Monday, May 19, 2014

አንድነት ፓርቲ በዝዋይ ማረሚያ ቤት በፖለቲካ እስረኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን ህገወጥ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን ሲል መግለጫ ሰጠ

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነትየተሠጠ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የትንሳዔን በዓል ምክንያት በማድረግ በተለያዩ እስርቤቶች የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን በያሉበት እስርቤቶች ፕሮግራም አውጥቶ በቡድን በቡድን በመሆን የእንኳን አደረሳች መልእክቶችን ለማድረስ ችሎ ነበር፡፡ ከእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታችን በተጨማሪ ከፍተኛ አመራሩ አላማ ያሉበትን የአያያዝ ሁኔታ ለመረዳት ጭምር ነው፡፡

ከዚህም መሰረት በተለይ በዝዋይ በፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀምባቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዝዋይ ማረሚያ ቤት በሚገኙ የፖለቲካ እስረኞችን እና ጋዜጠኞችን ዝዋይ የተመደበው የልዑካን ቡድኑ ጎብኝቶ ከመጣበት እለት ጀምሮ ደግሞ በእስረኞቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የአካል እንዲሁም የስነ ልቦና ችግሮች እየደረሱባቸው ይገኛል፡፡ ለዚህም የእስረኞች ቤተሰቦች ለጥየቃ በሚሄዱበት ጊዜ መጎብኘት እንደማይችልና ይዘውት የሄዱትን ምግብ ይዘውት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

እስረኞቹ የሚፈፀምባቸውን በደል ለማሳወቅ 3 ቀን የሚቆይ የርሃብ አድማ በማድረጋቸው የዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ከአራት ወራት በፊት ማንኛውም ቤተሰብ እስረኞችን ለመጠየቅ ወደዚህ ቦታ ድርሽ እንዳይል የሚል ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው የእስረኞች ቤተሰቦች  ምንአድርገዋቸው እንደሆነ አላወቅንም በማለት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የእስረኞቹን ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ተጠብቆ ከቤተሰቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው እንዲሁም ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበት መንገድ በአስቸኳ እንዲመቻች እንዲሁም በእስረኞች ላይ የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡

በተለይም ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ሀገር ዓቀፍና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ደርጅቶች፤ ዲፕሎማቶች፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች፤ ጋዜጠኞችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በእስረኞች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለማስቆምና የፖለቲካ እስረኞችን ለመታደግ እንዲሁም የህግና የሞራል ግዴታን ለመወጣት እንድንረባረብ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በውጭ ሀገር የምትኖሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ይህንን አስከፊ ድርጊት በማውገዝ ድምፃችሁን እንድታሰሙ እንጠይቃለን፡፡

ድል የሕዝብ ነው!!!

               አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
                           ግንቦት 11 ቀን 2006 .

                                አዲስ አበባ



No comments:

Post a Comment