Monday, May 5, 2014

ከወያኔ ኢህአዴግ የጣር በትር አገራችንን እና ሕዝባችንን እንታደግ

ባለፉት ፳፫ የስልጣን ዘመኑ እንዲሁም ከዚያም በፊት በ፲፯ የጫካ ዘመኑ ኢትዮጵያን ከካርታ፣ ህዝቧን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ወያኔ አርነት ትግራይ ያልፈነቀለው ድንጋይ ያላፈሰሰው ደም የለም።
በባዕዳን ሁለንተናዊ ድጋፍ በመታገዝና በአንቀልባ በመታዘል በተለያዩ የአገሪቱ አቅጣጫዎች በመገስገስ ላይ እያለ በተለያዩ ግዛት ያሉ ኢትዮጵያውያኖች የዚህን እኩይ ግስጋሴ ለመግታት አይከፍሉ መስዋእትነት ከፍለዋል፤ የጣሊያንን ወረራ ለመመከት በግንደ በረት በረሃ ለሃገራቸው ኢትዮጵያ ተጋድሎ እንዳደረጉት እንደ አባት እናቶቻቸው አያት ቅድመ አያቶቻቸው የዘመኑ የአምቦ ትንታግ ወጣቶች የዛሬ ፳፫ አመት በወርሃ ግንቦት ባደረጉት ተጋድሎ የገበሩት ህይወት ምንግዜም የጀግንነት ታሪካቸው በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል።
የብሄር ብሄረሰብ መብት አስከባሪ ከኔ በላይ ላሳር ባዩ ወያኔ በቴሌቪዥኑ በየቋንቋው ከማዘፈንና ከማስለቀስ ያለፈ እኩልነት ኢትዮጵያ ውስጥ ታፍኖ በመቀበሩ፤ የማንነትና ፍትሐዊ የመብት እኩልነትን በጠየቁ በአፋር፣በኦጋዴን፣በአማራ፣በኦሮሞ፣በደቡብ ወዘተ ወገኖቻችን ላይ በተለያዩ ጊዜያቶች የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ስልጣኑንም መከታ በማድረግ የህዝብን ሃብት ለመዝረፍ የጭቁኖችን መሬት በመቀማት የሚያደርገውን ጭፍጨፋ መዘርዘር ይቻላል። እነሆ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ያልጠግብ ባይነት መዘዙ ተመዞ ሰይፍ ሆኖ ሰሞኑን የአምቦ ተማሪዎችን አንገት ቀልቷል።
ለህዝብ መብት መከበር፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት እና ለዲሞክራሲ መስፈን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ባለፉት አመታት የከፈሉት መስዋዕትነት አልበቃ ብሎ የዛሬውንም ትውልድ ደም እያስገበረ ይገኛል። ግና ትግል ትግል ነውና ወላድ በድባብ ትሂድ ፀረ ወያኔው ትግል ሰሞኑን በአምቦ ተማሪዎች ተለኩሶ በጅማ፣ በድሬዳዋ ፣በአዲስ አበባ፣ ሃረማያ ወዘተ እየተቀጣጠለ ይገኛል።
ባለፉት ወራትም በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ፣በአዋሳ፣በአፋር፣በጋምቤላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ህዝባዊ አመፁና ሰልፉ እየተንቦገቦገ ይገኛል።
እኛ በዋሽንግተንና አካባቢዋ የምንገኝ የጋራ ግብረሃይልም ህዝባችን እያካሄደ ያለውን ትግል እየደገፍን በአምቦ የኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ አምርረን እናወግዛለን።
ለዚህም ነው ደማችሁ ደማችን ነው የምንለው፤ በልማት ስም ዘር ማጥፋት ይቁም እያልን ይህንኑ ድምጽ ለአለም ለማሰማት የፊታችን እሮብ ሚያዝያ ፳፱, ፳፻፮ ከጠዋቱ ሰአት ቀጠሯችን በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ይሁን እንላለን።

ቀን፦ MAY 7, 2014
ሰአት፦ 9:00 AM
ቦታ፦ U.S State Department
2201 C St NW
Washington, DC. 20520


የዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረሃይል

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/29986

No comments:

Post a Comment