Wednesday, May 7, 2014

የዜጎችን ጥያቄ በግድያ ማስቆም አይቻልም (ሰማያዊ ፓርቲ)

May 7, 2014
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የዜጎችን ጥያቄ በግድያ ማስቆም አይቻልም

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ነጻ እንዲወጡ እገዛ ያደረገችላቸውን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አገራት የህዝብን ጥያቄ በተገቢው የሚያዳምጡ፣ ችግሮች ሲኖሩ በጠረጴዛ ዙሪያና በሰከነ መልኩ መፍታት የሚችል መንግስት መመስረት ሲችሉ በተቃራኒው በአገራችን ስልጣን ላይ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ግን ዜጎችን በኃይል እየገዛ ይገኛል፡፡ ለዚህም በቅርቡ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች የተፈጸሙትን ግድያዎችና ሌሎች ህገ ወጥ እርምጃዎች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡Ethiopia's Semayawi (Blue) party logo
የአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙት ከተሞች ‹‹የተቀናጀ መሪ ፕላን (ማስተር ፕላን)›› አስመልክቶ በስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ የገባቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያነሱት ሰላማዊ ጥያቄ ተከትሎ በርካታ ተማሪዎችና ነዋሪዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ ቆስለዋል፡፡ በርካታ ተማሪዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በተያያዘ ከወራት በፊት በሀረር ከተማ የተከሰተውን ቃጠሎ ተከትሎም ዜጎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ በተመሳሳይ በባህር ዳርና ጎንደር ከተሞች ‹‹ህገ ወጥ ግንባታ ነው›› ተብለው ያለ ካሳ፣ ቅያሬና በቂ ጊዜ ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ቤታቸው በዚህ ሁኔታ መፍረሱ አግባብ አለመሆኑን በመግለጻቸው በጥይት ተደብድበዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ለከፋ ድብደባ ተዳርገዋል፡፡ ቀሪዎቹ በተለይም ጥያቄ ያነሳሉ ተብለው የተፈሩት አባወራዎች እስር ቤት ውስጥ ታጉረዋል፡፡
ዜጎች ጥያቄያችው ምንም ይሁን ምን ‹‹መንግስት ነኝ!›› ብሎ ስልጣን ላይ የተቀመጠ አካል ጥያቄያቸውን አዳምጦ በሰከነ መንገድ ምላሽ ወይንም መፍትሄ የመስጠት ግዴት የነበረበት ቢሆንም ዜጎችን ምንም አይነት ጥያቄ እንዲያነሱ የማይፈልገው ገዥው ፓርቲ ምላሹ ለሰላማዊ ዜጎች የማይገባ ጥይት ሆኗል፡፡ ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚሞክረው ለዜጎች መሰረታዊ ጥያቄን አሟልቶ አገር የመምራት ብቃት የሌለው ከመሆኑ አንጻር ህዝብ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳብኛል ብሎ ስለሚሰጋ፣ የተነሱትንም ጥያቄዎች የመመለስ አቅም ስለሌለውና ምንም አይነት ችግር ቢኖርም ህዝብ እያስፈራራ ለመግዛት ካለው አባዜ ነው፡፡
ይህ ስርዓቱ የራሱን መሰረታዊ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መመለስና መፍታት ሲያቅተው ህዝብን በኃይል አፍኖ የመግዛት የፖለቲካ ባህሉም አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ በፖሊስ መንግስትነት (ፖሊስ ስቴት) ስር እንደወደቀች ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ የስርዓቱ ባህሪ ምክንያት ኢትዮጵያ አገራችን ዜጎች ሰላማዊ ጥያቄያቸውን ለመንግስት የማያቀርቡባት፣ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡም ህይወታቸውን የሚያጡባት አገር እንደሆች የሰሞኑ አረመኔያዊ እርምጃን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ዜጎች የትኛውንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማንሳት መብታቸው እንደሆነ የሚያምነውና ለዚህም የሚታገለው ሰማያዊ ፓርቲ ስርዓቱ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች እየፈጸማቸው የሚገናቸውን አረመኔያዊ እርምጃዎች ያወግዛል፡፡ እስካሁን ድረስ ገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያውያን ላይ የወሰደውን እርምጃ ህጋዊ ለማስመሰል የባንክ ዘረፋንና ህገ ወጥ የቤት ግንባታን የመሳሰሉትን ምክንያቶች በመጥቀስ የተወሰደውን እርምጃ ህጋዊ ለማድረግ መሞከሩም ተጠያቂነት የጎደለውና ከምክንያት የራቀ በመሆኑ፤ እነዚህ ዜጎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ላይ ለህዝብ በቂ መረጃ እንዲሰጥና ተጠያቂነቱን እንዲወስድ እናሳስባለን፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ የአገራችንን ህዝብ ጥያቄ በኃይል ለመደፍጠጥ ቆርጦ የተነሳ በመሆኑ የትኛውንም ሰላማዊ ጥያቄ ያነሳ ኢትዮጵያዊ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ገዥው ፓርቲ በፈጠረው የከፋፍለህ ግዛ ስርዓት ሳይወናበዱ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን ህገ ወጥ እርምጃ ላይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙና ለስርዓቱ መሳሪያ ከመሆን እንዲቆጠቡ እንዲሁም አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ገዥው ፓርቲ በህዝብ ላይ እየወሰደው ያለውን የኃይል እርምጃ እንዲያጋልጡና እንዲቃወሙ፣ እያጋለጡና እየተቃወሙ ያሉትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሰማያዊ ፓርቲ ያሳስባል።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰማያዊ ፓርቲ
ሚያዝያ 2006 ዓ.ም
http://ecadforum.com/Amharic/archives/12216/

No comments:

Post a Comment