Wednesday, February 20, 2013

በወያኔ ኢትዮጵያ: ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ፣ ቆርጦ ቀጥል ኢኮኖሚ

ዶ/ር ዘላለም ተክሉ
02/19/2013
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተላለፈ ያለውን አሳፋሪ “ የጀሃዳዊ ሃረካት” ድራማ በአግራሞት ስመለከትና በቅርቡም ይለቀቃል ተብሉ ስለሚጠበቀው “ ነውጥን ናፋቂ የሩቅ አገር ሰዎች” የፕሮፖጋንዳ ቪዲዮ እያሰብኩ ሳለሁ ነው ሌላ ኢኮኖሚያዊ ድራማ በ Addis Fortune ድህረ ገጽ ላይ የተመለከትኩት:: ይህ እኔ ልጽፍ የተነሳሁበት ድራማ በፊት ከጠቀስኳቸው ድራማዎች ለየት የሚያደርገው ፊልሞቹ በሙስሊምና ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ ፍርሃት፣ አለመተማመንና ጥላቻን ለማባባስና የሃማኖት መብት ጥያቄያቸውን ለማፈን በስፋት እየተካሄደ ያለ ዘመቻ ሲሆን በጽሁፍ መልክ የወጣው ድራማ ግን መንግሥት ላለፉት 7 እና 8 ዓማታት አስመዘገብኩ እያለ በሚላላጥበት የሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የተከሰተውን የቀመር መዛባት ቅሌት ተድበስብሶ እንዲታለፍ እያደረገው ያለ ሴራ መሆኑ ነው::
ሁላችንን እንደምናውቀው ወያኔ በሃገሪቱ ከ 11 እስከ 12 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት አመጣሁ እያለ ከበሮ መደለቀና ማስደለቅ ከጀመረ ዓማታት አስቆጥሯል:: ይህ በሃገሪቷም ሆነ በአፍሪካ “ታይቶ ያልታወቀ” ብጽግና ሊገኝ የቻለው ባለ “ራዕዩ” እና “ብልሁ” መሪ መለስ ዜናዊ በቀረጹት “ልማታዊ መንግሥት” አመራር ብቃት እንደሆነም እስኪሰለቸን ሲነገረን ቆይቷል:: ይህ ፉከራ በጣም የተጋነነ መሆኑን የዓለም ባንክ (World Bank) እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund) በተደጋጋሚ ቢያስረዱም በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በሰላ ምላሳቸው እነዚህን ድርጅቶች ከምዕራባውያን ኒዮ-ሊብራሊስት (Neo- liberalist) እና የኒዎ-ኮሎኒያሊት (Neo- Colonialist) አፍራሽ ተልዕኮ ጋር በማመሳሰል አፋቸውን ዘግተው እንዲቀመጡ አድርገዋቸዋል:: የሃገራችን ህዝብም በነዚህ ዓመታት ተገኘ የሚባለው ዕድገት የቁጥር ቅዥት (Numerical Myth) እንጂ የሚዳሰስ ጥቅም ያላመጣ እልቁንስ ለበለጠ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ ድህነት፣ረሃብና ስደት የተዳረገበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ሲሞግት በጠባብ ብሄረተኝነት፣ ትምክተኝነት፣ ነፍጠኝነትና ሽብርተኝነት በመፈረጅ አርፎ እንዲገዛ ተደርጎ ይገኛል: ይህንኑ ዕብደትም የተቃወሙና በጽሁፍ ያጋለጡ ጋዜጠኞች፣ የሰባዊ መብት ተከራከሪዎች፣ ባለሙያዎችና የፖለቲካ ተንታኞች ወይ በአገር ውስጥ እስር ቤቶች እየማቀቁ ይገኛሉ ወይ ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል::
እውነታው በዚህ ሁኔታ ባለበት አንጻር ነው እንግዲህ አዲስ የዕድገት ቀመር ትንበያ በገዢው መንግሥት ጓሮ በር እየወጣ ያለው:: በ Addis Fortune ድህረ ገጽ ላይ እንደቀላል ነገር (as low profile issue) እዲወጣ የተደረገው ጽሁፍ እንደሚያሳየው የሃገሪቱን አጠቃላይ ምርት (Gross Domestic Product) ለማስላት እስካሁን ድረስ በማነጻጸሪያነት (Base Year) ሲወሰድ የነበረው 1999/ 2000 በ 2010/11 በመቀየሩ የዓመታዊ ዕድገቱ ትንበያ ከ 11 በመቶ ወደ 8.5 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተዘግቧል:: ይህ ድንገተኛ ክለሳ IMF/ World Bank ለዓመታት ከሚከራከሩበት የ 7-8 በመቶ ዕድገት ጋር ተቀራራቢ ሆኖ ቢገኝም መንግስት ይህንን ያደረገው ውጥረትና ጥርጣሬ ለማርገብ ሳይሆን ተጨማሪ ምርትና አገልግሎት በስሌቱ ሂደት በመጨመራቸው እንደሆነ ያስተባብላል:: የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም እስካሁን እየተሰራበት ያለው ቀመር ምን ያህል በተሳሳተ ግምት ላይ ተመስርቶ የተቀሸበ ተራ አሃዝ ብቻ እንደሆነና በአጠቃላይም የወያኔ ፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውም ቆርጦ ቀጥል (Cut & Paste) የሆነ የቁጭ በሉ ውጤት እንደሆነ ለማሳየት ነው::
የዕድገት ቀመሩ በተሳሳተ መሰረት ላይ እንደተቀሸበ የሚያመለክተው መነሻ የ 1999/ 2000 አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርትን (GDP) እስካሁን ድረስ ላሉት ዓመታት ዕድገት ማነጻጸሪያ ተደርጎ መወሰዱ ነው:: ከ 1998–2000 የሃገሪቱን ኢኮኖሚና ከ 70 እስከ 80 ሺህ ዜጎች ነፍስ እምሽክ አድርጎ የበላው የኢትዮጵያ–ኤርትራ ጦርነት የተካሄደበትና ሃገሪቷም በከፍተኛ ድርቅና የምግብ እጥራት የተመታችበት ጊዜ መሆኑ እየታወቀ እንደ ኖርማል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዘመን ተወስዶ ለዕድገት መለኪያነት ጥቅም ላይ መዋሉ በጣም የተሳሳተ አካሄድ ነበር:: ይህ እኮ ማለት የቀነኒሳን የረጅም ርቀት ሩጫ ውጤት መሻሻል ለመለካት ከሞ ኢብራሂም (ሶማሊ እንግሊዛዊው) ወይም ከስለሺ ስህን ወይም ከኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ሳይሆን ምንም ችሎታ ከሌለኝ ከኔ ጋር እንደማነጻጸር ማለት ነው:: እንኳንስ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነበትና ከ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕርዳታ በዓመት የሚጎርፍለት መንግሥት ይቅርና ያለማንም ምዕራባውያን ዕርዳታ ሲንገታገት የነበረው የደርግ ዘመን እንኳን ከ 1999/ 2000 ጋር ቢነጻጸር የተሻለ ዕድገት ሊያሳይ እንደሚችል ምንም ጥርጥር አይኖረኝም:: ወያኔ መቼስ ይህ እውነታ ጠፍቶ ነው ማለት ዘበት ነው:: እልቁንስ “የአኬልዳማ” እና “ የጀሃዳዊ ሃረካት”ን ቆርጦ በመቀጠል በሰራው ድራማ ሊመታው እንዳሳበው የህዝብ እንቅስቃሴ የሚመቸውን መለኪያ ቆርጦ በመቀጠል ከሚያሰላው ቀመር ከፍተኛ ዕድገት እንዳመጣ የሚያሳይ ድራማ ለመስራት አልሞ እንጂ::
በተለቀቀው ጽሁፍ እንደተመለከተው የዕድገት ማነፃፀሪያው (Base Year) መቀየሩ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ እውነታ ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለው ምንም ለውጥ አያመጣም ብሎ መንግስት እንደሚያምን ተገልጿል:: ይህ መከራከሪያ ነጥብ ግን ምንም ውሃ እንደማይቋጥር እንደሚከተለው ማሳየት ይቻላላል:: በመጀመሪያ ደረጃ የአገሪቱ አጠቃላይ ምርትን (GDP) አደገ ሲባል የአገሪቱ አመታዊ ገቢ አደገ ማለት ነው:: ይህም ያደገ አጠቃላይ ገቢ ለጠቅላላው ህዝብ ሲካፈል ነው የነፍስ ወከፍ ገቢ አደገ የሚባለው:: የነፍስ ወከፍ ገቢ የሚያድገውም የስራ ዕድልና የግል ንግድ ሲስፋፋ ነው:: የነፍስ ወከፍ ገቢ ሲያድግ ነው በቀን ሦስት ጊዜ የመመገብ፣ የተሻለ የመልበስና መጠለያ የማግኘት ዕድሉ የሚጨምረው:: እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ እየተሟሉ ሲሄዱ ነው ዜጎች ከድህነት ወጡ የምንለው:: ወገኖች ከድህነት እየወጡ ሲሄዱ ነው የፍጆታ ፍላጎቱ እያደገ የሚሄደው እንዲሁም የተረፈውንም ገቢ መቆጠብ የሚጀመረው:: እንግዲህ ባለፉት 7 እና 8 ዓመታት በእውነቱ ኢኮኖሚው እንደተባለው አድጎ ቢሆን ኖሮ ከላይ የጠቀስናቸው ቀጥተኛ ተያዥዥነት ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በህዝባችንና በሃገራችን ላይ በታዩ ነበር:: በየዓመቱ ተገኘ የተባለው የ 11 በመቶ ስሌት የላሸቀ አጠቃላይ ምርት (GDP) ከተገኘበት ዓመት ጋር ተነጻጽሮ የተቀሸበ ዕድገት በመሆኑ ህረተሰባችን ተጨባጭ (Tangible) የሆነ የገቢ መሻሻል እንዳመጣ አላሳየም፣ የሥራ ዕድሉም አልተስፋፋም፣ ፍጆታና ቁጠባውም አልተጠናከረም፣ የዕለት ኑሮም አልተሻሻለም፣ ድህነቱም አልቀነሰም፣ ስደቱም አልተገታም። እልቁንስ የተሳሳተው የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ በተዘዋዋሪ መንገድ ለኑሮ ውድነቱ (Inflation) የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል:: ገቢው ያደገለት ብዙ ተጠቃሚ (Consumer) እናገኛለን ከሚል የተሳሳተ ግምት በመነሳት ነው ጥቂት ጥቅመኞች በአጭር ጊዜ ትርፍ በሚያስገኝ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ብዙ ኢንቨስት ያደረጉት:: ለነዚህ ዘርፎች ልማት በጥሬ ዕቃነት (Intermediate Good) በብዛት በመዋላቸው ነው የኢንዱስትሪ ምርቶች እጥረትና ዋጋ መናር የተከሰተው:: የጠበቁትን ያህል ገዢ አጥተው ተንቀዋለው ቀሩ እንጂ ኢኮኖሚው ያደገ ህብረተሰብ ይገዘናል ብለው ነበር ብዙ መኖሪያ ቪላዎችና ኮንዶዎች የተገነቡት:: የነዚህ ግንባታዎች የጥሬ ዕቃ ፍላጎት መጨመር ነው ለተራው ቤት ሰሪ ህዝብ የሲሚንቶ፣ ቆርቆሮና ሌሎች የሕንጻ ግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ መናር አስተዋጽኦ ያደረገው:: በአጭር ጊዜ ትርፋማ ዘርፎች ላይ የተለየ ትኩረት በመደረጉና የግብርና ዘርፉ የግል ኢንቨስትመንት በመዘንጋቱ ነው የምግብ አቅርቦቱ የቀነሰውና ከፍተኛ የዋጋ መናር የታየው::
የዕድገት ማነፃፀሪያው (Base Year) መቀየሩ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተጽዕኖው ላለፉት ዓመታት ብቻ ሳይሆን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ (Growth and Transformation Plan)ተአማኒነትና ተግባራዊነትም ጭምር ነው:: እንደሚታወቀው ይህ ዕቅድ የተዘጋጀው ከ2005/06–2009/10 ተከሂዶ የተጠናቀቀውን የተፋጠነ፣ ዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ ዕቅድን (Plan for Acceperated and Sustainable Development to End Poverty) መሰረት አድርጎ ነው:: በዚህ የመካከለኛ የልማት ዕቅድ (Medium Term Plan) ወቅት ተገኘ የተባለውን የ 11 በመቶ ዕድገት ነው እንግዲህ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መነሻና መነጻጸሪያ የሆነው:: የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የ 2010/11–2014/15 ሲጠናቀቅ ቢያንስ የማነጸሪያውን 11 በመቶ ማስጠበቅ (Base Case) አለዚያም 14 በመቶ ዕድገት (High Case) የማግኘት፣ የሃገሪቱን ግብርና ምርት በእጥፍ ማሳደግና ድህነትን ከ 22 በመቶ በታች ማውረድ ነው:: ይህንንም ትልም በማሳካት በአጭር አመታት ውስጥ አገሪዋቷን አሁን ካለችበት ዝቅተኛ የገቢ ደረጃ ሃገሮች (Low Income Countries (<$996)) ተርታ ወደ መካከለኛ ሃገሮች መደብ (Middle Income Countries($996-$3945)) ማሸጋገር ነው ረጅም ዕቅዱ:: እንግዲህ ችግሩ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው:: በ 2005/06–2009/10 ተገኘ የተባለው 11 በመቶ ዕድገት ከላይ እንደተረዳነው በተሳሳተ ስሌት የተገኘ ጠቁዋሚ ቀመር ነው:: የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱም ይህንን የተሳሳተ ስሌት መሰረት ካደረገ ሊሰሩ የታቀዱት የግብርና፣የኢንዱስትሪና የአገልግሎች ዝርዝር ሥራዎች በእብቧይ ላይ እንደተካቡ ግንቦች ናቸው ማለት ነው:: ቀድሞውንም በሌለ የ 11 በመቶ ዕድገት እንዴ ተብሎ ነው ከዚያ በላይ ለውጥ ለማምጣት ተጨማሪ የሰውና የፋይናንስ ሃብት እየፈሰሰና በቀሪውም ጊዜ ማፍሰስ የሚቻለው:: በዚህ ሁኔታ ተአማኒነቱ ያጠራጥራል እንጂ አሁን ይገኛል ተብሎ የተገመተው 8.5 በመቶ ዕድገት እንደማነጻጸሪያነት ቢወሰድ እንኳን እንዴት ተደርጎ ነው መሰረቱ የተናጋውን ግንባታ እንዳይፈርስ አድርጎ ማስቀጠል የሚቻለው? እንዴትስ ተደርጎ ነው ካለፉት ግማሽ የዕቅዱ ዓመታት አፈጻጸም ጋር ማስማማት(reconcile) የሚቻለው?
ለነገሩ ፖለቲካው ቆርጦ በመቀጠል ህግና የመገናኛ ብዙሃን ሥርዓት ላይ ለተገነባ መንግሥት ቆርጦ የተቀጠለ የልማት ዕቅድና የልማት ዕድገት መረጃ ማዘጋጀት ምን ይሳነዋል ተብሎ ይታማል:: ወያኔ እስካለ ድረስ የዚህ ዓይነት ቁጭ በሉ ሥራዎች ወደፊትም በስፋት እንደምናይ ምንም ጥርጥር የለኝም:: ቁም ነገሩ ይህን ለአምባገነነዊ አገዛዙ ማራዘሚ ይጠቅመኛል ብሎ የተያያዘውን አካሄድ ድክመቶች መልሰን በግብአትነት በማጎልበት ሥርዓቱን በአፋጣኝ ለማስወገድ ለሚደረገው ትግል እንደመሳሪያነት የመጠቀም አቅም ማሳደግ መቻላችን ነው::
ኢትዮጵያ ሃገራችን በሰላምና በክብር ለዘላለም ትኑር::

   Posted By.Dawit Demelash

  

No comments:

Post a Comment