌላ መውደቂያ ሳይኖረኝማ አታፈርሰውም” ብለው ለበርካታ አመታት ሲደክሙ ቆዩትን ቤት በሌሊት እንደ ሽፍታ የማፍረሻ ትዕዛዝ ሳያሳዩ ለማፍረስ መሞከር ህገወጥነት ሆኖ እያለ የንፁሃንን ደም በከንቱ ማፍሰስ የመንግስትን ወሮ በላነትና የፖሊስን ደደብነት የሚያሳይ አሮጋንተነት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የባህርዳር ነዋሪዎች ይሰጣሉ፡፡
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/29034
No comments:
Post a Comment