Friday, April 17, 2015

በደቡብ አፍሪካ እየተፈጸመ ያለውን ስደተኞችን የማጥቃትና ማሳድድ ወንጀል በመቃወም ሰልፈኞች ድምጻቸውን ሲያሰሙ ዋሉ


 በደቡብ አፍሪካ የውጪ ሀገር ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ያስቆጣቸው በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ደርጊቱን ለማውገዝ በደርባን ታላቅ ሰልፍ ማድረጋቸውን የአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን እና የውጭ አገር ዜጎች በሰልፉ ላይ ተገኝተዋል። “የውጪ ሀገር ዜጎችን ማጥቃትና ማሳድድ ይቁም!” የሚል መፈክር ያነገቡት የደርባን ነዋሪዎች፤ በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ ተቃውሟቸውንና ቁጣቸውን ገልጸዋል።

ሰልፈኞቹ ትናንት በደርባን የተፈጸመውን ድርጊት ከማውገዝ ባሻገር ለውጪ ሀገር ዜጎች ያላቸውን አጋርነት በይፋ አረጋግጠዋል።.

ሰሞኑን በደርባን በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 5 ሰዎች መገደላቸውንና የበርካታ ሰዎች ሱቆች መዘረፋቸውን ቢቢሲ አመልክቷል። ከሟቾቹ ውስጥ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።


በደርባን የሚገኙ ኢትዮጵያኖች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰዱ ነው። በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ወኪል ወደ ደርባን በማቅናት ኢትዮጵያውያኑን ማነጋገሩን የደሰረን መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያውያን በወገኖቻቸው ላይ የደረሰውን ጥቃት የማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም እያወገዙት ነው።

በደርባን የተፈጸመው እርምጃ በጆሃንስበርግም ይደገማል የሚል የስልክ መልእክት ተላልፎአል በሚል፣ በከተማዋ የሚገኙ የውጭ አገር ነዋሪዎች ሱቆች ተዘግተው አርፍደዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 ዓመተ ምህረት በውጪ ሀገር ዜጎች ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት 62 ሰዎች እንደተገደሉ መዘገብቡ አይዘነጋም።

የዙሉ ንጉስ የውጪ ሀገር ሰዎች ሻንጣቸውን ሸክፈው ወደሀገራቸው መሄድ አለባቸው በማለት ያደረጉት ንግግር ለጥቃቱ መጀመርና መባባስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል። እርሳቸው ግን ለችግሩ ተጠያቂ አይደለሁም በማለት አስተባብለዋል።

ጥቃቱ መፈጸሙን ተከትሎ ማላዊ ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ በማውጣት ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን፤ ዚምባቡዌም ድርጊቱን በይፋ በማውገዝ በውጪ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ጠይቃለች።



http://www.zehabesha.com/amharic/archives/40558

Related Posts:

No comments:

Post a Comment