እኔ ክርስቲያን ነኝ ሙስሊም ወንድሞቸን በከንቱ አታሰቃዩብኝ ተዋቸዉ!
በጊዜው ይመርውድ አንባቢያን መቸም በየጊዜዉ መአት ሊወርድባችሁ፣ልትቀሰፉ ነዉ እያለ ነጋሪት የሚጎስምብንን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማክሰኞ ምሽት ጅሃድ ሃረካትን ሲያሳዬን ምን ያክል እንደምታዝኑ? ማዘን ብቻ አይደለም እንደምታፍሩበት አልጠራጠርም፡፡ መቸ ይሆን እኝህ ሃሰተ ነቢያት አንደበታቸዉ የሚዘጋዉ ስል ጊዜዉን ናፈኩ፡፡ አንድ ቢሂል ትዝ አለኝ አንድ እናቱ የሞተችበት አልቃሽ መሃል ገብቶ እናቴ እናቴ እያለ የለቅሶ ወግና ሥርዓቱ በጣሰ እየጮኸ ያስለቃሹን ወግ ያበላሸባት የሟች ዘመድ ጠጋ ብላ አንተ አያምርብህም ዝም በል ብትለዉ ድሮስ እናቴ ሙታ ምን ሊያምርብኝ ኖሯል ብሎ ያንኑ ልማደኛ አፉን መክፈት ቀጠለ ይባላል፡፡ አሁንም የኢትዮጵያ ተሌቪዥን ሃገር ያነዉርሃል የሙያ ባልደረቦችህ እነቢቢሲ፣ አልጀዚራ እና እነስም አይጠሬ መንግሥት እንዳይቀዬም ብዬ ነዉ ከአስገደዳችሁኝ ግን ስሙን እጠቅሳለሁ “ኢሳት” ይታዘቡሃል ብንለዉ ይኸዉ አልሰማ ብሎ ጅሃድ ሃረካት ሲል ማክሰኞ ምሽት ህግን ጥሶ ሲያላዝን አመሸ፡፡
ይቅርታ አድርጉልኝ የደደቢት ዉሃ እንዲህ አይምሮ እንዳያስብ ይለዉጣል? ነብሳቸዉ ከየት እንደሆነ በርግጠኝነት አድራሻዋን ባላዉቀዉም አትረፍ ያለዉ በሬ ቆዳዉ ከበሮ ይሆናል እንዲሉ እኒያ የሞቱት ሰዉዬ ለማክሰኞዉ ጅሃድ ሃረካት ትንቢት ሲናገሩ የነቢይ ቃላቸዉ ጠብ የማይል መሆኑን ያረጋግጥ ዘንድ ኢቲቪ እራያቸዉን በገቢር አሳዬን፡፡ እኔ የቸገረኝ እኚህ ሟች ሰዉዬ ስንት የጥፋት ዕራይ አይተዉልን ይሆን? እባካችሁ ‘’ ፍካሬ መለስ’’ መጽሃፍ ያላችሁ አዉሱኝ፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖብኝ ነዉ እንጂ ዋናዉ ጥያቄዬ ሙስሊም ወንድሞቸን ባልዋሉበት እያዋላችሁ አታሰቃዩዋቸዉ እናንተ ሳትመጡ በፊት እኔ አዉቃቸዋለሁ ለማት ፈልጌ ነዉ፡፡ በፊት አዉቃቸዋለሁ ስላልኩ አይግረማችሁ? አዎ ያኔ ፍትህ ዲሞክራሲ ባልሰፈነበት፣የሃይማኖት ነጻነት ባልታዎጀበት፣የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ልክ እንዳሁኑ በቁና በማይታፈስበት ዘመን አብረን እንጠጣ እንበላ ነበር፡፡ ሃዘናቸዉ ሃዘናችን ደስታቸዉ ደስታችን፣ እርሃባቸዉ እርሃባችን፣ጥማቸዉ ጥማችን ነበር፡፡ ምን ይህ ብቻ በሰላም አብረን እየተማርን አብረን እየተጫዉተን ኑረናል እየኖርንም ነዉ፡፡
ታዲያ ዲሞክራሲ ባካፋ፣
ኃይማኖታችን በኢትቪ በልፈፋ፣
የብሄረሰቦች እኩልነት በአንድ ሶፋ፣
የኢኮኖሚዉ እምርታ አድጎና ሞልቶ በአፍንጫችን ሲደፋ
በዚች ምድር ጅሃድ ሃረካትን ምን አመጣዉ? ወያኔ ጥያቄ አለኝ? ለበረከትና ለስብሃትም ጭምር እምነት የላችሁም
ግን ከሟች ወንድማችሁ ከመለስ መቃብር አትማሩም ነገ የገዛ ሥራችሁ ከዚህ ምድር ያጥፋችሁ ብዬ አልጸልይም ይልቁንስ
በቁም በሞተዉ ሥጋችሁና መንፈሳችሁ በህግ ፊት ለፍርድ ስትቀርቡ ማየት እንዲያበቃኝ አጥብቄ እጸልያለሁ እታገላለሁ፡፡
የዉሸት ፍቅር እስከ መቃብር በሆነበት በወያኔ ፕሮፖጋንዳ ሳትፈቱ ክርስቲያን ወንድሞቸና እህቶቸ ስለእዉነት
ከሙስሊም ወጎኖቻችን ጎን አብረን ስለነጻነታችን እንጩህ፡፡ መስዋዕት መክፈል ካስፈለገም እንክፈል ይህን ማድረግ
ካልቻልን በኋላ የምንከፍለዉ ዋጋ እጅግ እጥፍ ይሆናል ልብ ያለዉ ልብ ይበል፡፡እግዚአብሔር የኢትዮጵያዊያንን ጩኸት ይስማ አሜን!
Posted By.Dawit Demelash
No comments:
Post a Comment